ልናገር ገንዘብን በገንዘብ መግዛትና መሸጥ የሰነዶች ሁለተኛ ደረጃ ካፒታል ገበያ ንግድ ለኢትዮጵያ አንገብጋቢ…

አንባቢ

ቀን: May 1, 2024

በጌታቸው አስፋው

  1. የቀድሞ አቋሜ

ስለካፒታል ገበያ ጥቅም በተለያዩ ጊዜያት ባሳተምኳቸው መጽሐፍትና የጋዜጣ ላይ ጽሑፎች አብዝቼ ሞግቼ ነበር፡፡ ዛሬ ግን በተለያዩ ምክንያቶች በዚህ ወቅት ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ጥቅም የለም በማለት በተቃራኒው ቆሜያለሁ፡፡ በዋጋ ንረቱና በኑሮ ውድነቱ ባንኮች ሊመልሱ ያልቻሉትን ጥሬ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው መርጨታቸውንና ለመመገብ፣ ለመልበስ፣ ለመጠለል የሚያስፈልገውን ወጪ የትየለሌ መሆን አይቼ ኢኮኖሚው በገንዘብ መጥለቅለቁን አውቄ ሐሳቤን ቀይሬአለሁ፡፡ የኢኮኖሚው በገንዘብ መጥለቅለቅ (Financialization of the Economy) መገለጫን፣ ውጤትንና ጉዳትን ባለፈው ጽሑፌ አብራርቻለሁ፡፡ 

አቋሜን የቀየርኩባቸውን ምክንያቶች ከመግለጼ በፊት ቀድሞ የደገፍኩበትን ምክንያቶች ለመግለጽ በሁለት መጻሕፍቶቼ በጻፍኳቸው ጽሑፎች፣ የገንዘብ በገንዘብ ግዥና ሽያጭ የካፒታል ገበያ ሁለተኛ የሰነዶች ግብይይት (Securities Secondary Market) ንግድ ጠቃሚነት እምነቴን የቀየሩ የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታዎችና ወቅታዊ ጉዳዮች ደግሜ ደጋግሜ ሁለት ሦስት ጊዜ አስቤበት ወስኜ እንጂ፣ ሳይገባኝ ቀርቶ ከማወቅ ማነስ ምክንያት እንዳልሆነ ለማሳየት በጽሑፎቼ ያነሳኋቸውን አንዳንድ ነጥቦች አቅርቤ ወደ አዲሱ አቋሜ አመራለሁ፡፡  

– Advertisement –

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹ግላዊና ብሔራዊ ኢኮኖሚያችን›› በሚል ርዕስ በ2007 ዓ.ም. እና ‹‹ጥሬ ገንዘብና የዋጋ ንረት በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ በ2011 ዓ.ም. ጽፌ ባሳተምኳቸው መጻሕፍት ያካተትኳቸው ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡

በገንዘብ ገበያ ውስጥ የሚሸጠውና የሚገዛው ጥሬነት ነው፡፡ በአማርኛ ቋንቋ ጥሬ የሚለውን ቃል ለብዙ ነገር እንጠቀማለን፡፡ ያልበሰለ ነገር ጥሬ ነው ይባላል፣ ያላረጀም ነገር ያልተነካ ጥሬ ነው ይባላል፣ ሰዎች የእርሻ በሬ ሲገዙ ወይፈን ካገኙ የጉልበቱን ልክ ለመግለጽ ጥሬ ነው ይላሉ፡፡ ጥሬ ስንዴ ለቆሎ ይሆናል፣ ለንፍሮም ይሆናል፣ ለዱቄትም ይሆናል፡፡ አንዴ ንፍሮ ወይም ቆሎ፣ ወይም ዱቄት ከሆነ ግን ለሌሎቹ አይሆንም፡፡ ጥሬ ሥጋ ለጥብስ፣ ለወጥ፣ ለቅቅል ይሆናል፡፡ ጥሬ ወተትም ተፈልቶ ይጠጣል፣ ለእርጎ ይሆናል፣ ቅቤም ይወጣዋል፡፡ ስለዚህም ጥሬ ማለት በብዙ ዓይነት ሊጠቀሙት የሚችል ማለት ነው፡፡

