May 1, 2024 

ኢሰመጉ፣ መንግሥት በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎችና ታጣቂ ቡድኖች የሚፈጽሟቸውን “ግድያዎች”፣ “ሕገወጥ እስሮች” እና “ድብደባዎች” እንዲያስቆምና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለፍርድ እንዲያቀርብ አዲስ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።

የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ሚያዚያ 6 እና 7 በምሥራቅ ወለጋ ዞን ሰቡ ሲሬ ወረዳ 14 ነዋሪዎችን፣ ታጣቂዎች ደሞ በምዕራብ አርሲ ሽርቃ፣ ቃርሳ እና ኢተያ ወረዳዎች 5 ሰዎች መግደላቸውን ኢሰመጉ ገልጧል።

የፌደራሉና የክልል መንግሥታት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ “አፈናዎችን” እንዲያስቆሙና “የሰዎችን በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት” እንዲያስከብሩም ኢሰመጉ ጥሪ አድርጓል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድም፣ አማራ ክልል ውስጥ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማጣራት ወንጀለኞችን በሕግ እንዲጠየቁ ለመንግሥት የውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርብ ኢሰመጉ ጠይቋል።