May 1, 2024 

ኢትዮጵያ አሁን ከመፍረስ የመዳን እድሏ “ከ20/ከ30 በመቶ አይበልጥም”- ፖለቲከኛ ልደቱ አያሌው

 የፖለቲካዊ ኃይሎች የሚሳተፉበት ውይይት ሊያዘጋጁ ነው

ፖለቲከኛው ልደቱ አያሌው ‘የሃሳብ ገበታ” ከተባለ የዩ ትዩብ ገጽ ጋር ባደረጉት ቆይታ የአገሪቱ ከመፍረስ የመዳን ዕድል አሳሳቢ እየሆነ መሆኑን ተናግረዋል።

አንድ ፖለቲከኛ ወጥቶ ሃሳቤን ተቀበሉኝ ሲል እንደንቀት ሊቆጠር ቢችልም የአገሪቱ ሁኔታ ይህን ያስገድዳል በማለት መልዕክታቸውን የጀመሩት የቀድሞው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሊቀ መንበር ልደቱ አያሌው፤ “እስኪ ዛሬ ስሙኝ” በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

“ዛሬም ተቀባይነት እያገኙ፣ እየተደመጡ ያሉ ሰዎች ስህተቱን ደጋግመው የሰሩት ሰዎች ናቸው፤ ድሮ ቅንጅት ሆነው ትክክል ነን ሲሉ የነበሩት፣ አርበኞች ግንባር ሆነው ትክክል ነን ሲሉ የነበሩ ሰዎች፣ ኋላ ደግሞ የብልጽግና ደጋፊ ኢዜማ ሆነው ትክክል ነን ሲሉ የነበሩ ሰዎች አሁንም ፋኖ ሆነው ትክክል ነን እያሉ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

“አብዛኛውን ሚዲያዎች የተቆጣጠሩ ኃይሎች” የጥፋቱን መንገድ ደግመው ደጋግመው ሲያካሄዱ የነበሩ ናቸው ያሉት ፖለቲከኛው “የእነሱ ተደማጭነት ነው ያለው አሁንም፤ በዚህ ሁኔታ የትም ድረስ መሄድ አንችልም” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ከመፍረስና ከመዳን የትኛው እድሏ የሰፋ ነው ቢባል “የመፍረስ እድሏ ነው፤ 20/30 ፐርሰንት (በመቶ) የመዳን እድል የለንም” ያሉት ልደቱ አያሌው፤ “ምክንያቱም ሁላችንም ወደጥፋቱ አቅጣጫ ነው እየገፋን ያለነው። ከጥፋቱ ወደሚያወጣን አቅጣጫ የሚገፋ ኃይል የለም” ብለዋል።

ከጥፋት የሚያወጡ ኃይሎች ቢኖሩም እንዳሉ አይቆጠርም አልያም ተቀባይነትም አላገኙም ያሉት ልደቱ አያሌው፤ “ጦርነትና ብሔርተኛነት ነው ተቀባይነት ያለው፤ ችግሩ በተፈጠረበት መንገድ ደግሞ ችግሩ አይፈታም” ሲሉ አሳስበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፖለቲከኛው ልደቱ አያሌው በቅርብ ጊዜ ውስጥ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የውውይት መድረክ እንደሚያዘጋጁ መረጃዎች ተሰምተዋል።

ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት በፌደራል መንግሥት “በውጭ አገራት ሆነው ግጭት በመፍጠር የክልል እና የፌደራል መንግሥትን በኃይል ለመጣል ተንቀሳቅሰዋል” በሚል ተላልፈው እንዲሰጡት ማዘዣ ከወጣባቸው ፖለቲከኞች መካከል አንዱ የሆኑት ልደቱ አያሌው፤ በወቅቱ ክስ ከተመሠረተባቸው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ አስታውቀው ነበር።

ልደቱ አያሌው ለመገናኛ ብዙኀን ባሰራጩት መልዕክት 1ኛ. መቋጫው! የችግራችን ምንጭ፣ ያለንበት ሁኔታና የመዳኛው መንገድ፤ እንዲሁም 2ኛ. ምን ዓይነት የሽግግር ሂደት? ለምንና አንዴት? በሚሉ ርዕሶች ላይ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ማዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
———