May 1, 2024 – Konjit Sitotaw

የሶማሌላንድ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኢሳ ካይድ፣ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የደረሰችበት የባሕር በር ስምምነት በኹለት ወራት ውስጥ በይፋ ይፈረማል ብለው እንደሚጠብቁ መናገራቸውን ዶይቸቨለ ዘግቧል።

ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ጣቢያነት ልታከራያቸው የምትችላቸው ሦስት አማራጭ ቦታዎች እንደተለዩ ሚንስትሩ መግለጣቸውን ዘገባው አመልክቷል።

ካይድ፣ የመግባቢያ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የኹለትዮሽ ውይይት ሲደረግ እንደቆየ ገልጸዋል ተብሏል።

ሚንስትር ካይድ፣ ስምምነቱ ሲፈረም ኢትዮጵያ ለሱማሌላንድ አገርነት እውቅና የምትሰጥበት ሕግ ወዲያውኑ መከተል አለበት ማለታቸውንም ዜና ምንጩ ጠቅሷል።

የመግባቢያ ሰነዱ ከአራት ወራት በፊት ሲፈረም፣ ባንድ ወር ጊዜ ውስጥ የመጨረሻው ስምምነት እንደሚፈረም ተገልጦ እንደነበር አይዘነጋም።