ፖለቲካ

ሲሳይ ሳህሉ

May 1, 2024

በኢትዮጵያ የሠራተኞች ማኅበር ምሥረታ ታሪክ እ.ኤ.አ በ1945 አካባቢ የቀድሞው ፍራንኮ ኢትዮጵያ ምድር ባቡር ድርጅት ላይ ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞች የመሠረቱት የመጀመሪው ተጠቃሽ ማኅበር ሲሆን፣ የኢንዶ ኢትዮጵያን ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ የወንጂ ሰኳር ፋብሪካ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ አንበሳ ባስ ድርጅትና መሰል ድርጅቶች ቀጥለው ማኅበር የመሠረቱ ተቋማት ስለመሆናቸው መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

ስለመደራጀት መብት በሚያብራራው በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 31 መሠረት፣ ማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ በማኅበር የመደራጀት መብት እንዳለው በግልጽ ተቀምጧል፡፡  በ2011 ዓ.ም. በወጣው የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ አንቀጽ 113 ደግሞ ሠራተኞችና አሠሪዎች እንደ የአግባቡ የሠራተኞች ወይም የአሠሪዎች ማኅበር  ለማቋቋምና ለመደራጀት የማኅበር አባል ለመሆን እንዲሁም በማኅበር ለመሳተፍ መብት እንዳላቸው ያብራራል፡፡

በዚህ አዋጅ እንደተደነገገው በአንድነት ሆነው የሚያቋቁሙት ማኅበር አሥር ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ሠራተኞች ሲሆኑ፣ ሠራተኞች በሚገኙበት ድርጅት ውስጥ የተቋቋመው የሠራተኛ ማኅበር ደግሞ በአንድ ላይ በመሆን የአሠሪዎች ማኅበራት ፌደሬሽን፣ አንድ ላይ በመሆን ደግሞ የሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን ሊመሠርቱ እንደሚችሉ ተቀምጧል፡፡

በአዋጁ እንደተብራራው የማኅበራት ዋነኛ ዓላማ የአባሎቻቸውን መብትና ጥቅም ማስከበርና ማስጠበቅ ሲሆን፣ ፌዴሬሽኖችና ኮንፌዴሬሽኖች ደግሞ በሙያ ወይም በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሥራ ሁኔታዎችን ለማሻሻልና ለመወሰን በሚደረጉ ጥረቶች መሳተፍ፣ አባሎቻቸው በአገሪቱ ኢኮኖሚ ግንባታ ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ማድረግ፣ በማንኛውም ስብሳባ ላይ አባሎቻቸውን መወከልንና የመሳሰሉ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ተፈቅዷል፡፡

የሕጉን ተፈጻሚነት በሚያብራራው አዋጅ አንቀጽ ሦስት መሠረት በልዩ ሕግ የሚተዳደሩ እንደ የጦር ኃይል ባልደረቦች፣ የመንግሥት አስተዳድር ሠራተኞች፣ የፍርድ ቤት ዳኞችና ዓቃቢያነ ሕግ ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን ተመላክቷል፡፡ ይህ ማለት በዚህ አዋጅ መሠረት መደራጀት የሚችሉት በግልና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩት ሠራተኞች ብቻ ናቸው፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ  የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ ባለፈው ዓመት ከአንድ የአገር ውስጥ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ዳኞች፣ ዓቃቢያነ ሕጎች፣ ዳኞች በሠራተኛ ማኅበር ውስጥ እንደማይደራጁ መደንገጉን ጠቅሰው፣ በአፍሪካ አኅጉር ሦስት አገሮች ማለትም ኤርትራ፣ ጂቡቲና ኢትዮጵያ ብቻ የዚህ ዓይነቱ የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበር ምሥረታ በማይታወቅ ምክንያት መከልከሉን አስረድተዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ የመንግሥት አካላትና ተቋማት ማብራሪያ ሲጠየቁ የሚሰጡት መልስ የመንግሥት ሠራተኛ ከተደራጀ እናንተ መንግሥት ትሆናላቸሁ የሚል መልስ እንደሚሰጣቸው የሚናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ በኢትዮጵያ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ፣ የመንግሥት ሠራተኞች የመደራጀት መብት ስለሌላቸውና የማኅበሩ አባል መሆን ስለማይችሉ፣ ሠራተኞቹ ስለሚደርስባቸው የመብት ጥሰት መከራከርም ሆነ መታገል አልቻልንም ይላሉ፡፡ ነገር ግን በሌሎች አገሮችም ሠራተኞች ተደራጅተው መብታቸውን እንደሚጠይቁ እናውቃለን ብለዋል፡፡

