ሠራተኛ ባርያ አይደለም የሚል መፈክር የያዙ ተማሪዎች

11 መጋቢት 2024

ተሻሽሏል ከ 4 ሰአት በፊት

መስቀል አደባባይ ላለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ቦታ ካላቸው ስፍራዎች መካከል አንዱ ነው።

ከአራት ኪሎ ለመውጣትም ወደ አራት ኪሎ ለመግባትም መስቀል አደባባይ ቅርብ ነው።

የመስቀል አደባባይ የፖለቲካ ንዝረት አራት ኪሎ ጮኽ ብሎ ይሰማል። ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የአገሪቱን የፖለቲካ ትኩሳት መለኪያ ቦታው መስቀል አደባባይ ነው።

መስቀል አደባባይ የባለጸጋ አጸድ ሳይመስል በፊት የአገሪቱ የፖለቲካ ትኩሳት መለኪያ፣ የብሶት ማስተንፈሻ ነበር። አገዛዞችን የሚያሞካሹ እና የሚነቅፉ ሰልፎች ተካሂደውበታል።

በአገዛዙ የልባቸው የደረሰም፣ ልባቸው የተሰበረም ድጋፋቸውን እና ተቃውሟቸውን ይዘው ወደዚሁ አደባባዩ ተምመዋል።

መስቀል አደባባይ አብዮተኞችም፣ አማኞችም፣ ዳንኪረኞችንም በየፊናቸው እኩል አስተናግዷል።

መስቀል አደባባይ የወጡ ጩኸቶች እና ጥያቄዎች ሁሉ ግን አራት ኪሎ አይሰሙም። ገሚሶቹ እዚያው አደባባዩ ላይ እንዲከስሙ ይደረጋሉ። ገሚሶቹ ጩኸቶች ከእነ አካቴው ወደ አደባባዩ እንዳይወጡ ይታቀባሉ።

ከእነዚህ የታቀቡ ጩኸቶች መካከል ግማሽ ሚሊዮን ሠራተኞችን የሚወክለው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፈደሬሽን (ኢሠማኮ) ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር የጠራው ሰልፍ አንዱ ነው።

ኢሠማኮ 48ኛውን የዓለም የሠራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ) ሚያዚያ 23/2015 ዓ.ም. የሠራተኞችን ቀን በመስቀል አደባባይ በሰላማዊ ሰልፍ ለማክበር አቅዶ ነበር።

የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ባለፈው ዓመት ሊካሄድ በተጠራው ሰልፍ “ከሠራተኛው መብት ጋር የተያያዙ ሦስት መሠረታዊ ጥያቄዎችን” ለማቅረብ ታቅዶ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኢሠማኮ በጠራው በሚያዝያው ሰልፍ ሊነሱ ከነበሩ ጥያቄዎች መካከል አንደኛው፤ “ለምንጠይቃቸው ለምናቀርባቸው ጥያቄዎች መልስ ስላጣን የውይይት መድረክ ይከፈትልን” የሚል ነበር።

ለሁለት ዓመታት ያህል ሥራውን አቁሞ የነበረው የአሠሪ እና ሠራተኛ አማካሪ ቦርድ ዳግም እንዲደራጅ መጠየቅ ደግሞ ሌላኛው ኢሠማኮ በሰልፍ ሊያቀርበው የነበረው ጥያቄ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም ከሠራተኛው ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል፣ ከመደራጀት እና ከመደራደር መብት ጋር የተያያዙ ሌሎች ጥያቄዎችንም በተመሳሳይ በሰልፉ ላይ ለማቅረብ ኮንፌዴሬሽኑ አቅዶ ነበር።

አቶ ካሳሁን ፎሎ የሠራተኛውን ጥያቄ በአደባባይ ከማሰማት ባለፈ የሰልፉን ዓላማ ሲያብራሩ፤ “አንደኛ የሠራተኛውን ጥያቄ እናስተጋባለን፤ ሁለተኛ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢሆኑ ይሄን ሰልፍ፣ ይሄን ጥያቄ ሲያዩ ያነጋግሩናል የሚል ተስፋ ስለነበረን ነው አደባባይ መውጣት የፈለግነው” ይላሉ።

ነገር ግን ሰልፉን የጠራው ኢሠማኮ፣ ዕቅዱም ሠራተኞቹም እግራቸው መስቀል አደባባይን አልረገጡም። ሚያዝያ ከፍላጎት እና ከዕቅድ አልፎ መሬት ላይ አልወረደም።