በገንዘብ ኢኮኖሚ ትርጉምም በብዙ መልክ ልንጠቀመው የምንችለው ጥሬ ገንዘብ እንደ የጥሬነት ደረጃው (Liquidity Level) ተከፋፍሎ በተለያዩ ስሞች ይጠራል፡፡ ቴክኖሎጂና ሥልጣኔ ያመጣው የክሬዲት ካርድ ክፍያና ሌሎች የኤሌክትሮኒክ ቀጥታ መገበያያዎች ትርጉሙን እያደበዘዙት ቢመጡም፣ ብሔራዊ ባንክ የሚያሠራጫቸውና በኪሳችን ወይም በቤታችን የምንይዛቸው በጥሬነት ደረጃ በአንደኝነት የሚፈረጁት የብርና የሳንቲም ምንዛሪዎች (Currency) ምግብ፣ ልብስ፣ ጫማ፣ ወዘተ. ለመግዛት ለማኅበራዊ አገልግሎቶች ወዲያው ክፍያ ለመፈጸም ስለምንጠቀማቸው በጣም ጥሬ ገንዘቦች ናቸው፡፡ ከምንዛሪዎች ቀጥሎም የንግድ ባንኮች፣ የተንቀሳቃሽና የቁጠባ፣ እንዲሁም የጊዜ ተቀማጮች መልሶ ለማውጣት በመቅለሉ ዓይነት የጥሬነት ደረጃቸው ቢለያይም ጥሬ ገንዘቦች ናቸው፡፡ እነዚህ ባንኮች ጥሬ ገንዘብ (Money) ብለው በሪፖርቶቻቸው የሚነግሩን የጥሬ ገንዘብ ዓይነቶች ናቸው፡፡

ምንዛሪ ለብዙ ነገር አገልግሎት ስለሚውል ዋናው የጥሬ ገንዘብ ዓይነት በመሆኑ፣ እንደ ማንኛውም ቁሳዊ ወይም የአገልግሎት ሸቀጥ በገንዘብ ገበያ ይገዛል፣ ይሸጣል፣ የገበያ ዋጋም አለው፡፡ ምንዛሪ የእጅ በእጅ መገበያያ መሣሪያ ሲሆን ሦስት ባህሪዎች አሉት–የግብይይት መሣሪያ ስለሆነ የሸቀጦችን ዋጋ ይለካል፣ ክብደት ስለሌለው በኪስ ይያዛል፣ የመቶ ወይም የሃምሳ ብዙ ቁጥር የብር ኖቶች ወደ አሥርና አምስት ትንንሽ ኖቶች ይዘረዘራሉ ወይም ይሸራረፋሉ፡፡ ምንዛሪ በባንክ ቢቀመጥ ይወልዳል፣ ቢነገድበት ያተርፋል፡፡ ምንዛሪ የሌሎቹ የሀብቶች የቁሳዊም ሆነ የገንዘብ ሀብቶች ሁሉ ምንጭ ነው፡፡ የተጨማሪ እሴት ዋጋ መለኪያ ብቸኛ መሣሪያ ስለሆነ፣ ብቸኛው የገንዘብ በገንዘብ ንግድ ውጤት ያልሆነ የሥራ መጠንና የሥራ ዋጋን መለኪያ መሣሪያ ነው፡፡

የኤሌክትሮኒክ ግብይይት ከመጀመሩ በፊት ባንክ ያስቀመጥነውን ምንዛሪ ወደ ባንክ ሄደን ካላወጣነው፣ በድንገት ያጋጠመንና ለመግዛት የፈለግነውን ዓይነት ሸቀጥ ወዲያው ልንገዛበት አንችልም ነበር፡፡ ስለዚህም የባንክ ተቀማጭ በእጅ ከያዝነው ምንዛሪ ያነሰ ጥሬ ገንዘብ ነው፡፡ በተንቀሳቃሽ ሒሳብ በባንክ ያስቀመጥነው ቁጠባ ወደ ባንኩም ሳንሄድ ቼክ ጽፎ በመስጠት ብቻ ለሦስተኛ ወገን አንዲከፈል ማድረግ ስለሚቻል ከቁጠባ ሒሳብ የበለጠ ጥሬ ገንዘብ ነው፡፡ የቁጠባ ተቀማጭም ለማውጣት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መስጠት ከሚያስፈልገው የጊዜ ተቀማጭ የበለጠ ጥሬ ገንዘብ ነው፡፡ እነዚህ ጥሬ ገንዘቦች በምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ ካልተደገፉ ዋጋ የላቸውም፡፡

