የ66ቱ አብዮት

4 መጋቢት 2024

ተሻሽሏል ከ 5 ሰአት በፊት

የካቲት 1966 ዓ.ም. የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፀሐይ መጥለቅ የጀመረችበት ጊዜ ነበር።

ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከተሜ ኢትዮጵያውያን ወደ አደባባይ ወጡ።

ይዘው በወጧቸው ጥያቄዎች የአጼውን ፀሐይ ቀስ በቀስ ማክሰም ጀመሩ።

የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ያስተዋወቀውን የትምህርት ዘርፍ ማሻሻያ በመቃወም ማስተማር አቆሙ።

የሁለተኛ ደረጃ እና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች “መሬት ላራሹ”፣ “የብሔር መብት ይከበር”፣ “ድህነት ወንጀል አይደለም” የሚሉ መፈክሮችን አንግበው አደባባይ ወጡ።

ታክሲ ነጂዎች አድማ መቱ። የሠራዊቱ ዝቅተኛ እና መካከለኛ አባላትም እንዲሁ እምቢተኛ ሆኑ። ሠራተኞችም ለአራት ቀናት ያህል የሥራ ማቆም አድማ አደረጉ።

ኃይለሥላሴ እና መንግሥታቸው ማጣፊያው አጠራቸው። ንጉሡ ለሠራዊቱ አባላት የደመወዝ ማሻሻያ አደረጉ። የአብዮቱ ማዕበል ግን ዙፋናቸውን ማናጋቱን አላቆመም።

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ለመብት እና ጥቅማቸው እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመሩ ስልሳ ዓመታት ተቆጥረዋል። የሠራተኞች እንቅስቃሴ በዘውዳዊ ሥርዓት ተወልዶ፣ በወታደራዊ አገዛዝ ጎምርቷል።

እንቅስቃሴው አንዴ ጋም አንዴ ፋም እያለ፣ በኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲን አልፎ እዚህ ደርሷል።

ለሠራተኞች መብት የታገሉ የእንቅስቃሴው መሪዎች በጃንሆይ ፊት ተነስተዋል፤ በአብዮቱ ተረሽነዋል።

በኢህአዴግ የሥልጣን ዘመንም የሠራተኛ እንቅስቃሴ መሪዎች መሳደድ እና መንገላታት እንደ ደረሰባቸው በወቅቱ መሪ የነበሩ ግለሰቦች ያስታውሳሉ።

ሥርዓቶች በተፈራረቁበት ዘመናት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ለመቁጠር የሚያዳግቱ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

ከእነዚህ ጥያቄዎች ገሚሶቹ የሠራተኞች መብት እና ጥቅም ላይ ትኩረት ያደረጉ ነበሩ። ገሚሶቹ ደግሞ በጠቅላላ የአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ነበሩ።

የኢትዮጵያ ሠራተኞች እንቅስቃሴ ፈር ይዞ፣ በተቋም መልክ ተደራጅቶ ጥያቄዎችን ማቅረብ የጀመረው በ1954 ዓ.ም. ነበር።

ከ1954 ዓ.ም. በፊት ሠራተኞች በማኅበር የመደራጀት ሕጋዊ መብት አልነበራቸውም።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) አመራር የነበሩት አቶ ክፍሉ ታደሰ “አብዛኞቹ የውጭ አገር ፋብሪካዎች ናቸው በጣም ጥቂት ነበሩ በኢትዮጵያውያን የተያዙት። የውጭ ካፒታል እና ትርፋቸውን ማብዛት ስለሚፈልጉ ለሠራተኛው የሚታገል ማኅበር ባይኖር ደስታቸው ነው” ይላሉ።

አጼ ኃይለሥላሴ ለኢሠአማ ህንጻ የመሠረት ድንጋይ ሲያኖሩ
የምስሉ መግለጫ,አጼ ኃይለ ሥላሴ ለኢሠአማ ህንጻ የመሠረት ድንጋይ ሲያኖሩ

