May 1, 2024 

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሕይወት የመኖር እና የአካል ደህንነት መብቶች በመንግስት ኃይሎች ጭምር እየተጣሱ ነው- ኢሰመጉ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በአዲስ አበባ ከተማ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በሕይወት የመኖር እና የአካል ደህንነት መብቶች አደጋ ውስጥ መሆናቸውን አሳሰበ።

አዲስ ማለዳ ጉባዔው ትላንት ምሽት ካወጣው አስቸኳይ መግለጫ እንደተመለከተችው በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ሰቡ ሲሬ ወረዳ ሞቶ ቀበሌ ሚያዚያ 06 ቀን 2016 የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች 12 የአካባቢው ነዋሪዎች ተገድለዋል።

በምዕራብ አርሲ ዞን ደግሞ የታጠቁ ኃይሎች በሰዎች
ላይ ግድያ፣ እገታ እና የአካል ጉዳት መፈፀማቸውን እንደቀጠሉ ነው ሲል ኢሰመጉ አስታውቋል።

ኢሰመጉ “ስለጉዳዩ ከመንግስት አካላት ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረገው ጥረት ሊሳካ አልቻለም” ማለቱን አዲስ ማለዳ ከመግለጫው ተመልክታለች።

በአማራ ክልል ባለው ግጭት ሳቢያ በሰዎች ላይ የሚደርስ ግድያ፣ እገታ፣ የጅምላ እስር፣ የንብረት ውድመት፣ በየከተሞች ቦንብ ፍንዳታና የመንገዶች መዘጋት መቀጠሉ ተገልጿል።

የአካባቢው ማህበረሰብም ከቦታ ቦታ በነፃነት መንቀሳቀስ እንደማይችልና አሽከርካሪዎች ከእገታ ባለፈ በየቦታው የማለፊያ (የኮቴ) እየተባለ ክፍያ እንደሚከፍሉ የመብቶች ጉባዔው አመላክቷል።

የሕግ ባለሙያ አበራ ንጉሴ መጋቢት 20 ቀን 2016 በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ይህ ሪፖርት እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በአዋሽ አርባ በእስር ላይ እንደሚገኝ ኢሰመጉ የገለጸ ሲሆን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአባይ ህብር ብሔራዊ ፓርቲ አመራር የሆኑት ይታያል በላይ ከሁለት ወር በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ቢውሉም እስካሁን ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ታስረው እንደሚገኙ ገልጿል።

በራያ አላማጣ ወረዳ ከሚያዚያ 05 ቀን 2016 ጀምሮ በአካባቢው በተከሰተው ግጭት “ከፍተኛ” ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ወደ ቆቦ እና ሰቆጣ ከተማ የተፈናቀሉ ሲሆን በቂ የሰብዓዊ እርዳታ እና መጠለያ የሌለ ቢሆንም የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር ግን አሁንም ካለው በላይ ሊጨምር እንደሚችል ኢሰመጉ በመግለጫው ማሳሰቡን አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።

ኢሰመጉ በመንግስት ኃይሎች እና በታጠቁ አካላት የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ድርጊቶች በአስቸኳይ እንዲታረሙ እና ፍትህ እንዲሰፍን ጥሪ አቅርቧል።