Reuters

ከ 4 ሰአት በፊት

የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ መንግሥት በህገወጥ መንገድ በአውሮፓ የሚኖሩ ዜጎቹን ለመቀበል ያሳየው ተባባሪነት አናሳ ነው በሚል በኢትዮጵያውያን ላይ የጣለው ጊዜያዊ የቪዛ ገደብ እንዳሳዘናት ኢትዮጵያ አስታወቀች።

የአውሮፓ ህብረት ይህንን አቋሙን እንዲያጤነው በቤልጂየም፣ ብራስልስ ተቀማጭነቱን ያደረገው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ትናንት ሚያዝያ 22/ 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት (ካውንስል) ያስተላለፈው የእግድ ውሳኔ በህብረቱ አባል አገራት ለመኖር ህጋዊ ፍቃድ የተነፈጋቸው ኢትዮጵያዊ ዜጎችን በክብር፣ በስርዓት እና ዘላቂነት ባለው ሁኔታ እንዲመለሱ ለማድረግ ሁለቱ ወገኖች በቅርበት እየሰሩ ባለበት ወቅት ነው ሲልም መግለጫው አስፍሯል።

የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ከሰሞኑ በኅብረቱ ሕግ ሥር ያሉና ለኢትዮጵያውያን ቪዛ ለመስጠት ይውሉ የነበሩ አሠራሮች ላይ ገደብ መደረጉን አስታውቋል።

በዚህ ዕገዳ መሠረት፣ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ኢትዮጵያውያን በሚያቀርቧቸው ማስረጃዎች መሠረት ቪዛ ሲጠይቁ የሚያስፈልጓቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ማንሳት (waiving requirements) አይችሉም።

ኢትዮጵያውያን ከአንድ ጊዜ በላይ ወደ አውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ገብተው መውጣት የሚችሉበት ቪዛ (multiple entry) ማግኘት አይችሉም።

የዲፕሎማት እና አገልግሎት ፓስፖርት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ያለ ክፍያ ቪዛ እንዲሰጣቸው አይደረግም።

በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን ቪዛ ለማግኘት የሚጠብቁት ጊዜ ከ15 የሥራ ቀናት ወደ 45 የሥራ ቀናት ከፍ እንዲል ውሳኔ መተላለፉ ተገልጿል።

ለዚህም ውሳኔው የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎቹን ለመቀበል ያሳየው ተባባሪነት አናሳ መሆኑን ገልጾ “የኢትዮጵያ ባለሥልጣኖች ዜጎችን መልሶ ለመውሰድ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም” ብሏል።

ኢትዮጵያ በበኩሏ በሰጠችው ምላሽ ጊዜያዊ የቪዛ እግዱ ዜጎቿን ወደ አገራቸው ለመመለስ እና ከማህበረሰቡም ጋር መልሶ ለማዋሃድ በኢትዮጵያ እና በህብረቱ መካከል ያለውን ጠንካራ ትብብር ያላገናዘበ ነው ብላለች።

በተጨማሪም ውሳኔው ማንነትን ለማረጋጋጥ የሚደረገውን አድካሚ ሂደት ከግምት ውስጥ ማስገባት አልቻለም ሲል ኤምባሲው ተችቶታል።

የምክር ቤቱ እርምጃ “ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ከህብረቱ አባላት አገራት ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን የቅበላ ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራዊ እርምጃዎች ላይ እንቅፋት የሚፈጥር ነው ብሏል ከቤልጂየም በተጨማሪ ለሉክሰምበርግ ፣ ኔዘርላንድስ እና የአውሮፓ ህብረት የሚያገለግለው ኤምባሲው።

የአውሮፓ ህብረት አቋሙን እንደገና እንዲያጤን የጠየቀው ኤምባሲው ኢትዮጵያውያን ዜጎች ከአውሮፓ ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን አሰራር በተመለከተ ከተሰጠው ውሳኔ ጋር በሚጣጣሙ እርምጃዎች ላይ ይመክራል ብሏል።

ህብረቱ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ የአስቸኳይ ጊዜ የጉዞ ሰነዶች በመስጠት እንዲሁም በፍቃድ እና ያለ ፈቃድም የሚደረግ ስደተኞችን የመመለስ ሂደትን በተመለከተም ኢትዮጵያ “በቂ ትብብር አላደረገችም” ብሎ ነበር።

ስደተኞችን በመቀበል ረገድ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን “ትብብር” በድጋሚ እቃኛለሁ ያለው የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ውሳኔው ጊዜያዊ ቢሆንም ቀነ ገደብ አላስቀመጠም።

ህብረቱ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች እየተመሙ ያሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች እንደገጠሙት ያስታወቀ ሲሆን በየአገራቱ ያሉ ድንበሮች ጥበቃን ለማጠናከር እርምጃ መውሰዱም እየተገለጸ ነው።

ባለፈው ዓመት 380 ሺህ ስደተኞች የአውሮፓ ህብረት አገራትን ድንበር አቋርጠው “በህገወጥ መንገድ” ገብተዋል የተባለ ሲሆን ይህም ከአውሮፓውያኑ 2016 ወዲህ ከፍተኛው ቁጥር ነው።