የኢትዮጵያ ሠራተኞች እንቅስቃሴ ውልደት

እስከ 1950ዎቹ አጋማሽ የሠራተኛ ማኅበራትን ማደራጀትም ሆነ መመሥረት በጃንሆይ እና በአገዛዛቸው አይወደድም ነበር።

ሠራተኛ ማኅበራትም ሕጋዊ እውቅና አልነበራቸውም። ይህ ግን ሠራተኞች በማኅበር ደረጃ አይሁን እንጂ ከመደራጀት አላገዳቸውም።

‘የሠራተኞች ማኅበር’ የሚለው የስም ቅጥያ ባይኖራቸውም፣ ሠራተኞች በራስ አገዝ መረዳጃ ማኅበራት ሥር ይደራጁ ነበር።

አንዳንዶቹ ማኅበራት የአባላቶቻቸው የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል በማድረግ ረገድ የተሳካላቸው ነበሩ። ይህ በበኩሉ በመላ አገሪቱ ማኅበራት እንዲያብቡ መሠረቱን ጥሏል።

ኋላ ላይ ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ከዓለም አቀፍ እና አካባቢያዊ የሠራተኛ ድርጅቶች እንዲሁም ከአገር በቀል ራስ አገዝ መረዳጃ ማኅበራት ጫናው ሲበረታባቸው፣ ሠራተኞችን የተመለከተ ድንጋጌ ለማውጣት ተገደዋል።

ከስልሳ ሁለት ዓመታት በፊት በ1954 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ የአሠሪ እና ሠራተኛ ጉዳይ ድንጋጌ በሕግ መልክ ወጣ።

ዶ/ር አዳነ ካሴ “The Formative Period of the Ethiopian Labour Movement, 1962-1974” በሚል የኢትዮጵያ ሠራተኞች ንቅናቄ የመጀመሪያ አስር ዓመታት ጉዞን በሚዳስስ ጥናታቸው ላይ፣ ለማኅበራቱ መፈጠር የሠራተኞች አቤቱታዎች መበራከት የአሰሪ እና ሠራተኞች ድንጋጌ መውጣት ከፍተኛ ሚና እንዳለው አስፍረዋል።

የድንጋጌውን መውጣት ተከትሎ የመጣው የሠራተኛ ማኅበራት ሕጋዊ እውቅና ማግኘት በኢትዮጵያ ሠራተኞች ትግል ውስጥ የታየ ቀዳሚ ለውጥ መሆኑን ዶ/ር አዳነ ያነሳሉ።

የታሪክ ተመራማሪው ዶ/ር አዳነ አክለውም የድንጋጌው መውጣት በኢትዮጵያ ሠራተኞች እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ መለያ ነው ይላሉ።

ይህ ድንጋጌ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሠራተኛ ማኅበራት እንዲመሠረቱ መብት የሰጠ ነው።

አጼ ኃይለሥላሴ ከጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሃብተወልድ ጋር በመሆን የኢሠአማን ዋና ጽህፈት ቤት ሲመርቁ
የምስሉ መግለጫ,አጼ ኃይለ ሥላሴ ከጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሃብተወልድ ጋር በመሆን የኢሠአማን ዋና ጽህፈት ቤት ሲመርቁ

ሠራተኞች ተደራጅተው ጥቅሞቻቻውን እንዲያስከብሩ መብቶቻቸውን እንዲጠይቁ አበረታቷል። ከዚህ በተጨማሪም ዶ/ር አዳነ ይህ ድንጋጌ ሠራተኞች የአንድነትን ወይም የመደራጀትን ጠቀሜታ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል ይላሉ።

ከድንጋጌው መውጣት አንድ ዓመት በኋላ የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማኅበር (ኢሠአማ) በሚያዝያ 1955 ዓ.ም. ውልደቱን አገኘ።

ከኢሠአማ ሕጋዊ እውቅና ማግኘት በኋላ በርካታ ሠራተኞች በየፋብሪካዎቻቸው ተደራጁ፤ ነቁ፤ ማኅበርም መሠረቱ።

ተፈራ ኃይለ ሥላሴ “የኢንዱስትሪ እና የመንግሥት ሠራተኞች አስተዳደር እድገት” በሚለው መጣጥፋቸው በሠራተኛ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኩል ከ60-70 ሺህ አባላት ያሏቸው 109 ማኅበራት መመዝገባቸውን ጽፈዋል።

ኢሠአማ ከመንግሥት ጋር “ትዕግስት የሚፈታተን” የሚባለው አይነት ግጭት ውስጥ የገባው በምሥረታው ማግሥት ነው።

መንግሥት የኮንፈዴሬሽኑን ፕሬዝዳንት ከሥልጣን እንዲለቁ በማድረግ፣ ለመንግሥት ስስ ልብ ያላቸውን ግለሰብ እስከ መተካት የደረሰ ጣልቃገብነት ነበረው።

ኢሠአማም ቢሆን የጃንሆይን መንግሥት ላይ ጫና መፍጠር የሚችል ጥርስ አላወጣም ነበር። ከማኅበሩ ምሥረታ በኋላ ባሉት አስር ዓመታት ውስጥ ምንም አይነት ጫን ያለ ጥያቄም ሆነ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ አልሰጠም።

መንግሥት በሠራተኞች እና በማኅበራት ላይ ጡጫውን ሲያሳርፍ ተቃውሞ አለማሰማቱን ዶ/ር ሳሙኤል አንድርያስ አድማሴ በአንድ ጥናታቸው ላይ አስፍረዋል።

በፋብሪካዎች ውስጥ ያሉ የሠራተኛ ማኅበራት ለጠሯቸው የሥራ ማቆም አድማዎችም ድጋፉን እንደነፈጋቸውም በኢትዮጵያ ሠራተኞች ንቅናቄ ላይ ጥናቶችን ያካሄዱት ዶ/ር ሳሙኤል አክለዋል።

ለኢትዮጵያ ሠራተኞች እንቅስቃሴ ቅርብ የነበሩት አቶ ክፍሉ፤ “1956 የኢትዮጵያ ሠራተኞች የመጀመሪያውን የሥራ ማቆም አድማ ለማድረግ ሞከሩ፤ መንግሥትም አሠሪዎችም ተባብረው የሥራ ማቆም አድማውን አከሸፉ” ሲሉ ያስታውሳሉ።

የኢትዮጵያ ሠራተኞች እና አብዮቱ

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) የቀድሞ ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ዳዊ ኢብራሂም “የኢትዮጵያ ሠራተኞች ከየትኛውም ማኅበራዊ ኃይሎች በፊት ከወታደሩ አመጽ በፊትም ከፍተኛ የሆነ ጥያቄ አንስተው ነበር” ይላሉ።

አቶ ክፍሉ ታደሰም በተመሳሳይ “ተማሪዎች ዝም ብሎ ሰልፍ ማድረግ ነው፤ ታክሲ ነጂዎችም ታክሲ አንነዳም ነው ያሉት። ወሳኝ ነበር፤ የሠራተኞች ተሳትፎ ፋብሪካዎችን በሙሉ ቀጥ ነው ያደረገው” ሲሉ ይናገራሉ።

የመኢሶን መሥራች አባል የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው አሰገድ ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም።

አቶ አንዳርጋቸው “በአጭር የተቀጨ ረዥም ጉዞ” በተሰኘ መጽሐፋቸው የየካቲቱ እንቅስቃሴ የንዑስ ከበርቴው ክፍሎች በሆኑት በተማሪዎች፣ በታክሲ ሹፌሮች እና በሠራዊቱ አባላት የተመራ ነው ሲሉ ይከራከራሉ።

አቶ አንዳርጋቸው አክለውም ላብ አደሩ የየካቲት እንቅስቃሴን በግንባር ቀደምትነት እንዲመራ የሚያደራጀው የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም እና መስመር አልነበረውም ይላሉ።