ሰልፉ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው ሰኞ ሚያዚያ 23/2015 ዓ.ም. ነበር። ለዚህም ኮንፌዴሬሽኑ እና አመራሮቹ ቀደም ብለው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በደብዳቤ ማስታወቃቸውን አቶ ካሳሁን ያነሳሉ።

አቶ ካሳሁን “ዓለም አቀፍ የሠራተኞችን በዓል ለማክበር ፈቃድ አይጠየቅም ነበር፤ መንግሥትም ያውቀዋል ካላንደርም ዝግ ነው። ይሄ ማለት በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀ የተፈቀደ በዓል ነው ማለት ነው። እኛ ደግሞ ካለው ሁኔታ አንጻር ቢያንስ የፀጥታ አካላት ሊመድቡልን ስለሚገባ ይወቁት ብለን በደብዳቤ እንዲያውቁት አደረግን” ሲሉ ሁኔታውን በዝርዝር ያስታውሳሉ።

በሰልፉ ዋዜማ እሁድ ሚያዝያ 22/2015 በመስቀል አደባባይ ድንኳን ለመትከል የሞከሩ የኢሠማኮ ባልደረቦች በስፍራው በነበሩ የፖሊስ አባላት “አይቻልም፤ ካልተፈቀደ በስተቀር አታዘጋጁም” ተባሉ።

አቶ ካሳሁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማን ሲያናግሩ “እናንተ የሜይዴይ በዓል ለማክበር ሳይሆን መንግሥትን ጥያቄ ልትጠይቁ ስለሆነ አይቻልም። አይደለም መስቀል አደባባይ የትኛውም ቦታ ላይ በአደባባይ መውጣት አትችሉም” መባላቸውን ይጠቅሳሉ።

ፕሬዝዳንቱ ከኃላፊዋ ጋር ነበራቸውን የስልክ ልውውጥ፤ “‘እንግድያውስ ሠራተኛው ይወጣል ከአሁን በኋላ ቅሩ ማለት አንችልም’ [አልኳቸው]፤ ‘ሠራተኛው ሲወጣ እናያለን እኛ አስፈላጊውን እርምጃ እንወስዳለን’ ብለው ስልክ ጆሮዬ ላይ ዘጉ” ሲሉ ያስታውሳሉ።

አቶ ካሳሁን አክለውም “ሠራተኛው ካለው የኑሮ ውድነት ሁኔታ፣ [ሰልፍ] አትወጣም ሲባል ስሜታዊ ሁኖ ግጭት ይፈጠራል። ግጭት ተፈጥሮ አንድ ሰው እንኳን ቢሞት ወይ ቢቆስል ልንመልሰው አንችልም። [ስለዚህ] ሠራተኛው ከተዘጋጀ በኋላ ሰልፉ እንዲቀር አደረግን” ይላሉ።

አቶ ካሳሁን እና የኢሠማኮ አመራር ጓዶቻቸው ሰልፉን ቢቷዉትም ጥያቄያቸውን ግን የሙጥኝ እንዳሉ ያዙ። መስቀል አደባባይ አይጠየቁም የተባሉት የሠራተኞች ጥያቄ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ጥያቄዎች ሁሉ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ገቡ።

ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ጀምሮ ጥያቄዎች ቤተ መንግሥት ቀረቡ ማለት ምላሽ ያገኛሉ ማለት አይደለም። እዚያው ቀልጠው የሚቀሩ እንዳሉ ሁሉ በሽንገላ የሚታለፉም አሉ።

በ1969 በአዲስ አበባ የሠራተኞች ቀን ሲከበር የታየ የሰልፍ ትርዒት

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ጥያቄ ከየት ተነስቶ የት ደረሰ?

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ጥያቄ የአንድ አዛውንት ዕድሜን አስቆጥሯል። እነዚህ ጥያቄዎች መልካቸውን እየቀያየሩ አሁንም ድረስ አሉ። ከፊሎቹ ጥያቄዎች ምላሽ ሲያገኙ፣ ቀሪዎቹ አሁንም ድረስ እንደ አዲስ እየተጠየቁ አሉ።

የሠራተኞች ጥያቄ ጅማሮ በአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ወቅት ነው። ከእነዚህ ጥያቄዎች ቀዳሚዎቹ የሥራ ሁኔታን እና መደራጀትን የተመለከቱ ነበሩ። እነዚህ ጥያቄዎች በየመሥሪያ ቤታቸው ማኅበራትን የመመሥረት እና ለእነዚህ ማኅበራት ሕጋዊ ዕውቅና ማስገኘት ከጥያቄዎቻቸው ቀዳሚው ነበር።