ምንዛሪ አንዱ የጥሬ ገንዘብ ዓይነት ሲሆን፣ ወደ ባንክ ሲገባ ወደ ሌላው ጥሬ ገንዘብ የተቀማጭ ጥሬ ገንዘብነት (Deposit Money) ዓይነት ይቀየራል፡፡ ስለዚህም ጠቅላላው የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት በሰዎች እጅ ተይዞ ለመገበያያ የሚያገለግለው ምንዛሪና ባንኮች ውስጥ የሚገኘው በብድር ሥርዓት ረብቶ በሒሳብ ደብተሮች በተቀማጭነት የሰፈረ ቁጥር ጥሬ ገንዘብ ናቸው፡፡ በተንቀሳቃሽ ወይም በቁጠባ ወይም በጊዜ ተቀማጭ በንግድ ባንኮች ያስቀመጡ ሰዎች ለተወሰኑ ጊዜያት የምንዛሪያቸውን ጥሬነት ለባንኮቹ ስለሸጡ፣ ምንዛሪያቸውን ለጊዜው ላጡበት የግብይይት ዋጋም ወለድ ያገኛሉ፡፡ ይህ ነው በኢትዮጵያም ዘመናት ያስቆጠረው የጥሬ ገንዘብ ንግድ ዓይነት፡፡

ባንኮች ከአስቀማጩ የተቀበሉትን ምንዛሪ አርብተው በማበደር ወይም በሸቀጥ ተገበያዮች የሒሳብ ደብተሮች ውስጥ ቁጥሮችን በመደመርና በመቀነስ ምንዛሪን የማርባት አቅማቸው፣ ልክ ወደ ባንክ ከገባው ምንዛሪ ብዙ እጥፍ የሆነ የባንክ ብድር ጥሬ ገንዘብ (Credit Money) ይፈጥራሉ፡፡

በገንዘብ ገበያ የሚሸጠውና የሚለወጠው ጥሬነት ነው፣ ገንዘብ እንደ ጥሬነት ደረጃው የግብይይት ዋጋ አለው፡፡ የጊዜ ተቀማጭን ማስጠንቀቂያ ሳይሰጡ ወዲያው ከባንክ ማውጣት ስለማይቻል በተፈለገ ጊዜ ወደ ጥሬነት መቀየር ይከብዳል፡፡ ነገር ግን ባንኩ የተቀማጭ ሰርተፊኬት (Certificate of Deposit) ሰነድ ከሰጠና በአገሩ ውስጥ የገንዘብ ገበያ መድረክ ካለ፣ ሰርተፊኬቱን ወይም ሰነዱን በቅናሽ ዋጋ (At a Discount Rate) ሸጦ ወይም አስይዞ ወደ ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብነት መቀየር ይቻላል፡፡ ዓመታዊ የቤት ኪራይ ውል ወይም ማንኛውም ዓይነት ገንዘብ ነክ ውል ካለም አከራዩ (ተዋዋዩ) ጥሬ ገንዘብ ከቸገረው ውሉን በቅናሽ ዋጋ ሊሸጥ ይችላል፡፡ ግብር አስገቢዎችና ማዘጋጃ ቤቶች የግብር ጊዜ እስከሚደርስ ሰነድ ሸጠው ጥሬ ገንዘብ ያገኛሉ፡፡ ገንዘብ ሚኒስቴርም በጀት ሲያጥረው የግምጃ ቤት ሰነዶችን ይሸጣል፡፡

