መስከረም አበራ

ከ 39 ደቂቃዎች በፊት

“ኢትዮ ንቃት” የተሰኘው የዩቱዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት መስከረም አበራ ከአንድ ዓመት ከአራት ወር በፊት በዐቃቤ ህግ የተመሰረቱባትን ሁለት ክሶች እንድትከላከል በፍርድ ቤት ብይን ተሰጠ።

ብይኑን የሰጠው ትናንት ማክሰኞ ሚያዝያ 22፤ 2016 ዓ.ም የዋለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ልዩ ልዩ ከባድ ወንጀሎች ችሎት ነው።

መስከረም አበራ እንድትከላከል ብይን የተሰጠባቸው ክሶች በዐቃቤ ህግ የቀረቡት ባለፈው ዓመት ታህሳስ 26፤ 2015 ዓ.ም ነበር። ዐቃቤ ህግ በመስከረምላይ ያቀረበው ክስ የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ እና የወንጀል ህጉን ድንጋጌዎች በመጥቀስ ነበር።

የዐቃቤ ህግ ክስ “በኮምፒውተር ተጠቅማ በህብረተሰብ መካከል አመጽ፣ ሁከት እና ግጭት ለማነሳሳት ሞክራለች” የሚል ነበር።

ዐቃቤ ህግ ክሶቹን የመሰረታቸው መስከረም አበራ በባለቤትነት በምታስተዳድረው “ኢትዮ ንቃት” በተሰኘው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ከሁለት ዓመት በፊት የተላለፉ ሁለት ፕሮግራሞችን በመጥቀስ ነው።

ለክሶቹ ምክንያት የሆኑት ፕሮግራሞች በግንቦት 2014 ዓ.ም. የተለያዩ ቀናት የተላለፉ ናቸው።

ክሱን እየተመለከተ የሚገኘው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት “መስከረም አበራ በዐቃቤ ህግ የቀረበባትን ክስ ልትከላከል ይገባታል ወይስ በነጻ ልትሰናበት ይገባታል? የሚለው ላይ ብይን ለመስጠት” ለትናንት መቀጠሩን ጠበቃ ሄኖክ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ትናንት ማክሰኞ በሁለት ዳኞች የተሰየመው ችሎት፤ “ዐቃቤ ህግ ባቀረበው ማስረጃ መስከረም አበራ እነዚህ ሁለት ፕሮግራሞች ላይ ህብረተሰብን ከህብረተሰብ አመጽ እና ሁከትን የሚያነሳሳ ፕሮግራሞች አስተላልፋለች ብለን ያመንን ስለሆነ የቀረበባትን ክስ ልትከላከል ይገባታል” የሚል ብይን መስጠቱን ጠበቃው አብራርተዋል።

ካለፈው ዓመት ሚያዚያ 1፤ 2015 ዓ.ም ጅምሮ በሌላ ወንጀል ተከስሳ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ የምትገኘው መስከረም አበራ የትላንቱን የችሎት ውሎ በአካል ተገኝታ ተከታትላለች።

ከውሎው በኋላ የፍርድ ቤቱ ብይን “የጠበቀችው ነገር እንደሆነ” እና “ከዚህ የተለየ የጠበቀኩት ነገር የለም” ማለቷን ጠበቃዋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጠበቃ ሄኖክ ደንበኛቸው ላይ ክስ ከተመሰረተ በኋላ ፍርድ ቤቱ ብይን ለመስጠት ረዥም ጊዜ መውሰዱን፤ “በእኛ እምነት አንድ ዓመት ከአራት ወር ረጅም ጊዜ ነው ተከላከሉ ለመባል” ሲሉ ገልጸዋል።

“[ዳኞች] አልተሟላንም በሚል ቀጠሮዎች ሲሰጡ ነበር” የሚሉት ጠበቃ ሄኖክ መስከረም አበራ በሌላ ችሎት በቀረበባት የሽብር ወንጀል ክስ ምክንያት ቀጠሮዎች እንዳለፏት አስታውሰዋል።

ችሎቱ የትላንቱን ውሎ ከማጠናቀቁ በፊት ተከሳሿ መከላከያ የምታቀርብ ከሆነ መከላከያዋን ለማሰማት ለግንቦት 26፤ 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ጠበቃ ሄኖክ “በመከላከያው ምንድን ነው የሚቀርበው የሚለውን ዝርዝር ነገሮች በተመለከተ በእነዚህ ባሉት ቀናቶች ውስጥ ከመስከረም አበራ ጋር ተነጋግረን እናቀርበዋለን ወይም የሚሆነው ይሆናል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ነገር ግን መስከረም አበራ “ድካም ነው ፍርድ ቤቶች ላይ ብዙም እምነት የለኝም” የሚል ሃሳብ እንዳላት ጠበቃዋ ጠቁመዋል።

መስከረም አበራ ላይ ተመሰረቱት ሁለት ክሶች ምንድን ናቸው?