‘የአብዮቱ ሠራተኛው (የላብ አደሩ) ነው ወይስ የንዑስ ከበርቴው?’ የሚለው ሙግት እንደተጠበቀ ሆኖ የኢትዮጵያ ሠራተኞችን እንቅስቃሴ ከየካቲቱ አብዮት ነጥሎ ማየት ግን የማይቻል ነው።

የየካቲቱ የኢትዮጵያ አብዮት ኢሠአማ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሥራ ማቆም አድማ እንዲጠራ ገፊ ምክንያት መሆኑን ዶ/ር አዳነ በዶክትሬት ጥናታቸው ላይ አስፍረዋል።

ዶ/ር አዳነ “Trade Unions and the State in Ethiopia, 1946-1991” በተሰኘው ጥናታቸው፤ “የ1966ቱ አብዮት መፈንዳት ኢትዮጵያውያን ሠራተኞችን ከነበሩበት አስከፊ ሰቆቃ አውጥቶ፣ አጠቃላይ የአብዮቱን ጉዞ የበለጠ የሚያፋጥን የሥራ ማቆም አድማ እንዲያደርጉ አበረታቷል” ይላሉ።

በአብዮቱ መባቻ ሰሞን በኢሠአማ ጽህፈት ቤት ሠራተኛ የነበሩት አቶ ክፍሉ ታደሰ በበኩላቸው፣ ከመምህራን እና ከታክሲ ነጂዎች የሥራ ማቆም፣ ከተማሪዎች ወደ አደባባይ መውጣት፣ ከወታደሮች ማመጽ በላይ የሠራተኞች ሥራ ማቆም “ወሳኝ ሚና ነበረው” ሲሉ ይከራከራሉ።

በጊዜው የነበሩት ፋብሪካዎች ውስን መሆናቸውን የሚያስታውሱት አቶ ክፍሉ፤ “የሠራተኞች የሥራ ማቆም በአገሪቱ የነበሩትን ፋብሪካዎች ለአራት ቀናት ‘ፓራላይዝ’ አድርጓቸዋል” ይላሉ።

አቶ ክፍሉ “የተደራጀ ሠራተኛ ሥራ ማቆሙ ከፖለቲካ አንጻር ጉልህ ሚና ነበረው። ወሳኝ የነበረ የፖለቲካ ሂደት ነበር። ተማሪዎች እና የታክሲ ነጂዎች ጀምረውታል፤ ነገር ግን የሠራተኞች መካተት እና በዚህ ሂደት መሳተፍ ነው ያንን ለውጥ የበለጠ ሥር የሰደደ እንዲሆን ያደረገው” ሲሉ ያክላሉ።

የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማህበር አመራሮችን የሚያሳይ ምስል
የምስሉ መግለጫ,የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማኅበርን (ኢሠአማ) የመሩ11 አመራሮች

የኢትዮጵያ ሠራተኞች የሥራ ማቆም ከማድረጋቸው በፊት ግን የኢሠአማ ጠቅላይ ምክር ቤት ለአንድ ሳምንት ያህል ተሰብስቧል።

እንደ አቶ ክፍሉ ገለጻ ኢሠአማ የካቲት አጋማሽ ላይ ስብሰባ ለማካሄድ ቀጠሮ ይዞ የነበረው በሠራተኛው ጉዳይ ላይ ነበር።

ነገር ግን ፋም ጋም ሲል የቆየው የየካቲት ተቃውሞ፣ ኢሠአማን ሠራተኛውን ብቻ ሳይሆን የማኅበረሰቡንም ጉዳይ የተመለከቱ ጥያቄዎችን እንዲያነሳ አድርጎታል።

ከጠቅላይ ምክር ቤቱ ስብሰባ በኋላ ኢሠአማ ያቀረባቸው 17 ጥያቄዎች ምላሽ የማያገኙ ከሆነ፣ የሥራ ማቆም አድማ እንደሚጠራ አስጠነቀቀ።

