ፅዮን ታደሰ

May 1, 2024

አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር) የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በኦሞ ኩራዝ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ምንም ዓይነት ሥራ ባልተሠራበት 70.5 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉ ተገለጸ፡፡

የውኃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ሚኒስቴሩ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ባቀረበበት ወቅት እንደገለጸው የኦሞ ኩራዝ መስኖ ልማት ፕሮጀክት በ2016 በጀት ዓመት 13 በመቶ ለማከናወን ዕቅድ ይዞ የነበር ቢሆንም ማሳካት የቻለው ግን 0.023 በመቶውን ብቻ መሆኑና ይህም የዕቅዱን 0.08 በመቶ ብቻ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ 

ሚኒስቴሩ ዕቅዱን ሲያወጣ መነሻ ያደረገው በ2015 ዓ.ም. የተሠራውን ሥራ እንደሆነ ቢገልጽም፣ ቋሚ ኮሚቴው ባደረገው የመስክ ምልከታ መሬት ላይ ‹‹አንድም ሥራ አለመሠራቱን ተመልክቻለሁ›› በማለት ገልጾ፣ ባልተሠራ ሥራ 70.5 ሚሊዮን ብር ወጪ ሆኖ ክፍያ ተፈጽሟል ብሏል፡፡

ይህም መንግሥትን ለተጨማሪ ወጪ ከመዳረጉ ባለፈ መመረት ያለበትን ምርት እንዳይመርት ማድረጉን አመላክቷል፡፡ በዚህም ከፕሮጀክቱ መዘግየት ጋር በተያያዘ ላለው ችግር በኃላፊነት የሚጠየቀው ማን እንደሆነ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኦሞ ኩራዝ አንድ፣ ሁለትና ሦስት ላይ ባደረገው የመስክ ምልከታን መነሻ ያደረጉ ጥያቄዎችን ያቀረቡት መሐመድ አብዱ (ፕሮፌሰር)፣ የሽንኮራ አገዳን ለማምረት የሚያስችሉ ቦዮች ተገንብተው ባለማለቃቸው ስኳር ፋብሪካዎች ላይ ችግር ፈጥሯል ብለዋል፡፡

አክለውም የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ፋብሪካ የአገዳ ልማቱ ውኃ እንዲያገኝ የሚያስችለው ግድብ ባለማለቁ ሥራውን ማከናወን አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡ 

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር)፣ የኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ ማምረት ያልቻለው ‹‹ግድቡ ስላልተሠራ ነው የሚል መረጃ የለኝም›› ብለዋል፡፡ ‹‹50 ሺሕ ሄክታር መልማት የሚችል መሬት ስኳር ኮርፖሬሽን እጅ ላይ አለ›› ያሉት ሚኒስትሯ፣ ኮርፖሬሽኑ ያለማው ግን 14 ሺሕ ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

‹‹ኮርፖሬሽኑ ባለማልማቱ ምክንያት የመከላከያ ፋውንዴሽንን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ድርጅቶች እየገቡ ምርት እያመረቱ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ችግርን ለሌላ አካል ማስተላለፍ ሳይሆን የሚሻለው ተቋማቱ በጋራ ቁጭ ብለው ቢነጋገሩ ይሻላል በማለት ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት ስኳር ፋብሪካ በፀጥታ ችግር ምክንያት ምርት ለማቆም እየተገደደ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በተጨማሪም ፋብሪካው ሥራ ቢጀምርም የፕሮጀክት ሥራው ባለመጠናቀቁ በተለይም ፋብሪካው መፍጨት የሚችለውን ያህል ሸንኮራ እያመረተ እንዳልሆነ ዋና ሥራ አስኪያጁ ፈለቀ ቶማ (ኢንጂነር) ገልጸው ነበር፡፡