ታጣቂዎች ጠመንጃ ይዘው

ከ 5 ሰአት በፊት

የዘንድሮው 49ነኛው ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ) “በጸጥታ ችግር” ምክንያት ከባሕር ዳርና ከኮምቦልቻ ውጭ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች “በአዳራሽ” ይከበራል።

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማሕበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሠማኮ) መሠረታዊ ጥያቄዎችን አነሳበታለሁ ባለው የዘንድሮው የሠራተኞች ቀን የአገሪቱ የጸጥታ ችግርና የኑሮ ውድነት መላ እንዲባሉ ጥያቄ እንደሚያነሳ አስታውቋል።

በዓሉ “ለሠላምና ኑሮ ውድነት መፍትሄ እንሻለን” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ለቢቢሲ የተናገሩት የቀድሞው የኢሠማኮ ፕሬዝዳንትና የአሁኑ የኮንፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አማካሪ አቶ ዳዊ ኢብራሂም፤ “ሠራተኞች አጣብቂኝ ውስጥ ወድቀዋል” ብለዋል።

በተለይም በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የቀጠለው ግጭት ሠራተኞች ተንቀሳቅሰው መስራት ካለመቻል ጀምሮ ግድያና እገታ እየተፈጸመባቸው ነው ብለዋል።

“በእነዚህ ክልሎች በስፋት ሠራተኛው ሰርቶ የመኖር፣ ሰርቶ በሰላም የመግባት [መብቱ] እጅግ በጣም አጣብቂኝ ውስጥ የገባበት ነው” በማለት የሠራተኞችን የእንቅስቃሴ ገደብ፣ ግድያና እገታ አንስተዋል።

በአማራ ክልል በርካታ ሠራተኞች ባሉባቸው ባሕር ዳር፣ ኮምቦልቻ፣ ደብረ ብርሃን፣ ቡሬ፣ ጎንደር በመሳሰሉ ከተሞች ሠራተኞች “አሳሳቢ ችግር” ውስጥ መሆናቸውን አቶ ዳዊ ተናግረዋል።

“የሚሞቱ ሠራተኞች አሉ፤ ዳታዎች [መረጃዎች] አሉን። የሰላም ማጣት ገፈት ቀማሹ ከታች ያለው ክፍል ነውና ሠራተኛው ከዚህ የህብረተሰብ ክፍል አንዱ ነው። ስለዚህ ሊነገር የማይችል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው” ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል ሙገር፣ መተሃራ፣ ወንጂ አካባቢዎች ሠራተኞች መገደላቸውን የሚያነሱት አማካሪው፤ “ሠራተኛው ስራ ሰርቶ ዳቦ ለማምጣት ሲሄድ በመንገድ መገደል፣ ተጠልፎ፤ ታግቶ መወሰድ ለሠራተኛው ብቻም ሳይሆን ለቤተሰቦቹ፣ ለልጆቹ፣ ለማሕበረሰቡም እጅግ ፈታኝ የሆነ ሰቆቃ ነው የሚያስከትለው” ብለዋል።

ባለፈው መጋቢት 2016 ዓ.ም. ለሳምንታት ታግተው የነበሩ አምስት የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች ተገድለው መገኘታቸው የሚታወስ ነው።

ኢሠማኮ አገሪቱ ላይ ያሉ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ እንዲሰጣቸው የጠየቀ ሲሆን፤ ለረጅም ጊዜ ሲጠይቀው የነበረው የኑሮ ውድነት ሠራተኛው ላይ እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ መላ እንዲባል ጠይቋል።

የኑሮ ውድነቱ “የሚሊዮኖችን ሕይወት እያናጋ ነው” ያሉት አቶ ዳዊ ኢብራሂም፤ ለመሠረታዊ ጥያቄው መንግሥት ምላሽ እንዲሰጣቸው ተማጽነዋል።

ኢሠማኮ ባለፈው ዓመት የሠራተኞች ቀን የኑሮ ውድነቱን ያስታግሳል ያለውን የገቢ ግብር ይቀነስ በማለት ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ቢያቅድም በመንግሥት ተሰርዞበታል።

ኢሠማኮ ከወራት በኋላ ነሀሴ 24፤ 2015 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚንስትሩና ከከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ጋር ምክክር ማድረግ ችሏል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ለኢሠማኮ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ይወሰን እና የገቢ ግብር ይቀነስ የሚሉት ሁለት ዋነኛ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት “አቅጣጫ” ሰጥተው ነበር ቢባልም፤ እስካሁን ድረሽ ምላሽ አለመገኘቱን አቶ ዳዊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚህም መንግሥት የሠራተኛውን ጥያቄ ለመመለስ ተጨባጭ እርምጃ አልተራመደም የሚሉት አማካሪው፤ ኢሠማኮ ግን ውትወታውን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

አማካሪው የሠራተኛውን ኑሮ እያቀጨጨ ነው ያሉት የገቢ ግብር ስርዓት እንዲሻሻል ኢሠማኮ ድርድር እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።

“. . . የሠራተኛውን የኑሮ ሁኔታ ያቀጨጨ የግብር አከፋፈል እንዲሻሻል እንፈለጋለን። ለምሳሌ 35 በመቶ የሚከፈለው [ግብር] ወደ 30፣ 28፣ 25 በመቶ በተጨባጭ ዳታ [መረጃ] ቀርቦ ድርድር ሊደረግበት ይገባል“ ያሉት አቶ ዳዊ፤ ይህ ሲሆን ግን በመግሥትና በድርጅቶች በጀት ላይ ቀውስ እንዳያስከትል መጠንቀቅ አለብን ብለዋል።

ከዚህ ባሻገርም ኢሠማኮ በፍጆታ እቃዎችና አገልግሎቶች ላይ የሚጣለው የተጨማሪ እሴት ግብር (ቫት) እንዲሁም ከውሎ አበል ላይ የሚቆረጠው ግብር እንዲነሳ መጠየቃቸውንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማሕበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሠማኮ) ባለፈው ዓመት የአሠሪና ሠራተኛ አማካሪ ቦርድ ስራ መጀመርና የኤጄንሲዎች የክፍያ ምጣኔ ምላሽ ማግኘቱን በበጎ በመውሰድ ተከታታይ ጥያቄዎችን ማቅረቡንና ግፊቱን ይቀጥላል ብለዋል።