በእንግሊዝኛ እነዚህን በጥሬነት ደረጃ (Liquidity Level) የተከፋፈሉ የገንዘብ ዓይነቶች በተለያዩ ስሞች ይጠራሉ፡፡ ምንዛሪዎችን “Currency”፣ ጥሬ ገንዘብን “Money”፣ ገንዘብን “Finance” ብለው ይጠራሉ፡፡ እኛ በአማርኛ በጥቅል ስማቸው ሁሉንም ገንዘብ ብለን ስለምንጠራ ዘርዝረን ለመተንተንና ስለወለድ ትርጓሜ ለመረዳት እንቸገራለን፡፡ እንግሊዞች በፈሳሽነት መስለው ሲጠሩ እኛ በጥሬነት መስለን ለመጥራት እየተሸማቀቅን ስለገንዘብ ገበያ እንዴት ልንረዳ እንችላለን?

በባንክ አማካይነት የሚከናወን የጥሬነት ገበያ በብድር ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ሥርዓት (Credit Based Financial System) ይባላል፡፡ ፈረንሣይ፣ ጃፓን፣ ጀርመን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ቻይና ኢኮኖሚያቸው እስከሚዳብር ይህ ሥርዓት ነበራቸው፡፡

ጥሬ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ሰነዳዊ ገንዘቦችም በካፒታል ገበያ አማካይነት ይሸጣሉ፣ ይገዛሉ፡፡ ወጣቶች በረጅም ጊዜ የሚመለሱ ሰነዶችን ይገዛሉ አዛውንቶች በአጭር ጊዜ የሚመለሱ ሰነዶችን ይገዛሉ፡፡ የንግድ ወረቀቶችን (Commercial Papers)፣ የማዘጋጃ ቤት ሰነዶችን (Municipal Papers)፣ የግምጃ ቤት ሰነዶችን (Treasury Bills)፣ አክሲዮኖችንና ቦንዶችን የመሳሰሉ ገንዘቦች የምንዛሪና የንግድ ባንኮች ተቀማጮችን ያህል ጥሬ ገንዘቦች አይደሉም፡፡ የዕዳ ሰነዶች እንደ የመዳረሻ ቀናቸው (Maturity Date) ይለያያሉ፡፡ ነገር ግን ለአስቸኳይ ጉዳይ ምንዛሪና የባንክ ተቀማጭ ከተፈለጉ ሰነዳዊ ገንዘቦቹ በቅናሽ ዋጋ ተሸጠው ወይም እንደ መያዣ ተጠቅሞ ወደ ጥሬ ገንዘብነት ሊቀየሩ ይችላሉ፡፡ የገንዘብ ዓይነቶችን በጥሬነት ደረጃ አውቆ የጥሬ ገንዘብና የወለድ ግንኙነቶች ጽንሰ ሐሳብን ያልተረዳ ሰው፣ በካፒታልና በገንዘብ ገበያ ውስጥ ዘው ብሎ ሊገባ አይችልም፣ እናውቃለን በሚሉ የመታለል ዕድሉም ሰፊ ነው፡፡

ከአንድ ዓመት በላይ የሆነ መዳረሻ ያለው የካፒታል ገበያን (Capital Market) እና ከአንድ ዓመት በታች የሆነ መዳረሻ ያለው የጥሬ ገንዘብ ገበያን (Money Market) በጋራ የሚወክለው የገንዘብ ገበያ (Financial Market)፣ ሰነዶችን መግዛትና መሸጥ በገበያ ላይ የተመሠረተ የገንዘብ በገንዘብ ግዥና ሽያጭ ሥርዓት (Market Based Financial System) ይባላል፡፡ በአሜሪካ፣ በእንግሊዝና ሌሎች የምዕራብ አገሮች ከመቶ ዓመታት በላይ ታሪክ አለው፡፡