በኢትዮጵያ ሠራተኞችን በደመወዝ ማስተዳደር የተጀመረው በአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ነበር። ሆኖም ግን በአገሪቱ የግሉ ኢንዱስትሪ መነቃቃት የጀመረው በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ነው።

ነገር ግን ሠራተኞች የሚተዳደሩበት በመንግሥት ደረጃ የወጣ ሕግ እንዳልነበር፤ አቶ ተፈራ ኃይለ ሥላሴ “የኢንዱስትሪ እና የመንግሥት ሠራተኞች አስተዳደር እድገት” በተሰኘው መጣጥፋቸው ላይ አስፍረዋል።

አቶ ተፈራ በዚሁ መጣጥፋቸው “አሠሪው በመሰለው ደሞዝ እና የሥራ ሁኔታዎች ሠራተኛ የሚያስተዳድርበት አካሄድ ነበር የሰፈነው” ሲሉ ያክላሉ።

ከጣሊያን ወረራ በኋላ በ1936 ዓ.ም. የፋብሪካዎች መቆጣጠሪያ አዋጅ መውጣቱን አቶ ተፈራ ይገልጻሉ። የአዋጁ ዋና ትኩረት፤ “ፋብሪካዎች ስለሚሠሩበት ሁኔታ እና በውስጣቸው የሚተከሉት መሳሪያዎች በሠራተኞች ላይ አደጋ እንዳያደርሱ” መመሪያ ማውጣት ነበር።

አቶ ተፈራ “በ1952 ዓ.ም. ፍትሐ ብሔር ሕግ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ የሠራተኞችን የሥራ ሁኔታዎችን የሚደነግጉ እና የሥራ ክርክሮች የሚፈቱበት ሥርዓት በማቋቋም ረገድ ምንም ዕድገት አልታየም” ሲሉ ያክላሉ።

የአሰሪ እና ሠራተኛ መብቶች እና ግዴታዎችን የደነገገው የፍትሐ ብሔር ሕግ፤ “የጌታ እና የሎሌ የነበረውን የአሠሪ እና ሠራተኛ ግንኙነትን” ማሻሻሉን አቶ ተፈራ ይገልጻሉ።

ነገር ግን የፍትሐ ብሔር ሕጉ መደበኛ የቀኑን እና የሳምንቱን የሥራ ሰዓቶች ባለመወሰኑ “ሠራተኛውን ለብዝብዛ አጋልጦታል።” የሥራ ክርክር የሚፈታበትን ሥርዓት አለማቋቋሙ ሌላኛው የፍትሀ ብሔር ሕጉ ውስንነት ነበር።

ከፍትሐ ብሔር ሕጉ መውጣት አራት ዓመት በኋላ እነዚህን ውስንነቶች የሚሸፍነው የአሠሪ እና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ በ1956 ዓ.ም. ወጣ። አዋጁን ተከትሎ በፍትሐ ብሔር ሕጉ ያልተካተቱት የሥራ ሰዓት፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያ፣ የሕዝብ በዓላት፣ የዓመት ፈቃድን እና ሌሎች የሥራ ሁኔታዎችን በማሻሻል ደንብ ወጣ።

የአሠሪ እና ሠራተኛ አዋጁ የሠራተኛ ማኅበራትን በተመለከተም ትልቅ ለውጥ ያመጣ ነበር። የፍትሐ ብሔር ሕጉ ሠራተኞች የሙያ የሥራ ማኅበር ማቋቋም እንደሚችሉ ቢደነግግም፤ የማኅበሩን ተግባራት ግን አልደነገገም ነበር።

ዶ/ር አዳነ ካሴ “The Formative Period of the Ethiopian Labour Movement, 1962-1974” በተሰኘ ጥናታዊ ጽሁፋቸው “በ1948 የተሻሻለው ሕገ መንግሥት እና የፍትሐ ብሔር ሕጉ ላይ አንዳንድ የሠራተኛ ጉዳዮች ቢካተቱም የሠራተኛ ግንኙነት ተገቢ ትኩረት አልተሰጠውም” ይላሉ።

ሕገ መንግሥቱ ለሠራተኞች ማኅበር የማቋቋም መብት ቢሰጥም የፍትሐ ብሔር ሕጉ የሠራተኞች ማኅበራትን እንደ ሌሎች ማኅበራት ስለቆጠራቸው፤ የአሠሪ እና ሠራተኛ ጉዳይ ድንጋጌ እስከ ወጣበት ጊዜ ድረስ የአሠሪ እና የሠራተኞች ማኅበራት አልነበሩም።

