የላስታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው መልሴ እና የወረዳው የጤና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚሊዮን አፈወርቅ

1 ግንቦት 2024, 12:47 EAT

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የምትገኘው ላስታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ እና የወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ በታጣቂዎች በተፈፀመባቸው ጥቃት መገደላቸውን ምንጮች እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ዋና ከተማው ላሊበላ የሆነው የላስታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ጌታቸው መልሴ እና የወረዳው የጤና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚሊዮን አፈወርቅ ጥቃት የተፈጸመባቸው ትናንት ማክሰኞ ሚያዝያ 22፤ 2016 ዓ.ም. እንደሆነ አራት ምንጮች ገልፀዋል።

ባለስልጣናቱ ተኩስ የተከፈተባቸው በሰሜን ወሎ ዞን ዋና ከተማ ወልዲያ የነበራቸውን ስብሰባ አጠናቅቀው እየተመለሱ በነበረበት ወቅት እንደሆነ መስማታቸውን ለወረዳው አስተዳደር ቅርበት ያላቸው አንድ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመው ከላሊበላ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ ከምትገኘው ኩልመስክ ከተማ አቅራቢያ መሆኑን የሚናገሩት ምንጩ፤ ሌሎችም የወረዳው እና የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች አብረው በጉዞ ላይ እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

ከሁለቱ ኃላፊዎች በተጨማሪ አንድ ሌላ ግለሰብ መገደላቸውን እና ሌሎችም መቁሰላቸውን ምንጩ ጠቅሰዋል። ሌሎች ሁለት ምንጮች በጥቃቱ ቢያንስ ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጥቃቱ ሲፈጸም አብረው የነበሩ ሌሎች የመንግስት ኃላፊዎች ወደ ላሊበላ ከተማ የሚያደርጉትን ጉዞ አቋርጠው ወደ ኋላ በመመለስ ኩልመስክ ከተማ ማደራቸውን ሁለት ምንጮች ገልጸዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በወረዳው መዋቅር ውስጥ በኃላፊነት የሚሰሩ ሌላ ግለሰብ በጥቃቱ ሁለቱ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ እና የጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ መገደላቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል። ዛሬ ጠዋት የወረዳው አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች በሚገኙበት ህንጻ ላይ የጤና ፅህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ሚሊዮን አፈወርቅ ህይወታቸው ማለፉን የሚገልጽ የሀዘን መግለጫ ተለጥፎ መመልከታቸውንም አክለዋል።

አንድ የላሊበላ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው፤ “ማታ [በዋና አስተዳዳሪው] መኖሪያ ቤት ሲለቀስ ነው ያመሸው። አሁንም የአካባቢው ነዋሪ ወደ ለቅሶ እየሄደ ነው” ሲሉ የዋና አስተዳዳሪው ሞት በላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች ዘንድ መሰማቱን ገልጸዋል።

የላስታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ጌታቸው የቀብር ስነ ስርዓታቸው የሚከናወነው ጥቃቱ ከተፈጸመበት አካባቢ በምትገኘው የትውልድ ከተማቸው ገነተ ማርያም እንደሆነ ሶስት ምንጮች ገልጸዋል።

የጤና ፅህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ሚሊዮን የቀብር ስነ ስርዓት በላሊበላ ከተማ እንደሚከናወን የጠቀሱት የወረዳው አስተዳደር ውስጥ የሚሰሩ ኃላፊ፤ አስከሬኑ ወደ ከተማዋ እስከሚመጣ እየተጠበቀ መሆኑን አስረድተዋል። ቢቢሲ ከቆይታ በኋላ ያነጋገራቸው አንድ የላሊበላ ከተማ ነዋሪ የአቶ ሚሊዮን አስከሬን ወደ ወደ ከተማዋ መግባቱን አረጋግጠዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት ምንጮች ጥቃቱ በማን እንደተፈጸመ ለመናገር እንደማይችሉ ገልጸዋል።

ለወረዳው አስተዳደር ቅርበት ያላቸው ምንጭ በበኩላቸው ዋና አስተዳዳሪው አቶ ጌታቸው ከዚህ ቀደም “ማስጠንቀቂያዎች“ ይደርሷቸው እንደነበር እና “የቤተሰብ አባል ታግቶባቸው” እንደነበር በመጥቀስ፤ ጥቃቱን የፈጸሙት “ፋኖ ናቸው” ብለዋል።

ቢቢሲ ከወረዳው አስተዳዳሪዎች እና የላሊበላ ከንቲባ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በተደጋጋሚ ቢሞክርም ምላሽ ማግኘት አልቻለም።