በካፒታል ገበያ ላይ የተመሠረተ የጥሬነት ገበያ ቁማር ሊመስል ይችላል፣ ቁማር ነው ማለትም ይቻላል፡፡ ሆኖም ገንዘብ ፈላጊና ገንዘብ ሻጭን አገናኝቶ የንግድ ሥራ እንዲቀላጠፍ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ የሚፈጥረው ተጨማሪ እሴትም (Value Added) ሲረክስ ገዝቶ አስቀምጦ ሲወደድ መሸጥ ጥሬ ገንዘብ የማቅረብ አገልግሎት ነው፡፡ ከታላላቅ መንግሥታት መሪዎች ጀምሮ እስከ የታወቁ ቱጃሮች የመክበር ምክንያትና ምንጭ የጥሬነት ገበያ ሲሆን፣ ከትንሽ እስከ ትልቅ ያለው የበለፀጉት አገሮች ሕዝብ በአጭር ጊዜ ውስጥ የኑሮ ደረጃ መለወጥ ምክንያትም በጥሬነት ገበያ ውስጥ ለካፒታልና ለሥራ ማስኬጃ ሰነድና ምንዛሪ ተነጋግዶ የንግድ ሥራን ማቀላጠፍ ነው፡፡ የአክሲዮንና የቦንድ የካፒታል ገበያዎች ጥሬነትን ከመፍጠር ባሻገር አስተውሎና አጣርቶ ለሚገዛ ተገበያይ ከአክሲዮኑ በስተጀርባ ያለውን ድርጅት ትርፋማነት መለኪያ መንገድም ስለሆኑ፣ የሀብት ድልድልና የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትን ውጤታማ በማድረግ በኩል የተዋጣላቸው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መሣሪያዎች ናቸው፡፡

ቁጥራቸው በርከት ያለ የገንዘብ ገበያ ተቋማት ለኅብረተሰቡ፣ ለግለሰቦች፣ ለድርጅቶችና ለመንግሥት አገልግሎቶችን ይሰጣሉ፡፡ ንግድ ባንኮች ከቆጣቢዎች ወደ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ጥሬ ገንዘብ ያስተላልፋሉ፣ ሞርጌጅ ባንኮች ለቤት ሠሪዎች ብድር ያመቻቻሉ፣ የጡረታ ጥሪቶች (Pension Funds) በቁጠባና በመዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ተግባራት ይሳተፋሉ፣ የመዋዕለ ንዋይ ባንኮች ከሕዝባዊ ኩባንያዎች አክሲዮን በጥቅሉ ገዝተው ለሕዝብ በሽርፍራፊ (Underwriting) ይሸጣሉ፣ ኢንሹራንሶች ለአደጋ ጊዜ ዋስትና ይሰጣሉ፡፡ የጋራ መዋዕለ ንዋይ ጥሪቶች (Mutual Investment Funds) የብድር መያዣ ሰነዶችን በማዳበል (Repackaging or Clubbing Together) አዳዲስ የሰነድ ዓይነቶችን ፈጥረው ለአባሎቻቸው ይሸጣሉ፡፡ ለግል የካፒታል ገበያ ተሳታፊ ተቋማትና ግለሰቦችም ምክር ይሰጣሉ፡፡ የአደራ ጥሪቶች (Trust Funds)፣ የአባሎቻቸውን ንብረት ያስተዳድራሉ፣ የገንዘብ ተቋማት ከገበያ እንዳይወጡም ዋጋው በወደቀ ሰነድ ቢከስሩ በሌላው ዋጋው በተነሳ ለማትረፍ እንደ መጠበቂያ መድን ጥሪት (Hedge Fund) ያቋቁማሉ፡፡ 

  1. የዛሬ አቋሜን የያዝኩባቸው ምክንያቶች

ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት የጤናማ ኢኮኖሚ የገንዘብ በገንዘብ ግብይይት ሥርዓት መገለጫዎች እንጂ፣ እንደ ኢትዮጵያ ላለ የምርት ኢኮኖሚ ገበያ መዳከምና የዋጋ መዋዠቅ ውዝግብ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ መለኪያዎች አለመረጋጋት፣ የውጭ ምንዛሪ መውደቅን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው የአገር ሀብትን በርካሽ ዋጋ ለመቀራመት ላሰፈሰፉ የውጭ ሰዎች ሲሳይ ሊኮን የሚቻልበት ሁኔታ ባለበት፣ ለቁጠባና ለመዋዕለ ንዋይ መመጣጠን የምርት ኢኮኖሚው ፍላጎትና አቅርቦት መዳበር በሚያስፈልግበት ወቅት፣ የሕዝቡ የመቆጠብ አቅምና ፍላጎት በተዳከመበት ሁኔታ ውስጥ እንዳልሆነ የሚያመላክቱ አንዳንድ ነጥቦችን አንስቼ አብራራለሁ፡፡ 