‹‹የሕግ የበላይነት መከበር አለበት›› የሚሉት አቶ ካሳሁን፣ የሕግ ማሻሻያ ተደርጎ የመንግሥት ሠራተኞች እንዲደራጁ መፈቀድ አለበት እንጂ በመንግሥት መልካም ፈቃድ ላይ የተመረኮዘ ተግባር መሆን እንደሌለበት ያስረዳሉ፡፡

ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍ የሠራተኞች የመደራጀት መብትን የሚመለከቱ ኮንቬንሽኖች ተፈጻሚ አለማድረጓን በመጥቀስ፣ በዚህ ጉዳይ አገሪቱ በዓለም የሥራ ድርጅት በተደጋጋሚ እየተከሰሰች ቢሆንም፣ እስካሁን መልስ አላገኘም የሚለው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን፣ አገሪቱ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጇን እንድታሻሽል በየጊዜው መንግሥትን እየጠየቀ መሆኑ ሲናገር ይደመጣል፡፡

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ምዕራፍ ሦስት ላይ የተደነገጉ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች፣ አገሪቱ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ  የሰብዓዊ መብት፣ ሕግጋት ስምምነቶችና ሰነዶች ጋር እኩል የአገሪቱ ሕግ አካል ሆነው እንደሚቆጠሩ ይደነግጋል፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተዘረዘሩት መብቶች የአሠሪዎች መብት፣ የአካል ደኅንነት መብት፣ የነፃነት መብት፣ ኢሰብዓዊ አያያዝ ስለመከልከሉ፣ የተከሰሱ ሰዎች መብት፣ የክብርና የመልካ ስም መብት፣ የእኩልነት መብት፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት፣ የመደራጀት መብትና ሌሎችንም መብቶች አካቶ ይዟል፡፡ በተመሳሳይ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው አህመድ፣ ኢትዮጵያ መሠረታዊ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ከሚባሉትና ከፈረመቻቸው አሥር ስምምነቶች መካከል የመደራጀትና የመደራደር ጉዳይ ሁለቱ ቁልፍ መብቶች ስለመሆናቸው ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም ሠራተኛ የልማት ተቋም፣ የግል ተቋምና የመንግሥት ተቋም ተብሎ ሊከፋፈል እንደማይገባ ገልጸው፣ በሕገ መንግሥቱም ይሁን በዓለም አቀፍ ድንጋጌ መሠረት የመንግሥት ሠራተኞች ከዚህ መብት ሊገለሉ አይገባም ብለዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ዘጠኝ መሠረት ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ የሕግ አካል ናቸው ተብሎ መደንገጉን የሚናገሩት አቶ አያሌው፣ የመንግሥት ሠራተኛ በአሠሪና ሠራተኛ ሕጉም በመንግሥት ሠራተኞች የመደራጀትና የመደራደር ነፃነታቸው መከበር እንዳለበት ተግረዋል፡፡

የመንግሥት ሠራተኞች ቢደራጁ የሚደርስባቸውን ችግር በተወካዮቻቸው አማካይነት ማቅረብ ያለባቸው ቢሆንም፣ አሁን ግን ሠራተኛው የሚደርስበትን የመብት ጥሰትም ይሁን ሌላ ቅሬታ የሚያደርስበት አደረጃጀት የለም፡፡ በዚህም አንድ ሠራተኛ ከሠራተኛም አለመግባባት ቢፈጠር በተዋረድ ባሉ አመራሮች በደል ቢደርስበት ሚኒስትሩ ጋር ወይም መንግሥት ጋር አቤቱታና ቅሬታ ማቅረብ እንደማይችሉ ያስረዳሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ዘርፉ በትክክለኛ አደረጃጀት በአሠሪና ሠራተኛ መካከል ድርድር እየተከናወነ አለመሆኑን የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ሠራተኛው መብቱ እየተጠበቀለት ባለመሆኑ ጉዳዩ መፍትሔ እስከሚያገኝ ድረስ መንግሥት ላይ ግፊትና ጫና ማሳደሩን አናቆምም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሠራተኞች መብት ተሟጋች ድርጅት በመባል የሚታወቀውና በሠራተኞችና አሠሪዎች መካከል ያለውን ያልተመጣጠነ አቅም በመረዳት ሠራተኞች የሚደርስባቸውን ጫና በተለይም ከአሠሪ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ወደ ክስ በሚሄዱበት ወቅት፣ ሠራተኞች ከኩባንያ ጠበቃ ጋር የሚያደርጉት ክርክር ላይ ሙያዊ ዕገዛ በማድረግ እንዲሁም የሠራተኞችን አቅም የሚያጠነክር ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት በመስጠት የሚሠራ አገር በቀል ድርጅት ነው፡፡