ከዚህ ድንጋጌ በኋላ ግን በተለይ ሠራተኞች በማኅበር ተደራጅተው ሕጋዊ እውቅና አግኝተው ለመመዝገብ አፍታም አልወሰደባቸውም። ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማኅበር (ኢሠአማ) ውልደቱን አገኘ።

ድንጋጌው ሠራተኞች የሠራተኛ ማኅበራትን የመመሥረት መብት ከመስጠቱ በተጨማሪ ለሠራተኛ ማኅበራት አመራሮች እንዲሁም ለሠራተኞች እኩል የመደራደር አቅምን ፈጥሯል።

አቶ ተፈራ ኃይለ ሥላሴ፤ “በትምህርት ደረጃ ከሰርቶ አደሩ ከፍ ብለው የሚታዩ” ያሏቸው (white collar workers) በማኅበር የመደራጀት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዳልነበራቸው ያስታውሳሉ።

በአጭር ጊዜ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ማኅበራትን እና በ100 ሺዎች አባላትን በስሩ የያዘው ኢሠአማ የሠራተኞችን ጥያቄ ለመንግሥት ለማቅረብ ዓመታት ፈጅቶበታል።

ከኢሠአማ ምሥረታ በኋላ ባሉት አስር ዓመታት ውስጥ ከሠራተኞች ጋር የተያያዘ ምንም ዓይነት ጫን ያለ ጥያቄም ሆነ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ (ultimatum) አልሰጠም።

ከመንግሥት በኩል በሠራተኞች እና በማኅበራት ላይ የሚያርፈውን ጡጫም በተመለከተ ተቃውሞውን አያሰማም ነበር።

ዶ/ር ሳሙኤል አንድሪያስ በፋብሪካዎች ውስጥ ያሉ የሠራተኛ ማኅበራት ለጠሯቸው የሥራ ማቆም አድማዎችም ድጋፉን እንደነፈጋቸው በአንድ ጥናታቸው ላይ አስፍረዋል።

ኢሠአማ ጠንካራ ጥያቄዎች ያቀረበው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ማገባደጃ ላይ ነው። ኢሠአማ በ1966 ዓ.ም አጋማሽ 17 ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትር ልጅ እንዳልካቸው መኮንን አቀረበ።

እነዚህ ጥያቄዎች ግን የሠራተኛው መብት እና ጥቅም ላይ ያተኮሩ ብቻ አልነበሩም። ከአገሪቱ የወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት ጋር የተያያዙ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችንም አካታትዋል።

ኢሠአማ ካቀረባቸው ጥያቄዎች መካከል ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል፣ የደመወዝ ማሻሻያ፣ የሠራተኛ ጡረታ ፈንድ ከገቢ ታክስ ነፃ እንዲሆን፣ ያለ በቂ ምክንያት ከሥራ መባረር እንዲቀር፣ አዲስ ማኅበራትን መመሥረት እና የሥራ ማቆም አድማ ማድረግ ይገኙበታል።

ኢሠአማ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፈው ደብዳቤ “የሠራተኛው መብት እና ጥቅም እንዲጠበቅ በማለት በየጊዜው የተጠየቁት የሠራተኛው ጉዳዮች ምንም ዓይነት ውጤት ባለማግኘታቸው ለመጨረሻ ጊዜ” ጥያቄ ማቀረቡን ያትታል።

ኢሠአማ ባስቀመጠው ቀነ ገደብ መሠረት ምላሽ ባለማግኘቱ ለአራት ቀን የቆየ የሥራ ማቆም አድማ ተደረገ።

በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጋቢት 1/1966 ዓ.ም. ከኢሠአማ ስምምነት ላይ ደረሱ።

ሆኖም ጥያቄዎቹ “በዚህ ያህል ጊዜ ለፓርላማ ይቀርባል፤ ይኼኛው ጥያቄ በኮሚቴ ይታያል” ከሚሉ ሽንገላዎች ውጭ ይሄ ነው የሚባል ተጨባጭ ምላሽ አልሰጠም።

አጼ ኃይለ ሥላሴ እና መንግሥታቸው ለሠራተኞች ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ሳይሰጡ የየካቲት አብዮት እሳቸውንም ባለሟሎቻቸውንም ጠራርጎ ወሰዳቸው።