ከእነዚህ የኢሠአማ ጥያቄዎች መካከል የሠራተኛውን ፍላጎት የሚመለከቱ ጥያቄዎች አንደኛው መደብ ነበር።

እነዚህ ጥያቄዎች የሥራ ማቆም አድማ የማድረግ መብት፣ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል፣ የደመወዝ ስኬል ማሻሻያ፣ የሠራተኛ ጡረታ ከግብር ነጻ ይደረግ የሚሉትን ያካተተ ነው።

የትምህርት ዘርፍ ማሻሻያ ላይ ውይይት እንዲደረግ፣ ነጻ ትምህርት ተደራሽ እንዲሆን እና ለመምህራን ጥያቄ በአፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥም ኢሠአማ ጠይቋል።

የተማሪዎች እና የመምህራንን ጉዳይ ከሚያስተጋቡት ከእነዚህ ጥያቄዎች በተጨማሪ አጠቃላይ ሕብረተሰቡን የሚመለከቱ ጥያቄዎችንም አንስተዋል።

የሸቀጦች የዋጋ ቁጥጥር እንዲደረግ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት በኢንዱስትሪ ተቋማት የቦርድ አባል እንዳይሆኑ፣ ለኢትዮጵያውያን የሥራ ቅድሚያ እንዲሰጥ እና የሥራ ዕድል እንዲፈጠርም ኢሠአማ ጠይቋል።

የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ልጅ እንዳልካቸው መኮንን፣ ኢሠአማ ከዚህ በፊት ውጤታማ የሆነ ሥራ ማቆም አድማ ማድረግ ባለማቻሉ የየካቲት 66ቱን ጥያቄ እና ማስጠንቀቂያ ከቁብ ሳይቆጥሩ ችላ አሉት።

ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 1/1966 ዓ.ም. ድረስ የሥራ ማቆም አድማ አደረጉ።

የፋብሪካ ማሽኖች ቆሙ፤ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በራቸውን ከረቸሙ፤ አውሮፕላን ማረፊያው ተዘጋ።

አንዳርጋቸው አሰግድ በመጽሐፋቸው “ወደ 120 ሺህ የሚጠጉ ሠራተኞች ለአንድ ሳምንት ያህል ሥራ በማቆም አገሪቱን ቀጥ አደረጓት” ሲሉ ሁኔታውን ገልጸውታል።

የሥራ ማቆም አድማው ለአራት ቀናት ከቆየ በኋላ መጋቢት 1/1966 ዓ.ም. የሠራተኞችን ጥያቄ ቸል ብለው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልጅ እንዳልካቸው እና ኢሠአማ ስምምነት ላይ ደረሱ።

ሆኖም ጫና የበረታበት የአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ለጥያቄዎቹ መልስ ለመስጠት ቃል ከመግባት ውጪ ይኼ ነው የሚባል ተጨባጭ ምላሽ ለኢሠአማ አልሰጠም።

በግንቦት ወር 1969 ዓ.ም የዓለም ሠራተኞች ቀን ሲከበር መፈክር ይዘው የወጡ ሠራተኞች
የምስሉ መግለጫ,በግንቦት ወር 1969 ዓ.ም የዓለም ሠራተኞች ቀን ሲከበር መፈክር ይዘው የወጡ ሠራተኞች

የኢትዮጵያ ሠራተኞች እንቅስቃሴ ባለፉት ስልሳ ዓመታት

ዶ/ር ሳሙኤል እንድሪያስ “Trade Union Resurgence in Ethiopia” በተሰኘ የጥናት ሥራቸው “የኢትዮጵያ ሠራተኞች እንቅስቃሴ በስልሳ ዓመታት ዕድሜው እንደገና የማንሰራራት ባህሪ ያለው ነው” ይላሉ።

የኢትዮጵያ ሠራተኞች የስልሳ ዓመት ጉዞ በውጣ ውረዶች የተሞላ ነው።

አጼው እጃቸውን ተጠምዝዘው ባወጡት ሕግ የሠራተኛ ማኅበር እንዲመሠረት፣ ሠራተኞችም በማኅበር እንዲደረጁ ዕውቅና ቢሰጡም ማኅበራት ነጻ እና ገለልተኛ እንዲሆኑ ግን አይሹም ነበር።