በተመሳሳይ ድርጅቱ ለሠራተኞች መብት የተሻለ ጥበቃ የሚሰጡ ሕጎች እንዲወጡ ግፊት ማድረግ፣ አገሪቱ ለፈረመቻቸው ስምምነቶች ማስፈጸሚያ ሕጎች እንዲወጡ መጎትጎት፣ አገሪቱ ያልፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍ ሕጎች ደግሞ እንድትፈርም ግፊት የሚያደርግ ሥራ እንደሚሠራ የኢትዮጵያ የድርጅቱ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ቁምላቸው ዳኜ ለሪፖተር ይገልጻሉ፡፡ ይህ የመብት ተሟጋች ድርጅት ሠራተኞችን የሚመለከቱ ሕጎችን የማርቀቅ ሥራ እንደሚሠራ የጠቆሙት አቶ ቁምላቸው፣  አሁን ላይ የቤት ሠራተኞችን አጠቃላይ አስተዳድር በተመለከተ ሊገዛ የሚችል ሞዴል ረቂቅ ሕግ በማውጣት የመንግሥት አካላትን በማማከር የቤት ሠራተኞችን የተመለከተ ሕግ እንዲወጣ ግፊት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመደራጀት መብት በሕገ መንግሥቱ ከመረጋገጡ ባለፈ፣ ኢትዮጵያ አባል በሆነችበትና በዚሁ ተቋም ተዘጋጅቶ አገሪቱ በፈረመችው የዓለም አቀፉ የሠራተኞች ኮንቬንሽን መሠረት የሠራተኞች መብትን ተግባራዊ የሚያደርግ ሕግ ማውጣት እንዳለባቸው ግዴታ እንደሚጥል አቶ ደጀኔ ይገልጻሉ፡፡ በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ሕግም ይሁን በዓለም አቀፍ ሕግ ግዴታ አለባት ይላሉ፡፡

በተመሳሳይ በዓለም አቀፉ የሶሻል፣ ኢኮኖሚና የባህል መብቶች ኮንቬንሽን እንዲሁም በዓለም አቀፉ ሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ኮንቬንሽን የሠራተኞች የመደራጀት መብት በግልጽ መቀመጡ እየታወቀ፣ የመንግሥት ሠራተኞች የሚደረጁበት ሁኔታ አለመፈጠሩ የሕግ ጥሰት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በሥራ ላይ ያለው የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ምናልባት የግል ሠራተኞችን የሚመለከት ሕግ በመሆኑ፣ በዚህ አዋጅ ውስጥ የመንግሥት ሠራተኞችን የተመለከተ ድንጋጌ ማስገባት ባይቻልም እንኳን በመንግሥት ሠራተኞች አስተዳዳር አዋጅ ውስጥ ይህን መብት ማካተት እንደሚቻል ያነሳሉ፡፡

እንደ አቶ ቁምላቸው ማብራሪያ ይህ አለመደረጉ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎችን የሚጋጭና የመንግሥት ሠራተኞች የራሳቸውን ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን የሚፃረር ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ዜጎች ያላቸውን ሕገ መንግሥታዊ መብት ባለማስጠበቁ፣ ዓለም አቀፍ ሕጎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የሕግ አሠራር ባለማውጣቱ ረገድ የመንግሥት ሥራ  ጎደሎ ነው ማለት ነው ይላሉ፡፡

በተመሳሳይ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው ወይም Equality better the law principle በሚለው የሕገ መንግሥቱ መርህ መሠረት የግል ሠራተኞች የመደራጀት መብት ተጠብቆ፣ የመንግሥት ሠራተኞች እንዳይደራጁ ማድረጉ በግልጽ ይህን በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን አንቀጽ የሚፃረር አድሏዊ የሆነ አሠራር ስለመሆኑ አክለው ይናገራሉ፡፡