2.1 በዓለም አቀፍ ተቋማት ስብከት ላለመታለል

ዓለም አቀፍ ተቋማት ገንዘብን በገንዘብ በመግዛትና መሸጥ ንግድ ድራማ እየተወኑብን ነው፡፡ በዓለም ንግድ ድርጅት (World Trade Organization) አማካይነት በፕራይቬታይዜሽን መርህ እንደ ቴሌና አየር መንገድ የመሳሰሉ ትልልቅ ተቋማቶቻችሁን ሽጡ ይሉናል፡፡ በዓለም አቀፍ የጥሬ ገንዘብ ጥሪት (International Monetary Fund) አማካይነት ዛሬ በአንድ ዶላር ሊገዙ የሚችሉትን 56 ብር የሚያወጣ ሀብት፣ ነገ በሃምሳ ሳንቲማቸው ሊገዙ የብራችሁን ዋጋ አዳክሙ ይሉናል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግብይይቱና የካፒታል ገበያ ነገ ባዶ እጃችንን ሊያስቀሩን ይችላሉ፡፡

ስምንት መቶ ብር የሚያወጣ የቴሌ ወይም የአየር መንገድ አክሲዮን፣ በቀን ስምንት ሰዓት በሳምንት አርባ ሰዓት በወር አንድ መቶ ስልሳ ሰዓት ለሚሠራ ለሐዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ሠራተኛ  የወር ደመወዙ ዋጋ ነው፡፡ በሰዓት ሃያ ዶላር ደመወዝ ለሚያገኝ አሜሪካዊ የብር በዶላር ምንዛሪ ወደ መቶ ሃያ ሲወድቅ ስምንት መቶ ብር የሚያወጣ የቴሌ ወይም የአየር መንገድ አክሲዮን ስድስት ዶላር ከስልሳ ሰባት ሳንቲም የሃያ ደቂቃ ደመወዙ ነው፡፡ ሰዎች ለገንዘብ የሚከፍሉት ዋጋ በሥራ ላይ የሚያውሉት ጊዜያቸው ስለሆነ የኢትዮጵያዊ የአንድ ወር አንድ መቶ ስልሳ ስድስት ሰዓት የሥራ ጊዜ ከአሜሪካዊ ሃያ ደቂቃ የሥራ ጊዜ ጋር እኩል ሆነ ማለት ነው፡፡ አገሮች ወደ ግሎባል ገበያ ለመግባት ከማሰባቸው በፊት ሊያጤኑት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ትልቁና ዋናው የልዩ ልዩ አገሮችን ሕዝቦች የኑሮ ደረጃ መለኪያና መመዘኛ የግብይይት አቅምም መገመቻ መሥፈርት ነው፡፡ 

2.2 የምርት ኢኮኖሚስቶች ጽንሰ ሐሳቦችን በማጤን

ኢኮኖሚስትነት የኢኮኖሚ ሊቃውንት ተመራምረው የደረሱበትንና በጽንሰ ሐሳብ መልክ የነደፉትን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ መረዳት ነው፡፡ በመሰለኝና በደሳለኝ የሚናገሩት ዕውቀት አይደለም፡፡ ስለሆነም ስለምንናገረው ትክክለኛነት በኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳብ ማስረጃ ማረጋገጥ አለብን፡፡ ኢኮኖሚስቶች ሁሉ የአገርን ዕድገት የሚያደናቅፈው የካፒታል እጥረት እንደሆነ በጋራ ቢገነዘቡም፣ የካፒታል እጥረትን ለመቅረፍ ስለሚወሰዱ ዕርምጃዎች ግን የተለያዩ ሐሳቦችን ይሰነዝራሉ፡፡ እንደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታዎች አገናዝበን ለመተግበር የተለያዩ ጽንሰ ሐሳቦችን ማነፃፀር ይኖርብናል፡፡

