ተመስገን ተጋፋው

May 1, 2024

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሊዝ ፋይናንስ የብድር ሥርዓቱ አማካይነት 8.7 ቢሊዮን ብር ብድር ለግብርና ዘርፍ ብቻ ለማቅረብ በሒደት ላይ መሆኑን አስታወቀ።

ባንኩ የሊዝ ፋይናንስ የብድር ሥርዓትን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው አጠቃላይ ብድር 14.5 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቋል።

ከዚህ ብድር ውስጥ 20 በመቶው የሚሆነው ወይም 2.9 ቢሊዮን ብሩ ለግብርና ዘርፍ የቀረበ መሆኑን ያስታወቁት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ፋይናንስ፣ ፋይናንሲንግ ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው አበራ፣ በዚህም የብድሩ ተጠቃሚ የሆኑ የባንኩ ደንበኞች፣ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችን በሊዝ ፋይናንስ የብድር ሥርዓት አግኝተው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት ባንኩ በሊዝ ፋይናንስ የብድር ሥርዓት ለግብርናው ዘርፍ ካቀረበው 2.9 ቢሊዮን ብር በሦስት እጥፍ የሚበልጥ ወይም 8.7 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ለማቅረብ በዝግጅት ሒደት ላይ እንደሚገኝ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

ባንኩ ከዚህ ቀደም የነበረበትን የብድር አመላለስ ችግር በማጥናት የፖሊሲ ማሻሻያ አድርጎ፣ ጥራት ያለው ብድር ለግብርናው ዘርፍ እያቀረበ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ የሊዝ ፋይናንስ የብድር አገልግሎት ማቅረብ ከጀመረበት ወቅት አንስቶ እስካሁን ድረስ ካቀረበው አጠቃላይ 14.5 ቢሊዮን ብር ውስጥ፣ የተበላሸ ብድር ምጣኔው ከሁለት በመቶ በታች መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ የተበላሸ ብድር ምጣኔ የሊዝ ፋይናንስ የብድር አገልግሎትን የሚመለከት ሲሆን፣ የባንኩ አጠቃላይ የተበላሸ ብድር ምጣኔም በአሁኑ ወቅት ወደ 7.8 በመቶ ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል።

ባንኩ የተበላሹ ብድሮችን ለማስመለስ ጠንካራ ዕርምጃ እየወሰደ መሆኑን የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ የተበላሸ ብድር ያለባቸውን ደንበኛ እንዲሁም ጥለው የሸሹትን በሕግ የተደገፈ አሠራርን በመከተል ለማስመለስ እየተሠራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

እነኚህ የተበላሸ ውዝፍ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች አንድ በአንድ የማጥራትና የማፅዳት ትግበራ እየተደረገ ሲሆን፣ የነበረባቸውን ዕዳ ለመክፈል ዝግጁ የሆኑ ባለሀብቶችን በማበረታታት ወደ ጤናማ አሠራር እንዲገቡ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