May 1, 2024 – Konjit Sitotaw

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ሲያወያዩ ከሠራተኛው ጋር አለመወያየታቸው አሳሳቢ ነው ተባለ

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሚጠበቅበትን እያደረገ አይደለም

የሠራተኞች ቀን በዓል ላይ ታዳሚ የሆኑ ሠራተኞች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመላው አገሪቱ በየደረጃው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ጋር በመገናኘት ስላሉ ችግሮች ሲወያዩና መፍትሔ ሲፈልጉ የሚታይ ቢሆንም ከሠራተኛው ክፍል ጋር ውይይት አለማድረጋቸው እንዳሳሰባቸው ገለጹ።

ስለሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሠራተኛው ጋር ውይይት እንዲያደርጉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

ሠራተኞቹ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ለመወያየት ጥያቄያቸውን ያቀረቡት  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) በዛሬው ዕለት ሚያዝያ 23 ቀን 2016 በኦሮሞ ባህል ማዕከል በተዘጋጀው ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ቀን መድረክ ላይ ነው።

በዓሉ በዓለም ለ135 ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ49ኛ ጊዜ እየተከበረ ሲሆን ለሠላምና ለኑሮ ውድነት መፍትሔ ይሰጥ፣ ግጭቶች በውይይት ይፈቱ፣ ከደመወዝ የሚቆረጠው የገቢ ግብር ምጣኔ ይቀነስ፣ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ይወሰን የሚሉ ዋነኛ ጥያቄዎች በመድረኩ ላይ ተነስተዋል።

የዘንድሮዉ አከባበር ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው በአደባባይ የማይከበር ሲሆን “የአገሪቱን አጠቃላይ ሁኔታ በማገናዘብ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ያሉ ከባቢዎችንም ከግምት በመክተት እንደ ባሕር ዳር፣ ኮምቦልቻና ፊንፊኔ ዙሪያ ካሉት ውጪ” በአዳራሽ ውስጥ ለማክበር መወሰኑን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወቃል።

ባለፈው ዓመት 48ኛው የሠራተኞች ቀን በዓልን ኢሠማኮ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እንዲሁም በክልሎች በሰላማዊ ሰልፍ ለማክበር ቢያቅድም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጸጥታ ቢሮ መከልከሉ አይዘነጋም።

በበዓሉ ላይ በነበረው የውይይት መርሀ ግብር ከተለያዩ ተቋማት የመጡ እነዚሁ ሠራተኞች እንዳነሱት የኢትዮጵያ ሠራተኞች በአገሪቱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እና  በታማኝነት ግብሩን የሚከፍል ቢሆንም፤ እውቅና እንኳን ለማግኘት ያልቻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኑሮ ውድነትና ሌሎች ችግሮች እየተሰቃየ የሚገኘውን ሠራተኛ ችግሩን በቅርበት ለማወቅና ለማነጋገር እንኳን መድረክ ያልተመቻቸ መሆኑን የገለፁት ሠራተኞቹ፤ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሚጠበቅበትን ድርሻ እየተወጣ እንዳልሆነ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ሠራተኞች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ሁሉ አገራቸውን በማስቀደም ተቋቁመው እና ቅድሚያ ለአገራቸው ሰጥተው የሚገኙ ቢሆንም እነሱን ቀርቦ ያሉባቸውን ችግሮች ለመረዳትና ለማነጋገር ግን መድረክ ሊመቻች እንዳልተቻለ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህ በዓል የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሎ፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈርያት ካሚል፣ የሁለቱ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽንና ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም የዓለም ሥራ ድርጅት ተወካይ ተገኝተዋል።

የላብ አደሮች ወይም የሰራተኞች ቀን በሰራተኞች ላይ የሚደርስን የስራ ጫና ለመቀነስ የሚደረግን ትግል ለማሰብ ነበር በጎርጎሮሳውያኑ ከ1889 ጀምሮ መከበር የጀመረው።

የዓለም ሰራተኞች ቀን በፈረንጆቹ ግንቦት አንድ እንዲከበር ውሳኔ ላይ የተደረሰው በዓለም አቀፍ የሶሻሊስት ቡድን እና በሰራተኞች ማህበራት ውሳኔ ሲሆን በ1886 በችካጎ የተቀሰቀሰው የሄይማርኬት የሰራተኞች የመብት ጥያቄ አድማን ለማስታወስ በማሰብ ነው፡፡

የሄይማርኬት አድማ ግንቦት 1886 በችካጎ ከተማ መቀስቀሱን ተከትሎ በዕለቱ ከ400 ሺሕ በላይ ሰራተኞች የስምንት ሰዓት የስራ ጊዜ በመጠየቅ የስራ ማቆም አድማ በመምታት ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸው እና ሰዎች መገደላቸውን መዛግብት ያነሳሉ፡፡

በግጭቱ ወቅት በፖሊስ ላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ ሰባት ሰራተኞች ተይዘው ስድስቱ የሞት ፍርድ ሲፈረድባቸው አንዱ በ15 ዓመት እስራት ተቀጥቷል፡፡ ውሳኔው ግን ኢፍትሃዊ ነው በሚል ብዙ ሰራተኛ ቅር አሰኝቷል፡፡

ሁነቱም በታሪክ የሄይማርኬት ክስተት ወይም ጉዳይ (Haymarket Affair) ተብሎ ይታወሳል፡፡

የኢሰማኮ ጠቅላይ ምክር ቤት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ለመገናኘት የሚጠይቅ ደብዳቤ መጻፉንና ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑ ይታወቃል።