የማነ ብርሃኑ

May 1, 2024

ምን እየሰሩ ነው?

ጎዳና ተዳዳሪነትን ለማስቀረት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለዓመታት ሠርተዋል፡፡ ከችግሩ ስፋት አንፃር ሙሉ ለሙሉ መፍትሔ ባያገኝለትም፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመለወጥ በሚሠሩ ሥራዎች ዕድሉን አግኝተው ራሳቸውን ማስተዳደር የጀመሩ፣ ከቤተሰብ የተቀላቀሉና ለሌላም የተረፉ አሉ፡፡ ከጎዳና አንስተው ልጆችን ለቁም ነገር ካበቁ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አንዱ ሲዳርታ ነው፡፡ አቶ ፍሬሁን ገብረ ዮሐንስ በሲዳርታ ዴቨሎፕመንት ኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የማነ ብርሃኑ በድርጅቱ ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ መቼ ተቋቋመ? የተቋቋመለትስ ዓላማ ምንድነው?

አቶ ፍሬሁን፡- ድርጅታችን በኢትዮጵያ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎችን መሥራት ከጀመረ 24ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ሰዎች በሕይወት አጋጣሚ፣ በተለያየ ምክንያት ከመንገዳቸው ይደናቀፋሉ፣ መንገዳቸውንም ይስታሉ፡፡ በመሆኑም መንገዳቸውን ፈልገው እንዲያገኙ ድርጅታችን ይሠራል፡፡ በዚህ ዙሪያም ብዙ ሰዎች በመንገዳቸው ላይ እንዲገኙ ለማድረግ ችለናል፡፡ ትኩረት አድርገን የምንሠራው በተለያየ ምክንያት ኑሯቸውን፣ ውሏቸውንና አዳራቸውን ጎዳና ላይ የመሠረቱ ሕፃናት፣ ወጣቶችና ሴቶች ከዚህ ሕይወት እንዲወጡ ማስቻል ነው፡፡ ይህንንም የምናደርገው ከጎዳና ላነሳናቸው ልጆች የሙያ ሥልጠና በመስጠት ራሳቸውን ችለው እንዲቆሙና ሕይወታቸውን በዘላቂነት እንዲለውጡ በማስቻል ነው፡፡ ድርጅታችን ከጎዳና ላይ ላነሳቸው ልጆች በቅድሚያ የሚያደርገው የማገገሚያ ማዕከል እንዲገቡ ማድረግ ነው፡፡ በማዕከሉ በሚያገኙት ሥልጠና አገግመው ከጨረሱ በኋላ በተለያዩ ሙያዎች ማለትም በብረታ ብረት፣ በእንጨት፣ በልብስ ቅድና ስፌት እንዲሁም በቆዳ ሥራ ሙያዎች እንዲሠለጥኑ ይደረጋል፡፡ ዕድሜያቸው ለሥልጠናው ብቁ ያልሆኑና ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ሲኖሩ ደግሞ ከቤተሰብ ጋር እንዲገናኙና ተጣልተውም ከሆነ በማስታረቅ፣ የማቀላቀል ሥራ እንሠራለን፡፡ ይህ ሥራ በራሱ ሰፊና አድካሚ ነው፡፡ ብዙ ሒደቶችም አሉት፡፡ ሆኖም ድርጅታችን ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ሲሠራበት የቆየና ውጤቶችም የተገኙበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ እስከ ዛሬ ምን ያህል ወገኖችን ከጎዳና ላይ አንስቷል? ለእነኚህ ወገኖች የምትሰጡት የሙያ ሥልጠናስ ምን ይመስላል?

አቶ ፍሬሁን፡– ድርጅታችን እስከ ዛሬ 2,698 ልጆችን ከጎዳና በማንሳት፣ ልዩ ልዩ  ሥልጠናዎችን በመስጠት ራሳቸውን እንዲችሉ አድርጓል፡፡ ከጎዳና የምናነሳቸው ልጆች በማዕከላችን የሚቆዩበትን ጊዜ በተመለከተ በልጆቹ የቀደመ የጎዳና ላይ ሕይወት የሚወሰን ነው፡፡ ለአንድ ዓመትና ለአሥራ አምስት ዓመታት ጎዳና የቆዩ ልጆች ካሳለፉት መራር የኑሮና የሕይወት ፈተና አንፃር በእኩል ጊዜ ያገግማሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በመሆኑም አንድ ዓመትና ሁለት ዓመት በጎዳና ላይ የቆዩ ልጆች ለማገገም ብቻ አራትና አምስት ወራት ሊፈጅባቸው ይችላል፡፡ ረጅም ዓመት በጎዳና ላይ የቆየው ግን ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ ዓመት ጊዜ ይወስድበታል፡፡ ወደ ቤተሰብ የሚቀላቀሉ የጎዳና ልጆች በማገገሚያ ማዕከላችን ለአምስት ወራት ያህል እንዲቆዩ ነው የምናደርገው፡፡ በቆይታቸውም ከልጆቹ ጋር ብቻ ሳይሆን  ከቤተሰቦቻቸውም ጋር በመገናኘት ሰፊ ሥራዎች እንሠራለን፡፡ ወደ ልዩ ልዩ የሙያ ሥልጠና የሚገቡትም የሙያ ሥልጠና ለአንድ ዓመት ያህል ሥልጠናቸውን እንዲከታተሉ ይደረጋል፡፡ ልጆቹ በሚወስዱት ሥልጠና ፕሮፌሽናል ባለሙያ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ የሚሠራ ይሆናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ ጎዳና ላይ የሚገኙ ልጆችን ከማንሳትና የሙያ ባለቤት እንዲሆኑ ከማስቻል ባሻገር ሌሎች የሚሠራባቸው ዘርፎች ይኖራሉ?

አቶ ፍሬሁን፡– ከእናቶች ጋር በተያያዘ ሰፊ ሥራ እንሠራለን፡፡ የቤት እማወራ ሆነው፣ ልጆች ኖሯቸው፣ ቤታቸውን የሚያስተዳድሩና ምንም ዓይነት የገቢ ምንጭ የሌላቸውን እናቶች እንደግፋለን፡፡ በየዓመቱ ከ120 እስከ 150 የሚሆኑ እናቶችን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በማሠልጠንና የሥራ መነሻ ካፒታል በመስጠት ወደ ሥራ እንዲሰማሩና ኑሯቸው በዘላቂነት እንዲለወጥ እናደርጋለን፡፡ እስከ ዛሬም 5,670 ያህል ሴቶችን ለመድረስ ችለናል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 120 አረጋውያን የሚገኙ ሲሆን እነኚህንም በየዓመቱ በቋሚነት የሚደጎሙ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርገን የምንሠራቸው ሥራዎች አሉን፡፡ ወጣቶች ያላቸውን ተሰጥኦና አቅም እንዲያውቁ፣ ይህንንም አውጥተው ለመጠቀም እንዲችሉ በሳምንት ሦስት ቀናት ከትምህርት ሰዓት ውጪ በኪነ-ጥበብ ዘርፍ እናሠለጥናለን፡፡ የምንሰጠውም ሥልጠና በባህላዊና ዘመናዊ ውዝዋዜ፣ በሙዚቃ መሣሪያዎች፣ በድምፅ፣ በቲዓትርና በመሳሰሉት ዘርፎች ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ቀጥሎ በዘርፉ የላቀ ሥልጠና እየሰጠ የሚገኘው የእኛ ተቋም ነው ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ ማዕከላችን ለእነዚህ ልጆች ሥልጠና የሚሰጠው ያለምንም ክፍያ በነፃ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በማዕከላችሁ በኪነ ጥበቡ ዘርፍ ምን ያህል ወጣቶች በመሠልጠን ላይ ይገኛሉ? ከእናንተ ማዕከል የወጡና በኪነቱ ዘርፍ ስኬታማ የሆኑ ወጣቶች ካሉ ቢጠቅሱልኝ?

አቶ ፍሬሁን፡- ድርጅታችን በየዓመቱ ከ230 በላይ ወጣቶችን እያወዳደረ በመቀበል፣ በጥበቡ ዘርፍ አሠልጥኖ ያስመርቃል፡፡ ከወራት በፊትም 208 ወጣቶች በብሔራዊ ቴዓትር አስመርቋል፡፡ እስከ ዛሬ ከ3,450 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ሥልጠናችንን ተደራሽ አድርገናል፡፡ ማዕከላችን የሚሰጠውን ሥልጠና ወስደው ለስኬት የበቁ ወጣቶች ቁጥርም ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡ ለምሳሌ በፊልሙ ኢንዱስትሪ ‹‹ረቡኒ›› በሚባል ፊልም ታዋቂነትን ያተረፈው የአብሥራ የተባለ ወጣት የማዕከላችን ፍሬ ነው፡፡ ጊታር ተጫዋቹ ኢዮሲያስ፣ ‹‹ጃዝ አቢሲኒያ››፣ እና ‹‹ዓድዋ ባንድ›› ከእኛ ማዕከል የተገኙ ናቸው፡፡ ‹‹በድሉ ኢሳያስ›› የተባለ ታዋቂ ድምፃዊና የውዝዋዜ ባለሙያው ተመስገን በቅፅል ስሙ ‹‹ተሙ›› የማዕከላችን ፍሬዎች ያፈራቸው ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውጪም በተለያዩ ቲዓትር ቤቶችና በክፍለ ከተማ የኪነት ቡድኖች ውስጥ ታቅፈው የሚንቀሳቀሱ በርካታ ወጣቶችም አሉ፡፡ በተጨማሪም በትምህርት ገበታ ላይ ለሚገኙና ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ከአምስት ሺሕ በላይ ተማሪዎች ድርጅታችን የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ እያበረከተ ይገኛል፡፡ በኤችአይቪ ኤድስ ምክንያት ወላጆቻቸውን ላጡና ቫይረሱ በደማቸው ለሚገኝ ሕፃናትና ወጣቶች ድጋፍና እንክብካቤ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ እነኚህን ተግባራት ሲያከናውን ከመንግሥትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ያለው የሥራ ግንኙነት ምን ይመስላል?

አቶ ፍሬሁን፡– ድርጅታችን ለሚተገብራቸው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች የመጀመሪያ አጋራችን መንግሥት ነው፡፡ በጤና ለምንሠራው የጤና፣ በትምህርት መስክ ለምናከናውነው የትምህርት፣ በሴቶች ላይ ለምንሠራው ሥራ የሴቶች እንደየ ዘርፋቸው የተቋቋሙ የመንግሥት መዋቅሮች ድጋፍ ያደርጉልናል፡፡ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትም ከእኛ ጋር በጥምረት የሚሠሩ ናቸው፡፡ በተለይ ከጎዳና ልጆች ጋር በተያያዘ በምንሠራው ሥራ መንግሥት በከፍተኛ ደረጃ እያገዘን ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት 24 ዓመታት ለሠራችኋቸው ሰው ተኮር ተግባራት የገቢ ምንጫችሁን ያገኛችሁት ከየት ነው?

አቶ ፍሬሁን፡- ድርጅታችን በተለያዩ ፕሮግራሞች እያከናወናቸው ለሚገኙ ተግባራት  ገንዘብ የሚያገኘው ከውጭ ዕርዳታ ነው፡፡ አብዛኛው ድጋፍ ከቤልጂየም ሕዝብ የተገኘ  ነው፡፡ ለበርካታ ዓመታት የሠራናቸውን ሥራ በማየትና በውጤቱም ደስተኛ በመሆናቸው የቤልጂየም ዜጎች ይደግፉናል፡፡ ከስድስት ዓመታት ወዲህ ግን በአገር ውስጥ የሚገኙ ተቋማትና ግለሰቦች ድጋፍ እንዲያደርጉልን ጥረት እያደረግን እንገኛለን፡፡ ይህንንም ለማሳካት የድርጅታችን በጎ ፈቃድ አምባሳደር የሆነው ድምፃዊ መሐሙድ አህመድ ደከመኝ፣ ሰለችኝ ሳይል የድርጅቱን ዓላማ በአገራችን ለሚገኙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ባለሀብቶችና ታዋቂ ግለሰቦች በማስተዋወቅ ረገድ ከፍ ያለ ሚና ተጫውቷል፡፡ በድምፃዊው አበርክቶም ታላላቅ ስኬቶችና ብዙ ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡ ሲዳርታ ዴቭሎፕመንት ላለፉት ዓመታት በማኅበረሰቡ ዘንድ ለውጥ ያመጡ ሥራዎችን ሲሠራ በኪራይ ቤት ሆኖ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እንደሚታወቀው ደግሞ የቤት የኪራይ ዋጋ እጅግ ንሯል፡፡ ድምፃዊ መሐሙድ የምንሠራውን ሥራ ጠንቅቆ ስለሚያውቅና ያለብንንም ችግር ስለሚረዳ የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የሆኑትን ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በማነጋገር፣ 4000 ካሬ ሜትር ቦታ ሃያት አካባቢ እንዲሰጠን አድርጓል፡፡ በዚህ ቦታ ላይም የራሳችንን ሕንፃ ለመገንባት ዕቅድ ይዘን በመንቀሳቀስ ላይ ነን፡፡ ይህንንም ሕንፃ በሕዝብ ተሳትፎና በአገር አቅም ለመገንባት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ ላለፉት ዓመታት የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን ተግዳሮት የሆኑበት ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

አቶ ፍሬሁን፡- ለበርካታ ዓመታት የድርጅቱ ተግዳሮት ሆኖ የቆየው የቦታ ጥያቄ ነበር፡፡ ከውጭ አገሮች በልመና የመጣ ገንዘብ፣ ለቀረፅናቸው የተለያዩ ፕሮጀክቶች ማዋል ሲገባን፣ ለግለሰቦች ቤት ኪራይ ሲውል በእጅጉ የሚቆጭ ነው፡፡ አሁን ላይ ግን ይህ የቦታ ጥያቄያችን ምላሽ በማግኘቱና መሬት መረካባችን መንገዳችንን አቅልሎታል፡፡ ሌላው የመታወቂያ ችግር ነው፡፡ ይኸውም ከጎዳና ልጆች ጋር ተያይዞ የሚገጥመን ነው፡፡ ድርጅታችን ከጎዳና ያነሳቸውን ልጆች አሠልጥኖ፣ ሥራ አስይዞና ደመወዝ እንዲያገኙ ካደረገ በኋላ፣ ልጆቹ መታወቂያ በማጣት ገንዘባቸውን ባንክ ለማስመቀመጥ ሲቸገሩ እንመለከታለን፡፡ በተጨማሪም ቤት ለመከራየት፣ ፓስፖርትና መንጃ ፈቃድ ለማውጣት መታወቂያ የግድ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በመሆኑም እነዚህ ልጆች በመታወቂያ ዕጦት ሲፈተኑ ማየት ያልተፈታና እስከ ዛሬ የዘለቀ ችግር ነው፡፡ ይህንም ችግር ለመቅረፍ በክፍለ ከተማና በወረዳ የሚገኙና ሥራችንን የሚያውቁ ኃላፊዎች እየተባበሩን ቢገኙም፣ መንግሥት በዚህ ዙሪያ ዘለቄታዊ መፍትሔ ማበጀት የሚገባው ይሆናል፡፡