ምክትል ፕሬዚዳንት ጄነራል ታደሰ ወረደ

1 ግንቦት 2024, 17:31 EAT

የትግራይን ጦርነት ተከትሎ በአማራ ክልል ስር ተጠቅለው የተቋቋሙ አስተዳደራዊ መዋቅሮች እስከ ሰኔ 30/ 2016 ዓ.ም መፍትሔ እንደሚያገኙ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ጄነራል ታደሰ ወረደ ተናገሩ።

ጄነራል ታደሰ ባለፉት ሁለት ቀናት የፕሪቶሪያ ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት አተገባበር በተመለከተ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከመከላከያ እና ከፌደራል መንግሥት ባለስልጣናት ጋር ያደረጉትን ውይይት መሰረት በማድረግ ዛሬ ሚያዝያ 23/ 2016 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ ነው ይህንን የተናገሩት።

የአማራ ክልል ይገባኛል በሚላቸው እና የትግራይን ጦርነት ተከትሎ ክልሉ ጠቅልሎ እንደ አዲስ ባዋቀራቸው የደቡብ ትግራይ እና ጸለምቲ ወረዳዎች አስተዳደሮች እንደሚፈርሱ እና ተፈናቃዮች እንዲመለሱ እስከ ግንቦት 30/2016 ዓ.ም የጊዜ ሰሌዳ ስምምነት ላይ መደረሱን ጄነራል ታደሰ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በአማራ ክልል በኩል ወልቃይት ተብሎ በሚጠራው ምዕራብ ትግራይ እንደ አዲስ የተቋቋመው አስተዳደር እስከ ሰኔ 30 ባለው ጊዜ ይፈርሳል ብለዋል።

በዚህም ውይይት ላይ ትጥቅ መፍታትን አስመልክቶ የትኞቹ አስተዳዳራዊ መዋቅሮች መፍረስ እንዳለባቸው እና የተፈናቀሉ ዜጎች እንደሚመለሱ ዝርዝር እቅድ የወጣ ሲሆን ይህንንም የሚቆጣጠረው እና የሚያረጋግጠው የአፍሪካ ኅብረት የስምምነት ክትትል አረጋጋጭ እና አስከባሪ ኮሚቴ እንደሚሆን ተገልጿል።

ኮሚቴው መቀለ ላይ ቢሮ እንዳለው ከዚህ ቀደም ጄነራል ታደሰ መናገራቸው ይታወሳል።

ተፈናቃዮቹ ወደቀያቸው ከመመለሳቸው በፊት “መሬታቸው፣ ቤታቸውና እርሻቸው ተይዞ ስለሚገኝ በመጀመሪያ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር” መረዳዳት ላይ መደረሱን ነው የገለጹት።

ጄነራሉ በዛሬው መግለጫቸው በትግራይ በኩል የታጠቁ ኃይሎችን ከአካባቢው ለማስወጣት እና በዚያኛው ወገን ሰፍረው ያሉ ነዋሪዎች ከአካባቢው እንዲወጡ መግባባት ላይ መደረሱን በክልሉ ላሉ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ገልጸዋል።

እነዚህ ስፍራዎች በማን ቁጥጥር ስር ይሆናሉ? የሚለው ጥያቄ በቀጣዩ ምዕራፍ እንደሚታይ ጄነራሉ ቢናገሩም የትግራይ ኃይሎች ከየትኛው አካባቢ እንደሚወጡ ተጨማሪ መረጃ አልሰጡም።

የፕሪቶሪያን ስምምነት ተከትሎ ተግባራዊ ካልሆኑ ጉዳዮች አንዱ ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው የመመለስ ጉዳይ እንደሆነ ከሁለት ሳምንት በፊት የተናገሩት ጄራል ታደሰ በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት በተደረገው ውይይትም መግባባት ላይ እንደተደረሰም ገልጸው ነበር።