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ስነ ዜጋ መምህር የነበረችው መስከረም አበራ በአሁን ሰዓት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ ትገኛለች። መስከረም አበራ በቁጥጥር ስር የዋለችው ከአንድ ዓመት በፊት ሚያዝያ 1፤ 2015 ዓ.ም ነው።

አሁን ለእስር የተዳረገችበት እና ትናንት ብይን የተሰጠበት ወንጀል የተለያዩ ናቸው።

በትናንትናው ዕለት ብይን የተሰጠበት እና መስከረም የተከሰሰችበት ወንጀል ዐቃቤ ህግ ያቀረበው ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር መጀመሪያ ጊዜ በቁጥጥር ስር በዋለችበት ጊዜ ነው።

መስከረም አበራ ለ20 ቀናት በእስር ላይ ከቆየች በኋላ ዐቃቤ ህግ ክስ በመሰረተባት ዕለት በ50 ሺህ ብር ዋስትና ክሷን በውጭ ሆኖ እንድትከታተል በፍርድ ቤት ተወስኖ ነበር።

ዐቃቤ ህግ ክሱን የመሰረተው በእሷ እና በጊዜው የስራ ባልደረባዋ በነበረው አቶ አመሃ ደገፋ ላይ ነበር።

“ሁለተኛ ተከሳሽ በመዝገቡ ላይ ቢካተትም ነገር ግን ፖሊስ ላገኘው አልቻልኩም የሚል ምላሽ በተደጋጋሚ የሰጠ ስለሆነ የእሱ ክሱ እንዲቋረጥ ተደርጓል” ሲሉ ጠበቃ ሔኖክ ተናግረዋል።

በ21 ገጾች የተዘጋጀው የዐቃቤ ህግ ክስ፤ ተከሳሾቹ በ“ኢትዮ ንቃት” የዩቲዩብ ገጽ የተላለፉ ሁለት ፕሮግራሞችን በመጥቀስ ነው። ቀዳሚው ፕሮግራም ግንቦት 4፤ 2014 ዓ.ም. “መልዕክት ለጄኔራል አበባው ታደሰ” በሚል ርዕስ የቀረበ ነው።

ግለሰቦቹ “በኮምፒውተር ሥርዓት አማካኝነት በሕዝብ ደህንነት ላይ በሚፈጸም ወንጀል” ክስ እንደቀረበባቸው የዐቃቤ ህግ የክስ ሰነድ ያሳያል።

ተከሳሾቹ ባስተላለፉት ፕሮግራም፤ “የሰራዊቱን አንድነት የመሸርሸር ዓላማ ያነገበ፤ የአማራን ሕዝብ ለአመጽ እናብጥብጥ የሚጋብዝ አደናጋሪ መረጃ በመጻፍ እና እንዲሰራጭ [አድርገዋል]” ሲል ዐቃቤ ህግ ከስሷል።

ለሁለተኛው ክስ በዐቃቤ ህግ የተጠቀሰው ፕሮግራም ደግሞ በተመሳሳይ የዩቲዩብ ገጽ ግንቦት 7፤ 2014 “አማራ ክልል ምን እየተደረገ ነው?” በሚል ርዕስ የተላለፈ ነው።

በዚህ ፕሮግራም መስከረም አበራ “ሆነ ብላ ሁከት እና ግጭት ቀስቃሸ የሆነ ሀሰተኛ መልዕክት በማስተላለፍ” ተከስሳለች።

ከዚህ በተጨማሪ የዐቃቤ ህግ የክስ ሰነድ መስከረም ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ለአንድ ብሔር የቆሙ አድርጋ የሌላውን ብሔር ለአመጽ ለማነሳሳት እና የሀገርን አንድነት ለመከፋፈል አስባ ግጭት ቀስቃሽ መረጃ [አሰራጭታለች]” ይላል።

መስከረም አበራ ይህ ክስ ከተመሰረተባት በኋላ በዋስትና ከእስር ብትለቀቅም ከሶስት ወራት በኋላ በድጋሚ በቁጥጥር ስር መዋሏ ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎም ባለፈው ዓመት ሰኔ 2015 ዓ.ም ከሌሎች ግለሰቦች ጋር “የሽብር ድርጊት በመፈጸም” ወንጀል ክስ ቀርቦባታል።