ጠቅላይ ሚኒስትር ናታንያሁ
የምስሉ መግለጫ,ጠቅላይ ሚኒስትር ናታንያሁ

ከ 4 ሰአት በፊት

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ በቅርቡ በደቡባዊ ጋዛ፣ ራፋህ ከተማ ላይ አዲስ ወረራ እንፈጽማለን አሉ።

ናታንያሁ ይህን በራፋህ ላይ የታቀደው ዘመቻ “ከሐማስ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ብንደርስም ባንደርስም የማይቀር ጉዳይ ነው” ብለዋል።

ሐማስና እስራኤል ከመጋረጃ ጀርባ እያደረጉ ያሉት ድርድር ተስፋ እያሳየ መምጣቱ በሚነገርበት ወቅት ነው ናታንያሁ ይህን ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ጽኑ አቋማቸውን በሐማስ ቤተሰቦቻቸው የታገቱባቸው እስራኤላዊያን ጋር በነበራቸው ውይይት ነው ይፋ ያደረጉት።

“ራፋህ ከተማን ከመውረር የሚመልሰን ምንም ስምምነት አይኖርም።” ብለዋል።

የእስራኤል የምንጊዜም አጋር የሆነችው አሜሪካ ራፋህ ላይ የሚደረገው ወረራ እንዲቀር ትፈልጋለች።

ናታንያሁ ግን የጆ ባይደንን ተማጽኖና ማስጠንቀቂያ ቸል ያሉት ይመስላሉ።

ዋይት ሐውስ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ጆ ባይደን እሑድ ዕለት በነበራቸው የስልክ ጥሪ ራፋህ ላይ የሚደረግ ወረራን አሜሪካ እንደማትደግፍ ለናታንያሁ በማያወላዳ ሁኔታ ገልጸውላቸዋል።

ከዚህ ቀደም ጆ ባይደን ራፋህ ላይ የሚደረገው ወረራ “ቀይ መስመር” እንደማለፍ ይቆጠራል ብለው ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በራፋህ ላይ የሚፈጸም ጥቃት ብዙ ጦስ ይዞ ይመጣል ሲሉ አስጠንቅቀዋል። በእስራኤል ላይ ተጽእኖ ማሳደር የሚችሉ ኃያላን ሁሉ አሁኑኑ ሊረባረቡ ይገባል ነው የሚሉት ጉተሬዝ።

ዓለም አቀፉ የላብ አደሮች ቀን ለምን ሚያዝያ 23 ይከበራል?ከ 5 ሰአት በፊት

የጋዛ ጠቅላላ ነዋሪ ከግማሽ በላዩ አሁን የሚኖረው በራፋህ ነው። አሐዙም 2.5 ሚሊዮን ይገመታል።

አብዛኛው ፍልስጤማዊ ወደ ራፋህ የሸሸው ሕይወቱን ለማዳን ነው። ምክንያቱም በሰሜንና መካከለኛ ጋዛ እስራኤል መጠነ ሰፊ ዘመቻ ላይ ነበረች።

ከፍተኛ ሕዝብ ባለባትና በተጨናነቀችው ራፋህ እስራኤል ወረራ ከከፈተች ከፍተኛ እልቂት ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት አለ።

አሁን በራፋህ ከፍተኛ የምግብ፣ የመድኃኒትና የዉሃ እጥረት ተከስቷል።

የፍልስጤሙ መሐመድ አባስ ሰኞ ዕለት ራፋህ ላይ እስራኤል ወረራ ከፈጸመች “በፍልስጤም ታሪክ ትልቁ ጥፋት ሊደርስ ይችላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ናታንያሁ “ፍጹማዊ ድል” በሚል መሪ ቃል እየመሩት ያሉት ወረራ በምንም ዓይነት ስምምነት እንዲሰናከል አይፈልጉም። ግብ ያደረጉትም ሐማስን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተከፈለው ዋጋ ሁሉ ተከፍሎ ከምድረ ገጽ ማጥፋት ነው።

“ራፋህ እንገባለን። የሐማስን ባታሊዮን እንደመስሳለን። ስምምነት ተደረገም አልተደረገም ይሄን ወረራ የሚያስቆም ምድራዊ ኃይል የለም። ፍጹማዊ ድል ነው የምንጎናጸፈው” ብለዋል ናታንያሁ።

ሐማስ አግቶ ከወሰዳቸው 253 ታጋቾች 130 የሚሆኑት ያሉበት ሁኔታ በውል አይታወቅም። 34 የሚሆኑት እንደሞቱ ይገመታል። ቀሪዎቹ ደግሞ ተለቀዋል።

አሁን በራፋህ የሚገኙ ፍልስጤማዊያን አዲስ ጥቃት ሊከፈት ይችላል በሚል በከፍተኛ የአእምሮ ጭንቀት ውስጥ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት ኃላፊ ፊሊፔ ላዛሪኒ ተናግረዋል።

“ራፋህ ያሉ ባልደረቦቼ እንደሚነግሩኝ ከሆነ በዚያ ዜጎች በከፍተኛ ፍርሃትና ሰቀቀን ውስጥ ናቸው።”