በወቅቱ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር መግባባት ላይ ተደርሶባቸዋል ካሏቸው ጉዳዮችም መካከል “ተፈናቃዮችን ለመመለስ በዋነኝነት በደቡብ እና ምዕራብ ትግራይ የተቋቋሙ ህገ ወጥ አስተዳደሮችን ማፍረስ፤ የተደራጁ ታጣቂ ቡድኖችን መበተን” ተፈጻሚ እንደሚሆኑም ጠቅሰዋል።

በዋነኝነት ይህንን የሚተገብረው የመከላከያ ሰራዊት እንደሆነ በወቅቱ ገልጸው ነበር።

ባለፉት ሳምንታት የራያ አላማጣ አካባቢዎች እንደ አዲስ ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ የተለያዩ አወዛጋቢ ሪፖርቶች ወጥተዋል።

ጦርነቱን ተከትሎ በአማራ ከልል ስር የተጠቀለሉት የአካባቢው አስተዳደራዊ መዋቅሮች ሙሉ በሙሉ መፍረሳቸው የተነገረ ሲሆን፣ የአላማጣ ከተማ በመከላከያ ሠራዊት እና በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር ከሚያዝያ 7/2016 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ ተናግረው ነበር።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ግጭቱን ተከትሎ በሰጡት አስተያየት “የይገባኛል ጥያቄዎች” የሚነሳባቸውን አካባቢዎች በተመለከተ “በሕግ እና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከስምምነት ላይ የተደረሰበት በመሆኑ ለመርኅ ተገዢ መሆን ያስፈልጋል” ብለዋል።

መከላከያ የሰሞኑን ግጭት አስመልክቶ ያለው ነገር የለም።

ከሰሞኑ በተነሳው ግጭትም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ አራተኛ ዙር ወረራ በሕዝብ በላይ ፈጽሟል ሲል ከሷል።

የክልሉ መንግሥት ግጭቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫው “ከትናንት ታሪካዊ ስህተቱ መማር የተሳነው ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ ለአራተኛ ዙር ሕዝባችን ላይ ወረራ ፈፅሟል” ብሏል።

ክልሉ ይህንን ያለው ካለፈው ሳምንት ማብቂያ ጀምሮ በአላማጣ እና ራያ አካባቢዎች ለቀናት የዘለቀ የተኩስ ልውውጥ ከተካሄደ በኋላ በከተሞች አካባቢ የመከላከያ እና የፌደራል ፖሊስ በዙሪያቸው ደግሞ የትግራይ ኃይሎች ገብተዋል የሚሉ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ተከትሎ ነው።

ከሰሞኑ በራያ ወረዳዎች እና አላማጣ ከተማ እንደ አዲስ ከተቀሰቀሰው ግጭት ጋር ተያይዞ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 50 ሺህ መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ተፈናቃዮቹ የተጠለሉባቸውን የዞን ባለሥልጣናት ዋቢ አድርጎ ጽህፈት ቤቱ ሰኞ ሚያዝያ 14/2016 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት መሠረት ከተፈናቃዮቹ መካከል 42 ሺህ የሚሆኑ በሰሜን ወሎ በምትገኘው ቆቦ ከተማ እንዲሁም 8300 የሚሆኑት ደግሞ በሰቆጣ እና ዋግ ኽምራ ዞኖች ተጠልለዋል ብሏል።

የትግራይን ጦርነት ተከትሎ በአማራ ክልል ስል ተጠቃለው የተዋቀሩ አስተዳደሮች በፌደራል መንግሥቱ እንዲፈርሱ እንደሚደረግ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም ከዚህ ቀደም መግለጻቸው ይታወሳል።

ሚኒስትሩ ባለፈው ዓመት የአሸንዳ በዓልን ምክንያት በማድረግ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ላይ በትግርኛ ባሰፈሩት ሰፋ ያለ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት “በአካባቢዎቹ ቀደም ሲል የተፈጠረውን ሁኔታ በመጠቀም የተቋቋሙ አስተዳደሮች እንዲፈርሱ” እንደሚደረግ እና በአካባቢዎቹ ከፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ውጭ የታጠቀ ኃይል አንዳይኖር እንደሚደረግ አስፍረው ነበር።