May 1, 2024 

” የትግራይ ደቡባዊ ዞንና ፀለምት እስከ ግንቦት 30 ፤ የምዕራብ ትግራይ ጉዳይ ደግሞ እስከ ሰኔ 30 እንዲተገበርና እነዲፈፀም ስምምነት ተደርሶ ወደ ተግባር ተገብቷል ” – ሌ/ጀነራል ታደሰ ወረደ

የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕረዜዳንት ጀነራል ታደሰ ወረደ (ወዲ ወረደ) ዛሬ በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተው ነበር።

በመግለጫቸው ፥ ” በፕሪቶሪያ ውል አተገባበር ላይ መሰረት ያደረገ ከአገር መከላከያ ሰራዊትና ከፌደራል መንግስት ጋር የሁለት ቀን ውይይት በማድረግ የአፈፃፀም ስምምነት ላይ ተደርሷል ” ብለዋል።

” በውይይቱ የማጠቃለያ ስምምነት መሰረት የትግራይ ደቡባዊ ዞንና ፀለምት እስከ ግንቦት 30/2016 ዓ.ም ፤ የምዕራብ ትግራይ ጉዳይ ደግሞ እስከ ሰኔ 30/2016 ዓ.ም  እንዲተገበርና እንዲፈፀም ስምምነት ተደርሷል ” ሲሉ ተናግረዋል።

” ትጥቅ ማን ይፈታል ? ፣ እንዴት ይፈታል ? የትኞቹ አስተዳደሮችስ ይፈርሳሉ ? እንዴት ያሉ ተፈናቃዮች ይመለሳሉ ? በሚሉ ነጥቦች ውይይት ተካሂዶ ዝርዝር እቅድ ወጥቶሎታል ” ሲሉ ገልጸዋል።

የእቅዱ አፈፃፀም በአፍሪካ ህብረት የክትትልና ቁጥጥር ቡድን እንዲመራና እንዲተገበር ስምምነት ላይ መደረሱን አመልክተዋል።

” በትግራይ አመራር መካከል በፕሪቶሪያ የውል ስምምነት አፈፃፀም ዙሪያ ‘ ሰላም ፈላጊና ጦርነት ፈላጊ አለ ‘ በሚል እየተፈጠረ ያለው ትርክት ስህተት ነው ” ያሉት ጄነራሉ ” ትርክቱ ስህተት መሆኑን ለፌደራል መንግስት ገለፃ ሰጥተናል ” ብለዋል።

በትግራይ በኩል የፕሪቶሪያ ውል ለመተግበር እስከ ታች የአስተዳደር መዋቅር ድረስ መግባባት ተደርሶ ወደ ትግበራ ለመግባት የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች ተመቻችቷል ሲሉ አሳውቀዋል።

” የፌደራል መንግስትም የስምምነቱ ትግበራ እስከ ታች ድረስ እንዲያወርደው እንጠብቃለን ” ብለዋል።

” የፕሪቶሪያው ውል ስምምነቱ ከተፈፀመበት ቀን ጀምሮ ከማንኛውም አይነት ግጭት በፀዳ መልኩ ተፈፃሚ ይሆናል ተብሎ ባይጠበቅም ፤ አሁን መሬት ላይ ካለው ሁኔታ በመነሳት እንዳችም ለግጭት የሚጋብዝ ሁኔታ የለም  ” ሲሉ ገልጸዋል።