የኢሠአማ 17 ጥያቄዎች ለሠራተኛው በቀጥታ ካስገኙት ጥቅም ይልቅ በጥቅል ለሥርዓት ለውጥ ያበረከቱት ሚና የላቀ ነው።

ጥያቄዎቹም ሠራተኛውን ብቻ የሚመለከቱ ሳይሆኑ ከሌሎች የሕብረተሰቡ ክፍሎች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጥያቄዎች ጋር ተዳብለው የቀረቡ ነበሩ።

በ1969 ዓ.ም በአዲስ አበባ የዓለም አቀፉ የሠራተኞች ቀን ሲከበር

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ጥያቄ እና ደርግ

የዛሬ 50 ዓመት የፈነዳውን አብዮት ተከትሎ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት የገባው ወታደራዊ መንግሥትም የሠራተኞችን ጥያቄ ያስተናገደበት አኳዃን፤ “ከእጅ አይሻል ዶማ” ዓይነት ነበር።

የቀድሞው የኢሠማኮ ፕሬዝዳንት አቶ ዳዊ ኢብራሂም፤ “በጠቅላላው የሠራተኛ ማኅበራት አጠቃላይ መብቶቻቸው ክፉኛ የተጣሱበት ሁኔታ ነበር” ይላሉ።

አቶ ዳዊ አክለውም፤ “የሠራተኛው እንቅስቃሴ ላይ በደርግ ጊዜ አንዲት ጸጋ ብቻ ናት የነበረችው፤ ይሄም የሠራተኛ ማኅበራቱ ቁሳዊ የሆነ መሠረት ጥሏል” ሲል ያክላሉ።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) አመራር የነበሩት አቶ ክፍሉ ታደሰ “የደርግ እና የሠራተኛው እንቅስቃሴ በቅራኔ የተሞላ ነበር” ይላሉ። ለዚህም በማሳያነት የሚያነሱት የሠራተኛ ማኅበራት ለሚጠይቋቸው ጥያቄዎች የደርግ ምላሽ በመሳሪያ የታጀበ መሆኑን ነው።

ዶ/ር ሳሙኤል አንድሪያስ ከአብዮቱ በኋላ ባሉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የሚገኙ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ያነሳሉ።

ከ1967 እስክ 1969 ባሉት ሦስት ተከታታይ መስከረሞች የሥራ ማቆም አድማዎች በተለያዩ የስኬት ደረጃዎች መደረጋቸውን፣ ነገር ግን አንዳቸውም በ1966 ዓ.ም. የካቲት መጨረሻ ከተደረገው ጋር አይስተካከሉም ይላሉ።

የወታደራዊው መንግሥት አጸፋም የከፋ እንደነበር የሚገልጹት አጥኚው በ1967 በተሞከረው የሥራ ማቆም አድማ ምክንያት 100 ሰዎች መደገላቸውን እና 1600 ሰዎች መታሰራቸውን ጽፈዋል።

ዶ/ር ሳሙኤል “Trade Union Resurgence in Ethiopia” በተሰኘው ጥናታዊ ጽሁፋቸው በወታደራዊው አስተዳደር የሠራተኞች ደመወዝ ላይ ይሄ ነው የሚባል ለውጥ እንዳልነበር አስፍረዋል።

በ2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም በተከበረው የሠራተኞች ቀን ላይ የታዩ መፈክሮች
የምስሉ መግለጫ,በ2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም በተከበረው የሠራተኞች ቀን ላይ የታዩ መፈክሮች

“የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ”

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ከአራት ሥርዓቶች በኋላም ከስልሳ ዓመታት በፊት ለጠየቋቸው ጥያቄዎች ምላሽ አላገኙም። የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) አሁንም ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወሰን እየጠየቀ ነው።

የአገሪቱ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ጉልህ መሻሻል ቢያሳዩም የሠራተኞች ጥያቄ ግን አሁንም ባለበት እየረገጠ ነው። የኢሠማኮ ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ የሠራተኛ ማኅበራትን ማደራጀት “ትልቅ ተግዳሮት” እንደሚገጥማቸው ይናገራሉ።

አቶ ካሳሁን “ብናደራጅም ባደራጀነው ማግስት ይፈርሳል፤ አደራጅተን ስንመጣ መሪዎቹ ይባራራሉ እነሱን ወደ ሥራ ለማስመለስ ፍርድ ቤት እንመላለሳለን” ሲሉ በምሬት ይናገራሉ።

