ዕለቱ በበርካታ አገራት ሠራተኞች በሚያካሂዷቸው የተቃውሞ ሠልፎች ይታሰባል
የምስሉ መግለጫ,ዕለቱ በበርካታ አገራት ሠራተኞች በሚያካሂዷቸው የተቃውሞ ሠልፎች ይታሰባል

ከ 5 ሰአት በፊት

ቀደም ሲል ሜይ ዴይ በበርካታ አገራት እንደ ጥንታዊ የፀደይ ፌስቲቫል ይታወቅ ነበር። አሁን ግን በዓለም ዙሪያ ባሉ ሠራተኞች ያደረጉትን ታሪካዊ ትግሎች እና ጥቅሞችን ለማስታወስ የላብ አደሮች ቀን (ወይም ዓለም አቀፍ የላብ አደሮች ቀን) በመባል ይታወቃል።

የተሻለ የሥራ ሁኔታ እና ለሠራተኛ ማኅበራት ተጨማሪ ድጋፍ የሚጠይቁ ሠልፎች በመላው ዓለም በየዓመቱ ይካሄዳሉ።

መጀመሪያ አካባቢ በተለያዩ የሶሻሊስት እና የኮሚኒስት ድርጅቶች እና የሠራተኛ ቡድኖች ይዘወተር ነበር።

ነገር ግን የመጀመሪያዎቹ ሰልፎች የተካሄዱት በዩናይትድ ስቴትስ ነበር። ሰልፎቹ በመስከረም ወር የመጀመሪያው ሰኞ ይከናወኑ ነበር።

በሃይማርኬት አደባባይ ቦምብ ሲፈነዳ የሚያሳይ ምስል

እንዴት ተጀመረ?

ብሪታኒያዊው የማኅበራዊ ተሃድሶ አራማጅ ሮበርት ኦውንን መሠረት በማድረግ በቀን ስምት ሰዓት ለመሥራት በመጠየቅ በአሜሪካ የሚገኙ የሠራተኛ ማኅበራት እአአ በ1986 ከተሞችን ያንቀጠቀጡ ሠልፎችን አካሄዱ።

ኦውን “ስምንት ሰዓት ሥራ፣ ስምንት ሰዓት መዝናኛ፣ ስምንት ሰዓት እረፍት” በሚል የስምንት ሰዓት ሥራ ሃሳብን አነሳ።

ትልቁ የሥራ ማቆም አድማ በቺካጎ ከተማ ሚያዝያ 23 የተካሄደ ሲሆን፣ 40 ሺህ ሠራተኞች እንደተሳተፉበት ይገመታል። በወቅቱ ያለምንም የሥራ ሰዓት ገደብ እና የእረፍት ቀናት ፋብሪካዎች ውስጥ ጠንክሮ መሥራት የተለመደ ነገር ነበር።

ቺካጎ የአሜሪካ ኢንዱስትሪ እና የሠራተኛ ማኅበር ማዕከል ነበረች።

በባለሃብቶች እና በፖለቲከኞች በበጎ ያልታየውን ሠልፍ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ቅሬታ ያላቸው ሠራተኞች እና አናርኪስቶች ተቀላቀሉት። በወቅቱ አናርኪስቶች የሚባሉት በሕግ የበላይነት እና አተገባበር ዙሪያ የተዋቀረ ማኅበረሰብን የሚቃወሙ ሰዎች ነበሩ።

ውጥረቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ። በፖሊስ እና በተቃዋሚዎች መካከል በተነሳ ግጭትም ቢያንስ አንድ ሰው ሲሞት በርካቶች ደግሞ ቆሰሉ።

በፖሊስ ጭካኔ የተበሳጩት የሠራተኛ ማኅበራት መሪዎች በዝነኛው የቺካጎ ሃይማርኬት አደባባይ በሳምንቱ ሌላ ሰላማዊ ሰልፍ ጠሩ።

እስካሁን ድረስ በትክክል ማንነቱ ያልታወቀ ግሰለብ ፖሊሶች ላይ ቦንብ ወረወረ። በፍንዳታው እና በተፈጠረው ድንጋጤ ሰባት ፖሊሶች ሲሞቱ 67 የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ቆስለዋል። በትንሹ አራት ሰልፈኞች ሲገደሉ ከ30 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቆስለዋል።

የሃይማርኬት እልቂት ወይም የሃይማርኬት ጉዳይ ተብሎ የሚታወቀውን ክስተት ተከትሎ ስምንት አናርኪስቶች በነፍስ ግድያ ወንጀል ተከሰው ፍርድ ቤት ቀረቡ። አንዳንዶቹ ጥፋታቸው በትክክል ባይረጋገጥም በሞት እንዲቀጡ ተወሰነ።

ቀኑን ለማስታወስም እአአ በ1889 በሰከንድ ኢንተርናሽናል የመጀመሪያ ኮንግረስ የሶሻሊስት እና የሠራተኛ ፓርቲዎች እና የ20 አገራት የሠራተኛ ማኅበራት ተወካዮች ስብሰባ ላይ ውሳኔ ተላለፈ።

በዕለቱ ሠራተኞች የመብት ጥያቄዎቻቸውን ያሰማሉ
የምስሉ መግለጫ,በዕለቱ ሠራተኞች የመብት ጥያቄዎቻቸውን ያሰማሉ

በርካታ አገሮች ሜይ ዴይን ተቀብሉ

በቺካጎ የነበረው ግጭት ለበርካታ የግራ ክንፍ ፓርቲዎች መነሳሳት ምክንያት ሆኖ አገልግሏል።

በደቡባዊ አውሮፓ ሜይ ዴይን ለመጀመሪያ ጊዜ ያከበሩት በወቅቱ የኦስትሮ-ሃንጋሪ ኢምፓየር የነበሩት ስሎቬኒያውያን እና ክሮአቶች ናቸው።

አስቸጋሪ የሥራ ሁኔታ፣ ዝቅተኛ ደመወዝ እና ረጅም የሥራ ሰዓት መኖሩ በሰርቢያ ያሉ ሠራተኞች በ1893 ለሜይ ዴይ ሠልፍ እንዲያዘጋጁ አነሳስቷቸዋል።

ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ፈጣን የኢንዱስትሪ ልማት መስፋፋት እና በሩሲያ የኮሚኒስት አብዮት ተጽዕኖ ምክንያት በዓለም ዙሪያ ያሉ ሠራተኞች ለመሠረታዊ መብቶቻቸው ታግለዋል።

በጀርመን የናዚ ፓርቲ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በ1933 የሠራተኞች ቀን ይፋዊ በዓል ሆነ። ነገር ግን በዓሉ እንዲከበር በታወጀ ማግስት ነፃ ማኅበራትን እንዲበተኑ መደረጉ ግን አግራሞትን ጭሯል።

ይህም የጀርመን የሠራተኞች እንቅስቃሴን ከሞላ ጎደል ቢያስቆምም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የሠራተኛ ማኅበራት እንደገና ተደራጅተዋል።

በቤልግሬድ የላብ አደሮች ቀን እአአ1950

ምሥራቅ እና ምዕራብ

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የዓለም የፖለቲካ ገጽታ ተለውጦ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ክፍፍሎች ይበልጥ ጎልተው መታየት ጀመሩ።

የላብ አደሮች ቀን እንደ ኩባ፣ የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት እና ቻይናን በመሳሰሉ የሶሻሊስት አገራት ውስጥ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው በዓላት አንዱ ሆኖ ለአስርት ዓመታት ተከብሯል።

በሞስኮ ቀዩ አደባባይ ከፍተኛ የፓርቲ እና የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት የሚካሄደው ሠልፍ የሶቪየት ወታደራዊ ኃይል ማሳያም ሆኖ ነበር።

የኮሚኒስት መሪዎች አዲስ የተጀመረመው በዓል እና አከባበር በአውሮፓ እና በአሜሪካ ያሉ ሠራተኞች በፀረ ካፒታሊዝም ትግል ውስጥ እንዲተባበሩ ያነሳሳቸዋል ብለው ያምኑም ነበር።

በዩጎዝላቪያ የሶሻሊስት ፌዴራላዊ ሪፐብሊክም ተመሳሳይ ነበር። በ1945 የላብ አደሮች ቀን በይፋ የመንግሥት በዓል ሆኖ በታወጀበት ወቅት ወታደራዊ ሰልፍ እና ጠንካራ መንግሥታዊ ፕሮፓጋንዳ ይካሄድ ነበር።

በሌሎች የዓለም ክፍሎች ደግሞ ማኅበራት እና ሠራተኞች የተሻለ የሥራ ሁኔታን ለመጠየቅ በላብ አደሮች ቀን ሠልፎችን ያዘጋጃሉ።

በአብዛኞቹ የቡድን 20 (ጂ20) አባል አገራት ምንም እንኳን ዝቅተኛ ሥራ አጥነት እና አዎንታዊ የሥራ ዕድል ዕድገት ቢኖርም፣ ደመወዝ ከመቀነሱ በላይ የደመወዝ ጭማሪው ካለፈው ዓመት የዋጋ ግሽበት ጋር መሄድ አለመቻሉን ዓለም አቀፉ የሠራተኛ ድርጅት (አይኤልኦ) በ2024 ባወጣው የትንበያ ዘገባ ገልጿል።

ባለፈው ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ በአስከፊ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሠራተኞች ቁጥር ወደ አንድ ሚሊዮን ጨምሯል ብሏል ድርጅቱ።

በመጠነኛ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሠራተኞች ቁጥር ደግሞ በ8.4 ሚሊዮን ገደማ ከፍ ብሏል።

በሃኖይ የላብ አደሮች ቀን ሲከበር