በአማራ ክልል ከሚሴ ዞን በሚገኝ አንድ የመንግሥት ጤና ጣቢያ ውስጥ በሕክምና ሙያ ውስጥ ይሠሩ የነበሩት አቶ ትዕዛዙ በለጠ፣ የመደራጀት መብት ባለማግኘታቸው የደረሰባቸውን መንግሥታዊ በደል ለሪፖርተር ያስረዳሉ፡፡

አቶ ትዕዛዙ ይሠሩበት በነበረው የጤና ተቋም እንደማንኛውም የሕክምና ባለሙያ በትርፍ ሰዓት ለሚሠሯቸው ሥራ የትርፍ ሰዓት አበል ታስቦላቸው ይሠሩ እንደነበር፣ ነገር ግን ከሁለት ዓመታት በፊት በነበረ የሰው ኃይል ዕጥረት ምክንያት ለሠሩበት የአሥር ወራት የትርፍ ሰዓት ክፍያ ይሰጠኛል ብለው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ክፍያው ሊከፈላቸው እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከተቋሙ ጋር በገቡት ዕሰጣ ገባ የተነሳ ክስ ቢመሠርቱም በሲቨል ሰርቪስ አስተዳደራዊ ችሎት ታይቶ አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ፣ የበጀት ውስንነት፣ በተቋሙ ያለው የሰው ኃይል እጥረትና ሰፋ ያሉ ምክንያቶች ከቀረቡ ቡኋላ የክፍያ ጠያቄው ውድቅ እንደተደረገባቸውና መጨረሻም ሥራውን ሳይፈልጉ ለመልቀቅ መገደዳቸው ይናገራሉ፡፡

የገለልተኛ ሠራተኛ ማኅበር አባል ቢሆኑና ጉዳዩ ለመደበኛ ፍርድ ቤት ቢቀርብ ኖሮ ለሠሩበት የትርፍ ሰዓት ጊዜ ማግኘት የሚጠበቅባቸው ክፍያ ያገኙ እንደነበር አቶ ትዕዛዙ ይናገራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሠራተኞች መብቶች ተሟጋቾች ድርጅት በዚህ የመንግሥት ሠራተኞች የመደራጀት መብት ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን ጋር በመሆን፣ ወደ ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሕገ መንግሥት መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶችን በተመለከተ በተያዘው ዓመት ክስ ለማቅረብ ዕቅድ ስለመያዙ የተናገሩት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ፌደሬሽኑም ባይተባበር እንኳ ድርጅቱ ብቻውን ክስ እንደሚመሠርት ተናግረዋል፡፡

የዜጎች የመደራጀት መብት ከመደራጀት አልፎ ሌሎች ያሏቸውን መብቶች ለማስጠበቅ ዋነኛ መሣሪያ Instrumental በመሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች ተደራጅተው እንደማኝኛውም ሠራተኞ ጥቅማቸውን ማስከበር እንደሚችሉና መደራጀትም እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡

የግል ሠራተኞች በመደራጀታቸው ምክንያት በሚያጋጥማቸው የሥራ ላይ አለመግባባት ወደ ክስ ሲሄዱ ጉዳያቸው የሚታየው በትክክለኛና ገለልተኛ በሆነ መደበኛ ፍርድ ቤት ቢሆንም ይህ መብት ግን ለመንግሥት ሠራተኛ የተሰጠ ዕድል አይደለም ይላሉ፡፡

 አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ከቀጣሪው ተቋም ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ወደ ክስ ቢሄድ ጉዳዩ የሚታየው በአስተዳደራዊ ፍርድ ቤት እንጂ እንደግልጽ ሠራተኛ  እንደገለልተኛና መደበኛ ፍርድ ቤት የሚሠራ ሳይሆን በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የተቋቋመ ነው፡፡