ከክላሲካል ኢኮኖሚስቶች ጀምሮ እስከዚህ ዘመን እየተሻሻለና እየዳበረ የመጣ የብድር ጥሪት ጽንሰ ሐሳብ (Loanable Fund Theory)፣ ቁጠባና መዋዕለ ንዋይ የሚመጣጠኑበት የወለድ ምጣኔ ቀመር ነው፡፡ በክላሲካል ኢኮኖሚስቶች ዘመን ለወለድ ምጣኔ ቁጠባንና መዋዕለ ንዋይን ማመጣጠን በገንዘብ ገበያ ትልቅ ትኩረት የተሰጠ ቢሆንም፣ ኬንስና ተከታዮቹን የመሳሰሉ ማክሮ ኢኮኖሚስቶች ገቢ ከሌለ ቁጠባ ስለማይኖር ቁጠባን ለማሳደግ ከወለድ ምጣኔ የገንዘብ ገበያ ይልቅ፣ ለብሔራዊ ገቢ የምርት ገበያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ኬንስ ከገቢ መጠን እንጂ ከወለድ ምጣኔ ጋር አይለዋወጡም ያላቸውን ለግብይይት (Transactionary) እና ለጥንቃቄ (Precautionary) ተብለው የሚያዙ በብሔራዊ ገቢ መጠን ላይ ጥገኛ የሆኑ የጥሬ ገንዘብ ፍላጎት ዓይነቶችን ትቶ፣ በወለድ ምጣኔ ላይ ጥገኛ የሆነውን ጥሬ ገንዘብ (Speculative Demmand for Money) ብቻ የጥሬ ገንዘብ ፍላጎት መመዘኛ አድርጎ የጥሬነት ምርጫ ጽንሰ ሐሳብን (Liquidity Preference Theory) ነድፏል፡፡ ከእሱ በኋላ የመጡ ማክሮ ኢኮኖሚስቶችም ከወለድ ምጣኔ ይልቅ የምርት ፍላጎትና የምርት አቅርቦትን ለሚያመጣጥን ብሔራዊ ገቢ የምርት መጠን የላቀ ትኩረት ሰጥተዋል፡፡ የቁጠባና የመዋዕለ ንዋይ መመጣጠንም ኬንስ የተሟላ ፍላጎት (Effective Demand) ብሎ ከሰየመው ከጥቅል ምርት ፍላጎትና ከጥቅል ምርት አቅርቦት መመጣጠን የተቀዳ ወይም ተቀጂ (Derivative) እንደሆነ በሞዴል ሥሌት አረጋግጠዋል፡፡

ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ሰፊ አምራች የሰው ኃይልና ሰፊ ገበያ ስላላት ዕምቅ የማምረትና የመነገድ አቅሟ (Potential Output Level) እጅግ ከፍተኛ ሆኖ፣ አሁን የምታመርተው ምርት መጠን (Actual Output Level) ከማምረት አቅሟ የራቀና ዝቅተኛ በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነትም ሰፊ ነው፡፡ ለወደፊት የማደግ ዕድሏ ከፍተኛ ቢሆንም የሕዝቡ መሠረታዊ የኑሮ ፍላጎቶች ባለመሟላታቸው የሚነደፉትን ፖሊሲዎች ውስብስብ ስለሚያደርገው፣ ስለገንዘብ ኢኮኖሚው ብቻ በተናጠል ማሰብ ስህተት ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት ለማደግ የተንደረደረችው በልማታዊ መንግሥት ፍልስፍና ልማት ባንኩን ተጠቅማ ለወሳኝ የምርት ኢንዱስትሪ ዘርፎችና ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ በማድላት (Preferencial Treatment) አይደለምን?