በጫና የተፈጠረው ኢሠአማ ከምሥረታው በኋላ ያሉትን የመጀመሪያ ዓመታት፣ ዶ/ር አዳነ የትግል ዓመታት ሲሉ ይጠሯቸዋል።

እነዚህ ዓመታት ንቁ እና ገለልተኛ ኮንፌዴሬሽን ለመሆን ሲሰራ የነበረው ኢሠአማ፣ በአንድ በኩል ጠንካራ የሠራተኛ ማኅበራት መፈጠር ለፖለቲካ ሥልጣኑ እንደ ስጋት ሲመለከት ከነበረው የንጉሡ መንግሥት ጋር በሌላ በኩል ሲታገሉ የቆዩባቸው ዓመታት ነበሩ።

ከንጉሡ በኋላ የመጡት የፖለቲካ ሥርዓቶችም ቢሆኑ ከሠራተኛው እንቅስቃሴ ጋር ቅራኔ ውስጥ መግባታቸው አልቀረም። የእነዚህ ቅራኔዎች መነሻ የሠራተኞችን መብት እና ጥቅም የተመለከቱ ጥያቄዎች በመነሳታቸው ብቻ አይደለም።

የኢትዮጵያ ሠራተኞች እና ማኅበራቸው ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ጥያቄዎችን ከማቅረብ ወደ ኋላ አላሉም ነበር።

በየካቲት 1966 የፈነዳው የአብዮት ማዕበል በ1967 በአዲስ ዓመት ማግሥት ንጉሡን እና ዙፋናቸውን ቮልስዋገን ጠራርጎ ወሰዳቸው።

ጃንሆይ ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር፣ ባለሟሎቻቻው ደግሞ ወደ ‘ዓለም በቃኝ’ ከርቸሌ ተጋዙ።

በተማሪዎች፣ መምህራን፣ ሠራተኞች፣ ታክሲ ነጂዎች እና በሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች በመጣው አብዮት ወታደሩ ሥልጣን ጨበጠ።

አዲሶቹ ባለጠመንጃ አገር አስተዳዳሪዎች ከሠራተኛው እንቅስቃሴ ጋር ፍጥጫ የጀመሩት ሳይውሉ ሳያድሩ ነበር።

ደርግ ሥልጣን ላይ ከወጣ ጥቂት ቀናት በኋላ የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማኅበር ጠቅላላ ጉባኤ አካሂዶ ውሳኔዎችን አሳለፈ። አቶ ክፍሉ ኢሠአማ በወቅቱ መስከረም 1967 ላይ ጠቅላላ ጉባኤ የጠራው በራሱ በማኅበሩ ጉዳይ ላይ ለመወያያት እንደነበር ያስታውሳሉ።

አቶ ክፍሉ በስብሰባው ላይ “[ኢሠአማ] በራሱ ጉዳይ ላይ ማተኮሩን በመተው ሠራተኛው በአገራዊ ጉዳይ እንዲያተኩር ስምምነት ላይ ይደርሳል” ይላሉ።

ከሠራተኞች እንቅስቃሴ ጋር ቅርብ ግንኙነት ያላቸው አቶ ዳዊ ኢብራሂም፤ ኢሠአማ ከዚህ ስብሰባው በኋላ “ወታደራዊ አገዛዝ ለዚች አገር አይበጃትም፤ ስለዚህም ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም የሚል ጥያቄ አነሳ” ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪም “የኢትዮጵያ ችግር የሥርዓት ችግር ነው፤ ሕዝባዊ የሆነ መንግሥት ሳይቋቋም ለወታደራዊው መንግሥት መሠረት ለመጣል ተማሪዎች መዝመት የለባቸውም” በሚል የደርግን የዕድገት በኅብረት ዘመቻ መቃወሙን አቶ ዳዊ ያክላሉ።

