ሳሙኤል ቦጋለ

May 1, 2024

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብዱረህማን ዒድ

በሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ላይ የተወሰ ድርሻቸውን ለሕዝብ የሚሸጡ ስድስት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መለየታቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ (Ethiopian Investment Holdings – EIH) ኃላፊዎች ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን መጀመር አስመልክቶ የተወሰኑ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች (State Owned Enterprises) ውስን ድርሻዎቻቸውን በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ላይ እንደሚሸጡ ሲገለጽ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት በፊት ይፋ እንደሆነውም መንግሥት የኢትዮ ቴሌኮምን አሥር በመቶ ድርሻ ለሕዝብ እንደሚሸጥ ገልጾ ነበር፡፡ ምን ያህል መጠናቸው እንደሆነ ውሳኔ ላይ ባይደረስም ሌሎች አምስት የልማት ድርጅቶች ድርሻዎቻቸው በገበያው ላይ እንዲሸጡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ መወሰኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ አብዱረህማን ዒድ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ድርሻቸው ለሽያጭ የሚቀርበው የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት (አባትሎአድ)፣ የኢትዮጵያ መድኅን ድርጅት፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፣ የትምህርት ማምረቻና ማሠራጫ ድርጅትና የኢትዮጵያ የቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ሲሆኑ፣ አምስቱ ተጨማሪ የልማት ድርጅቶች፣ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመሆን ስድስት ድርጅቶች ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ላይ ድርሻቸውን ይሸጣሉ፡፡

ከትምህርት ማምረቻና ማሠራጫ ድርጅትና ከኢትዮጵያ የቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ውጭ ያሉት አራቱ የልማት ድርጅቶች፣ በበላይ ከሚቆጣጠራቸው ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጋር አምስት በመሆን የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያን (Ethiopian Securities Exchanges – ESX) 25 በመቶ ድርሻ በመግዛት ገበያውን በዚህ ዓመት መስከረም ወር ላይ ማቋቋማቸው የሚታወስ ነው፡፡

እንደ አቶ አብዱረህማን ገለጻ፣ እነዚህን አራቱ ድርጅቶች የገበያውን አክሲዮን ገዝተው እንዲያቋቁሙ የተመረጡበት ምክንያትም በገበያው ላይ በኋላ ድርሻቸውን እንዲሸጡ በመወሰኑ ነው፡፡ በኋላ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአራቱ የልማት ድርጅቶችና ከሆልዲንጉ ጋር በመግባት ስድስተኛ ተቋም ሆኖ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይን 25 በመቶ ድርሻ በጋራ መግዛቱ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድርሻቸውን እንደ ኢትዮ ቴሌኮምና ሌሎቹ የልማት ድርጅቶች ለሕዝብ እንዲሸጥ አለመወሰኑን አቶ አብዱረህማን ተናግረዋል፡፡

‹‹የንግድ ባንክ አሁን አይሆንም፡፡ ምናልባት ወደፊት ከሆነ እንጂ አሁን አልተወሰነም፤›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ‹‹ኢትዮ ቴሌኮም በጣም ግዙፍ ድርጅት ነው፣ የእሱን ድርሻ በተወሰነ መጠን ከሸጥን የንግድ ባንክ አለመሸጥ ምንም አይደል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መድኅን ድርጅትም ግዙፍ መሆኑንና ከ50 በመቶ በላይ የመድኅን ገበያውን የሚቆጣጠር መሆኑን፣ ኢባትሎአድም በጣም ትልቅ ድርጅት እንደሆነ፣ እንዲሁም ብርሃንና ሰላም በአገሪቱ ትልቁ የኅትመት ድርጅት እንደሆነ ያስታወሱት አቶ አብዱረህማን፣ የእነዚህ ድርጅቶች በገበያው ላይ መቅረብ ትልቅ ነገር እንደሆነ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

ድርጅቶቹ ምን ያህል የድርሻ መጠናቸውን ለሕዝብ እንደሚያቀርቡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ሥራ አስፈጻሚው፣ ‹‹የኢትዮ ቴሌኮም አሥር በመቶ እንደሆነ ይታወቃል፣ ነገር ግን ሌሎቹ ምን ያህል መጠናቸውን እንደሆነ የሚሸጡት ገና አልወሰንም፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በውጭ አጋሮቹ ድጋፍ በቅርብ የድርጅቱን ዝግጁነት እያስጠና ሲሆን፣ በገበያው ላይ ለመሸጥ በጣም ጥብቅ የሆኑ መሟላት ያለባቸውን መሥፈርቶች ማሟላት ያለባቸው እንዳሉ ተገልጿል፡፡

የልማት ድርጅቶቹ በገበያው ለመቅረብ ምን መቀየር እንዳለባቸው ሐሳቡ ያላቸው መሆኑን፣ በዚህ ሳምንትም ጨምሮ በየጊዜው ጥልቅ ውይይት እንደሚያደርጉ አቶ አብዱረህማን ተናግረዋል፡፡

ሆልዲንጉ በካፒታል ገበያ ላይ ትኩረ አድርጎ የሚሠራ ልዩ ቡድን የሚያቋቁም ሲሆን፣ ቡድኑ የልማት ድርጅቶቹን ለገበያ ለማቅረብ እንዲዘጋጁ የሚያግዛቸው ይሆናል፡፡