የአቶ ካሳሁን አማካሪ የሆኑት የቀድሞው የኢሠማኮ ፕሬዝዳንት አቶ ዳዊም በተመሳሳይ፤ “ዛሬም ሠራተኞችን ለማደራጀት እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው። ይሄ ሁሉ ሕግ እያለ ማደራጀት አትችልም። ከተደራጀ በኋላ ያፈርሱታል ከተደራጀ በኋላ የማኅበር መሪ ያባርራሉ” ይላሉ።

ኢሠማኮ ሠራተኞችን ለማደረጃት ችግር የሚገጥመው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተቋቋሙት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ነው።

አቶ ዳዊ “የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሠራተኞችን ለማደራጀት አምስት ዓመት ነው የፈጀው” ሲሉ ይናገራሉ። በተመሳሳይ አቶ ካሳሁን ፎሎ “ዱከም ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ 103 ድርጅቶች አሉ፤ እዚያ ውስጥ አንድም ሠራተኛ ማኅበር አልተደራጀም” ይላሉ።

“ዝቅተኛ ደመወዝ ወለል ይወሰን የሚለው ጥያቄ የተነሳው በ1966 ዓ.ም. ነው። የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ቦርድ ተቋቁሞ ይወሰናል ነው ያለው። ነገር ግን ዛሬም ቦርድ ተቋቁሞ ይወሰናል እያልን ነው ያለነው” ሲሉ አቶ ዳዊ በምሬት ይናገራሉ።

አቶ ዳዊ ኢብራሂም የሠራተኞች ጥያቄ እስካሁን ድረስ ምላሽ ማግኘት ያልቻለው፤ “ኢትዮጵያ ሥርዓት መዘርጋት ስላልቻለች ነው” ይላሉ።

አቶ ክፍሉ ታደሰ በበኩላቸው ምክንያት የሚሉትን “ከደርግ ጀምሮ በንጉሡም ጊዜ ያው ነው፤ የመጡት ሁሉም ሥርዓቶች አምባገነኖች ናቸው፤ በነጻነት የሚደራጅ፣ በነጻነት ሃሳቡን የሚገልጽ፣ በነጻነት መሰብሰብ የሚችል፣ በነጻነት የሚተች፣ በምርጫ ሂደት ላይም የፈለገውን እመርጣለሁ የሚል አቆጥቁጦ እንዲያብብ አይፍልጉም” ሲሉ ያስቀምጣሉ።

“መብት አይሰጥም ይታገሉለታል እንጂ” የሚሉት አቶ ክፍሉ፤ “ሠራተኛው በራሱ ጉልበት በራሱ ጥረት መብቱን ካላስከበረ መንግሥት ለሠራተኛው ሊቆምለት አይችልም። ሠራተኛውን አደራጅቶ አደባባይ ወጥቶ መሞገት መቃወም ሃሳብን ማሰማት ያስፈልጋል” ሲሉ መፍትሄ ያሉትን ይጠቁማሉ።

ካለፈው ዓመት የ“ሜይዴይ” ሰልፍ መከልከል በኋላ የሠራተኛው ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ ይችላል የሚል ተስፋ በኢሠማኮ አመራሮች በኩል ተፈጥሯል። ይህ ተስፋ የኢሠማኮ አመራሮች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ከተወያዩ በኋላ የመጣ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በውይይቱ ወቅት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን የሚወስነውን ቦርድ ለማቋቋም ቃል መግባታቸውን አቶ ካሳሁን ይገልጻሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሠራተኞች ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ቃል በመግባት የመጀመሪያው መሪ አይደሉም። ከእሳቸው በፊት የነበሩ መሪዎችም ለሠራተኛው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ቃል ገብተዋል፤ አሁን ግን ሠራተኛው እነዚያኑ ጥያቄዎች እየጠየቀ ነው።

ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን የሚወስን የደመወዝ ቦርድ እንደሚቋቋም የሚደነግገው አዲሱ የአሠሪ እና ሠራተኛ አዋጅ የጸደቀው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ነው።

ይህ አዋጅ ከጸደቀ አምስት ዓመታት ቢያልፉም እስካሁን ግን የደመወዝ ወለል አለመቋቋሙን ልብ ይሏል።

ሃምሳ ዓመታትን ከደፈነው አብዮት ቀደም ብለው የተነሱት እና በአብዮቱ ወቅትም ሠራተኛው ያነገባቸው ጥያቄዎች አሁንም ምላሽ ሳያገኙ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ከዚህስ በኋላ ምላሽ ለማግኘት ምን ያህል ጊዜ ይጠይቅ ይሆን?

የኢትዮጵያ አብዮት ባነር