2.3 የድርጅቶችንና የሕዝቡን አቅምና ዝግጁነት በመመልከት

ከውጭ የመጡ የካፒታል ገበያ ውስጥ ሠርቼ አውቃለሁ የሚሉ ተሟጋች ምሁራን ዘወትር የሚነግሩን በአሜሪካና በእንግሊዝ የካፒታል ገበያ ስለሰጠው ጥቅም ነው፡፡ በ1960ዎቹ በኢትዮጵያ ተጀምሮ እንደነበርም ለማሳመኛነት ያነሳሉ፡፡ ከባቡር ሐዲድ፣ ከአውቶሞቢል፣ ከኮምፒዩተር ፈጠራ ጋር ተያይዞ የተጀመሩና የተስፋፉ የአሜሪካና የእንግሊዝ የካፒታል ገበያ ምሳሌ የሚሰጡ ምሁራን፣ አሜሪካና እንግሊዝ ስለካፒታል ገበያ ያሰቡትና የጀመሩት የሕዝቡ ገቢ እያደገ በነበረበት፣ ድርጅቶች ገበያ አጥተው ባልተቸገሩበትና ሊዘጉ ባልደረሱበት፣ የሒሳብ መዝገባቸው ቢመረመር ትርፍን እንጂ ኪሳራን በማያመለክትበት ብሩህ ተስፋ በነበራቸው ጊዜ መሆኑን አብረው ሊነግሩን ይገባል፡፡

የኢትዮጵያው ተብሎ እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው የ1960ዎቹ ሼር ዲሊንግ የካፒታል ገበያ የአዋሽ ሸለቆ ልማትን ተከትሎና ሌሎች በፍጥነት ያደጉትን ሰፋፊ የምርት ኢኮኖሚ ድርጅቶች ተመርኩዞ የመጣ ወጣት፣ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ወደ እርሻና ወደ ኢንዱስትሪ ምርት በገቡበት ጊዜ እንጂ፣ እንደ ዛሬ ለቤት ኪራይ እንኳ የማትበቃ ደመወዝ ለማግኘት ለታቦታት ስለት በሚሳሉበት፣ ረጅም ዓመታት ያስቆጠሩትን ቴሌና አየር መንገድን ብቻ መሠረት አድርጎ አልነበረም፡፡ 

በዋጋ ንረትና በብር የውጭ ምንዛሪ መውደቅ የሕዝቡ ገቢ በማሽቆልቆል ላይ ባለበት፣ ሰነድ ለመግዛት የሚያስችል ቁጠባ ሊኖረው የሚችል ኢትዮጵያዊ በሌለበት፣ የገንዘብ በገንዘብ ግብይይት የካፒታል ገበያ ንግድ ጥቅም ከጥቂቶች በስተቀር ለብዙዎች አይታይም፡፡ የዋጋ ንረት ሰላላ በመቶ ሆኖ በሰባት በመቶ ወለድ የምንዛሪውን ጥሬነት ለባንክ የሚሸጥ አስቀማጭ አትራፊ ነጋዴ ነውን ብለን ብንጠይቅ መልሱ አሉታዊ ነው፡፡ ምክንያቱም በዓመቱ መጨረሻ ምንዛሪው ከእነ ወለዱ አንድ መቶ ሰባት ብር ቢሆንለትም፣ የምንዛሪው ሸቀጦችን የመግዛት አቅም በሰላሳ ብር ስለሚቀንስ ያገኘውና ያጣው ተቀናንሶ ሸቀጦችን በመግዛት አቅሙ ልክ የተለካው የተጣራ ምንዛሪው ሰባ ሰባት ብር ብቻ ስለሚሆን ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንዛሪዎቹን በባንክ የሚያስቀምጠው በአደጋ ምክንያት ከመጥፋትና ከስርቆት ለመዳንና ለክፉ ቀን መጠባበቂያ ብሎ እንጂ ወለድ ለማግኘትና ለማትረፍ አይደለም፣ ልምዱም ፍላጎቱም የለውም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ የማስተርስ ዲግሪ ሲኖራቸው፣ ለዶክተሬት ዲግሪ በመማር ላይ ናቸው፡፡ በሙያቸውም በዩኒቨርሲቲዎች በማስተማርና በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከማገልገላቸውም በላይ ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማርኛ ቋንቋ አራት መጽሐፍትን በመጻፍ በጋዜጦችና በመጽሔቶችም የሚነበቡ ጽሑፎችን አበርክተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በማይክሮ ኢኮኖሚና በማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮች በግል ምርምር በማድረግና የምክር አገልግሎት እየሰጡ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመላካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው getachewasfaw240@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