የአስተዳደር ፍርድ ቤት የሚቋቋመው በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ውስጥ በመሆኑና የገለልተኛ ጥያቄ የሚነሳበት ቅደም ተከተሉን የጠበቀ አቤቱታ ለማቅረብ የማይመችና የተወሰነው ውሳኔ ላይ ይግባኝ ለማለት ለመከራከር አስቸጋሪ እንደሚሆን አቶ ቁምላቸው ያነሳሉ፡፡ በኢትዮጵያ የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበር አለመኖርና እንዲደራጁ አለመፈቀዱን ሲያብራሩ በኢትዮጵያ ታሪክ ብዙውን ጊዜ የመንግሥት ሠራተኞች በተለይም እስከ ቡድን መሪ ድረስ ፖለቲከኛና ካድሬዎች መሆናቸውንና በሁለቱ መካከል የዘለቀ ትስስር ስለመኖሩን ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ሠራተኞች በሕግ ካላቸው መብት የበለጠ ፖለቲካዊ ተፅዕኖው ከፍተኛ በመሆኑ፣ ሠራተኞች ለሆነ ችግር መፍትሔ ቢፈልጉ የሚወስዱት አማራጭ ፖለቲካዊ መፍትሔን እንጂ የሕግ አንቀጽን በመጥቀስ የመከራከር ልምድ አለመኖሩ ለመደራጀት እንቅፋት ስለመሆኑ አክለው ያብራራሉ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የሕገ መንግሥታዊ መብቶችና ነፃነቶች የሚያስጠብቅ ችሎት የተቋቋመው በቅርቡ የመንግሥት ለውጥ ከተደረገ ወዲህ በአዋጅ 1234/2013 በወጣው ሕግ በመሆኑና አዋጁ ራሱ ዝርዝር ማስፈጸሚያ ያልወጣለት ስለሆነ፣ የመንግሥት ሠራተኞች የግል መብታቸውን በማስከበር የሚያስችላቸው ጥሩ ምኅዳር ገና አለመገንባቱን ያስረዳሉ፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንደሌሎች ተሟጋች ተቋማት ሁሉ የብዙኃኑን ጥቅም በሚመለከት ሠራተኞችን ወክለው ክስ እንዳያቀርቡ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓቱ ሕጉ ገደብ እንደነበረባቸው ገልጸዋል፡፡ ይህ ገደብ ከሳሹ ድርጅት ከሚያቀርበው ክስ በቀጥታ የሚደርስበት ኪሳራ ወይም ጥቅም መኖር አለበት ተብሎ ተቀምጦ እንደነበርና በሌላ ቋንቋ ክስ የሚያቀርበው ራሱ ሠራተኛው መሆን እንዳለበትና ሠራተኛው የሚከራከረው በጠበቃ ወይም በተወካይ ሳይሆን ራሱ መሆን አለበት በሚል እንደነበር ይናገራሉ፡፡

ይህ አሠራር በአዋጅ 1234/ 2013 ቢቀየርም፣ ነገር ግን አሁንም በግልጽ ተብራርቶ ሥራ እየተሠራበት አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ለሠራተኛ መብት ጥበቃ የሚያደርግ ማኅበር መኖር ለሠራተኛው የሥራ ላይ ደኅንነት ዋስትና መሆኑን የገለጹት አቶ ቁምላቸው ይህ ሊታሰብበት የሚገባ ትልቅ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው አህመድ፣ የመደራጀት መበት ሲባል ኢትዮጵያ መሠረታዊ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ከሚባሉትና ከፈረመቻቸው አሥር ስምምነቶች መካከል የመደራጀትና የመደራደር ጉዳይ ሁለቱ ቁልፍ መብቶች ናቸው፡፡

ሠራተኛ ‹‹የልማት ተቋም፣ የግልና የመንግሥት ተቋም›› ተብሎ በዓለም አቀፍ ድንጋጌ መሠረት ሊከፋፈልና የመንግሥት ሠራተኞች ከዚህ መብት ሊገለሉ አይገቡም፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 ላይ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ የሕግ አካል ናቸው ተብሎ ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም የመንግሥት ሠራተኛ በአሠሪና ሠራተኛ ሕጉም የመንግሥት ሠራተኞች የመደራጀትና የመደራደር ነፃነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡

የመንግሥት ሠራተኞች የሚደርስባቸውን ችግር በተወካዮቻቸው አማካይነት መድረስ ያለበት ቢሆንም፣ ሠራተኛው የሚደርስበትን ጥሰት የሚያደርስበት አደረጃጀት ባለመኖሩ፣ አንድ ሠራተኛ ከሠራተኛም ይሁን በተዋረድ ባሉ አመራሮች በደል ቢደርስበት ለሚኒስትሩ ወይም ለመንግሥት አቤቱታና ቅሬታ ማቅረብ የሚችሉበት አደረጃጀት የላቸውም፡፡

በዚህም የተነሳ ዘርፉ ትክክለኛ የሆነ ሠራተኛና አሠሪ መካከል ድርድር ወይም መብት ማስጠበቅ ያለበት በመሆኑ ጉዳዩ መፍትሔ እስከሚያገኝ ድረስ ግፊትና ጫና ማሳደሩን አያቆምም፡፡