ፅዮን ታደሰ

May 1, 2024

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱ ባቀረበበት ወቅት

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ ከተያዘለት በጀት በዘጠኝ ወራት ውስጥ 5.4 ቢሊዮን ብር ቢጠቀምም ከ27 ፕሮጀክቶች አሥሮቹ አፈጻጸማቸው ዜሮ ሆኖ መመዝገቡና ያጠናቀቀው አንድም ፕሮጀክት አለመኖሩ ተገለጸ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዚያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. 23ኛ መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን አቅርቧል፡፡ የውኃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የሚኒስቴሩን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት መነሻ በማድረግ ባቀረበው ጥያቄ፣ ሚኒስቴሩ የበጀት ዓመቱ ሲጀመር ተይዞለት ከነበረው 7.8 ቢሊዮን ብር በዘጠኝ ወራት ውስጥ 5.4 ቢሊዮን ብር ወጪ አድርጎ ሥራ ላይ ማዋሉን ገልጾ፣ ካከናወናቸው 27 ፕሮጀክቶች ጥራትና ዲዛይን ሥራ የመከታተልና ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ የአሥር ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ዜሮ መሆኑን አመላክቷል፡፡

በተጨማሪም ባለፈው ዓመት ከተጠናቀቁ ሦስት ፕሮጀክቶች ውጭ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት አንድም ፕሮጀክት በዕቅዱ መሠረት ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ አለመኖሩን ገልጿል፡፡ በዚህም ከሁሉም ፕሮጀክቶች 29 ሥራዎች አፈጻጸማቸው ዜሮ በመቶ፣ 17 ሥራዎች ደግሞ ከ50 በመቶ በታች ሆነው እያለ 5.4 ቢሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙ በቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ አስነስቷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በክልሎች መካከል ያለው የአፈጻጸም ግምገማ ሰፊ ልዩነት ማሳየቱ የሚኒስቴሩን ድጋፍና ክትትል መላላት የሚያሳይ ነው ሲል የገለጸ ሲሆን፣ በደቡብ ክልል ውስጥ ሲከናወኑ የነበሩ ፕሮጀክቶች በክልሉ እንደ አዲስ መደራጀት ምክንያት ፕሮጀክቶቹ ተጓተዋል በሚል በምክንያትነት የተቀመጠው ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ፣ የሚኒስቴሩ ድጋፍና ክትትልን መላላት የሚያሳይ ነው በማለት አስቀምጧል፡፡

የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ያቀረቡት የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር)፣ አሥራ ሰባት ፕሮጀክቶች የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታ አማካይ አፈጻጸም ከ80 እስከ 85 በመቶ መሆኑንና በፀጥታ ችግሮች ምክንያት በዕቅዱ ያልተሠሩ ወይም ሙሉ በሙሉ የቆሙ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትሯ ከቋሚ ኮሚቴው ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ በዚህም የፕሮጀክቶች ጥራትና ዲዛይን አፈጻጸም ዝቅተኛ ሆኖ ለመመዝገቡና ለእያንዳንዱ ፕሮጀክት የተለያየ ምክንያት ቢኖርም፣ የፀጥታ ችግሩ ግን ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በየደረጃው ያሉ የማስፈጸም አቅም ውስንነት፣ የወሰን ማስከበርና የካሳ ክፍያ ላይ ያሉ ችግሮች እንዲሁም የዋጋ መናር እንደ ችግር አስቀምጠዋል፡፡ 

ሚኒስቴሩ አንድም ያጠናቀቀው ፕሮጀክት ሳይኖር በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከተያዘለት በጀት 99.7 በመቶውን መጠቀሙን አስመልክቶ ላልተሠሩ ሥራዎችም ክፍያዎችን ፈጽሟል በሚል ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አይሻ (ኢንጂነር)፣ ሚኒስቴሩ ላልተሠሩ ሥራዎች ምንም ዓይነት ክፍያ አለመፈጸሙን አብራርተው ‹‹ከፕሮጀክት አፈጻጸሙ ጋር በቀጥታ ለማገናኘት ያለው ሁኔታ አይፈቅድም፤›› ብለዋል፡፡ 

መሬት ላይ የሚሠራው ሥራና በጀቱ እኩል እየሄደ ያልሆነበትን ምክንያት ሲያስረዱም ‹‹ሚኒስቴሩ እየከፈለ ያለው ክፍያ ዓምና ለተሠሩ ፕሮጀክቶች ጭምር መሆኑ፣ የዋጋ ንረቱ እየጨመረ በመሄዱ በሚደረግ የዋጋ ማስተካከያ እንዲሁም በእጃችን ያለው የ100 ቢሊዮን ብር ኮንትራት ሆኖ፣ የሚሰጠው ከአሥር ቢሊዮን ያነሰ በጀት ሲሆን፣ የተሠራው ሥራና የሚከፈለው ክፍያ እኩል አይሆንም›› በማለት ገልጸዋል፡፡ ካስፈለገም የወጪዎቹን ሰነዶች ድጋሚ መመልከት ይቻላል ብለዋል፡፡ 

በመጨረሻም የውኃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ወ/ሮ ፈትያ አህመድ፣ ሚኒስቴሩ በቋሚ ኮሚቴው የሚሰጡ አስተያየቶችን እየተቀበለ አለመሆኑን ገልጸው፣ የበጀት አጠቃቀሙ ለሙስና ተጋላጭ እየሆነ ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ዕቅድና ሪፖርቱ መሬት ላይ ካለው ሁኔታ አንፃር አለመናበብ መኖሩን ጠቁመው፣ የተሰጡ አስተያየቶችን ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