ኢሠአማ በዚህ ብቻ አላበቃም። የሥራ ማቆም አድማ ለማደረግም ውሳኔ ላይ ይደርሳል።

ይህ የማኅበሩ ውሳኔ ደርጉ ጆሮ ደርሶ፣ ደርጉ የማኅበሩን አመራሮች ጠርቶ ውሳኔዎቻቸውን እንዲሰርዙ ማግባባቱን አቶ ክፍሉ ያስታውሳሉ።

የማኅበሩ አመራሮች ውሳኔውን ለመሰረዝ ባለመስማማታቸው በወቅቱ የኢሠአማ ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ በየነ ሰለሞንን ጨምሮ አራት አመራሮች በደርግ ታሰሩ።

ከዚያ በኋላ ባሉት ጥቂት ዓመታት ኢሠአማ የሥራ ማቆም አድማ ለማድረግ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርጉም የደርግ ምላሽ ግን የከፋ ነበር።

መስከረም 1968 ዓ.ም. ተጠርቶ ለነበረው የሥራ ማቆም አድማ ምላሽ ብቻ መቶ ገደማ ሰዎች መገደላቸውን ዶ/ር ሳሙኤል በአንድ ጥናታቸው ላይ አስፍረዋል።

አዲስ ዘመን ጋዜጣ በመስከረም 16/1968 ዓ.ም. ዕትሙ “በቦሌው ሁከት የሞቱት ሰዎች ብዛት ሰባት ደረሰ” በሚል ርዕስ በጊዜው የተገደሉ የአየር መንገድ ሠራተኞችን ጉዳይ ዘግቦ ነበር።

የኢሠፓ መስራች ጉባዔ
የምስሉ መግለጫ,የኢሠፓ መስራች ጉባዔ

ይህ ውዝግብ ለጥቂት ጊዜያት ከዘለቀ በኋላ ደርግ ኢሠአማን አፍርሶ፤ የመላው ኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራትን (መኢሠማ) ማቋቋሙን አቶ ዳዊ ይናገራሉ።

መኢሠማ የተቋቋመው ራሳቸው ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም በመሩት እና በአምቦ ከተማ ለ13 ቀናት በተካሄደ ስብሰባ መሆኑን አቶ ዳዊ ያክላሉ።

መኢሠማ በጊዜው ለወታደሩ ‘ሂሳዊ ድጋፍ’ በማድረግ ከደርግ ጋር ይሠራ የነበረው የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) ጋር ቅርበት ነበረው በሚል ይታማ ነበር።

አቶ ዳዊ ኢብራሂምም የመኢሠማ አመራሮች የሚሾሙት “ለደርግ ቅርበት ካላቸው ፓርቲዎች ነበር” ይላሉ።

አቶ አንዳርጋቸው አሰገድ በበኩላቸው፤ የኢሠአማ ውሳኔዎች የሚተላለፉት በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ነበር ይላሉ።

1968 አጋማሽ የተመሠረተው መኢሠማ ሚያዚያ 1978 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ፤ የማኅበሩ ስያሜ የመላው ኢትዮጵያ ሠራተኞች (መኢሠማ) መሆኑ ቀርቶ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበር (ኢሠማ) መሆኑን ይፋ አደረገ።

የሠራተኛ ማኅበሩ ስያሜውን የለወጠው ከአንድ ዓመት በፊት ከተመሠረተው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) ጋር የሚስማማ ለማድረግ መሆኑን ዶ/ር አዳነ በዶክትሬት ጽሁፋቸው ላይ አስፍረዋል።

ከደርግ ጋር ለ17 ዓመታት የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የቆዩት አማጽያን በ1983 የማዕከላዊ መንግሥቱን ሥልጣን ሲቆጣጠሩ መንትዮቹ ኢሠፓ እና ኢሠማ ኅልውናቸው አከተመ።

አቶ ዳዊ ሁኔታውን ሲያስታውሱ “ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ‘ኢሠማ የደርግ ተለጣፊ ነው’ ተብሎ ፈረሰ” ይላሉ።

ከደርግ ውድቀት እና ከኢሠማ መፍረስ በኋላ የሠራተኛ ማኅበሩን ለማደራጀት ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ፈጅቷል።

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፈዴሬሽን (ኢሠማኮ) ኅዳር 1986 ዓ.ም. በይፋ ተመሠረተ። አቶ ዳዊ ኢብራሂምም የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ።

ኢሠማኮ በምሥረታው ማግስት ነው ከመንግሥት ጋር ቅራኔ ውስጥ የገባው። ኢሠማኮ ከተመሠረተ ዘጠኝ ወራት በኋላ የኢህአዴግ መንግሥት ተግባራዊ ባደረገው የመዋቅር ማስተካከያ ፕሮግራም (Structrural Adjustment Program) ላይ ያለውን ተቃውሞ ሲያሰማ የቅራኔው ጅማሮ ሆነ።

አቶ ዳዊ በጊዜው የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውሱ፤ “ይሄ ጉዳይ ሠራተኛውን ይጎዳል፣ የሠራተኛ ቅነሳ ሊመጣ ስለሚችል ይጎዳናል እና [በውይይቱ] አሳትፉን አልናቸው። መጀመሪያ ትሳተፋላችሁ አሉን፤ በኋላ ኢኮኖሚው እንዲያገግም ስለምንፈልግ [ፕሮግራሙን] በፍጥነት ሥራ ላይ ማዋል ስላለብን አትሳተፉም ተባልን” ይላሉ።

ይህን ተከትሎ ኢሠማኮ የመዋቅር ማስተካከያ ፕሮግራሙን ተቃውሞ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ። በዚያው ቅጽበት በኢህአዴግ መንግሥት ጥርስ እንደተነከሰበት አቶ ዳዊ ያስታውሳሉ።

ዶ/ር ሳሙኤል Cycles of Mobilisation, Waves of Unrest: Ethiopian Labour Movement History በሚለው ጥናታቸው፤ መሠረታዊ ሠራተኛ ማኅበራት በሥራ ማቆም አድማ ጭምር ከኮንፌዴሬሽኑ ጎን ለመቆም ፍላጎት ቢያሳዩም፣ በኢሠማኮ አመራር ግን ተቀባይነት አለማግኘቱን አስፍረዋል።

ኮንፌዴሬሽኑ አባል የሆኑ የሠራተኛ ማኅበራትን ማስተባበርን መሠረት ባደረገ ስልት ከመታገል ይልቅ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰድን መርጧል።

ነገር ግን በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ፍርድ ቤት የኮንፌዴሬሽኑን ንብረቶች እና ሥራዎች አገደ፤ ፕሬዝዳንቱም ወደ ቢሮው እንዳይገቡ ተከለከሉ።

በጊዜው ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ዳዊ ኢብራሂም፤ “የመዋቅር ማስተካከያ ፕሮግራሙን በመቃወማችን ምክንያት የኮንፌዴሬሽኑ ሕጋዊ የእውቅና ምዝገባ ተሰረዘ” ይላሉ።

ከዚህ በኋላ አቶ ዳዊ ኢብራሂም በ1989 ዓ.ም. በኬንያ በኩል ወደ አውሮፓ ተሰደዱ።

ለ21 ዓመታትም በኔዘርላንድስ አምስተርዳም ቆዩ። ዶ/ር ሳሙኤል ከአምስት ዓመት በፊት በጻፉት መጣጥፍ ከዚህ ሂደት በኋላ የነበረውን ሁኔታ ሲያብራሩ፤

“በመሠረታዊ ማኅበራት እና በኢንዱስትሪ ፌዴሬሽንኖች አመራር ለመንግሥት ስስ ልብ ያላቸው ሰዎች ላይ አረፈ። ለሁለት አስርት ዓመታትም ፍዘት እና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ተከተለ” ይላሉ።

የኢትዮጵያ ሠራተኞች እንቅስቃሴ በስልሳ ዓመት ጉዞው ምን አሳካ? የሠራተኞች ሕይወት ምን ያህል ተሻሻለ? በእንቅስቃሴው ጅማሮ ከተነሱት ጥያቄዎች ምን ያህሉ ተመለሱ? እነዚህ ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ አብዮት 50ኛ ዓመት ባነር