ተማሪዎች

ከ 4 ሰአት በፊት

ተማሪዎች በቀጣይ ምን ሊፈጠር እንደሚችል እርግጠኛ አይደሉም።

ፖሊሶችና የግል ጥበቃ ሠራተኞች በትነዋቸዋል። ትምህርት ቆሟል። ፈተናም የለም።

ተማሪዎች ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ ዩኒቨርስቲው ፖሊስ መጥራቱ እጅግ አሳዝኗቸዋል። ፖሊስ ተማሪዎች ተቆጣጥረውት የነበረው የሃሚልተን ሕንጻን ጥሶ ገብቷል። ከ100 በላይ ሰዎችም ታስረዋል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ኔሜት ሻፊክ፣ ፖሊስ ወደ ቅጥር ጊቢው እንዲገባ ያዘዙት “እያዘኑ” መሆኑን ተናግረዋል።

ተቃውሞ ውስጥ ተማሪ ያልሆኑ ሰርገው ገብተዋል ብለዋል ፕሬዝዳንቷ።

ከደረሰው ነገር “ለማገገም ጊዜ ይወስዳል” ሲሉም አክለዋል።

ተመራቂ የጋዜጠኝነት ተማሪ አና ኮክስ “ነገሮች የፈራረሱ ይመስላሉ” ብላለች።

“ሁሉም ነገር ካለቀ በኋላ የሚሰማው የመሰበር ስሜት ነው” ስትል የገለጸችው አና፣ ፖሊሶች ተማሪዎችን ሲበትኑ እየዘገበች ነበር።

ፖሊሶችና ተማሪዎች ከተፋጠጡበት ምሽት በኋላ የቀረው የተቃውሞ ማስታወሻ በውሃ የራሱ መፈክሮች ናቸው። አንደኛው “አናቆምም። ወደኋላ አንልም” ይላል።

የትምህርት ዘመን መዝጊያ ፈተና ስለመውሰዳቸውና ዩኒቨርስቲውም በቀጣይ ምግብ ስለማቅረቡ እርግጠኛ እንዳልሆኑ ተማሪዎች ይናገራሉ።

ዊል ፓርኪንሰን 20 ዓመቱ ነው። የአካባቢ ሳይንስ ተማሪ ነው። “ግራ የሚገባ ስሜት ውስጥ ነኝ” ይላል።

“ምን ማድረግ እንዳለብን እርግጠኛ አይደለንም” ብሏል ተማሪው።

ፖሊሶች የሃሚልተን ሕንጻን ሲወሩ መስኮት ላይ ሆኖ እየተመለከተ ነበር።

ዩኒቨርስቲው ሠራተኞችን ስለቀነሰ መመገቢያ ገንዘብ እንደሰጣቸው ይናገራል።

መመሪቂያ ጽሑፉን መቼ እንደሚጽፍ እርግጠኛ አይደለም።

“ፖሊሶች ከካምፓስ ውጡ” “የተማሪ ኃይል ከእስራኤል ኃይል ጋር ሲነጻጸር” የሚሉና ሌሎችም መፈክሮች ይዘው ነበር ተማሪዎች ተቃውሞ የወጡት።

መምህራን እንዴት የትምህርት ጊዜውን እንደሚጨርሱ አያውቁም። ወደ ዩኒቨርስቲው እንዳይገቡ ገደብ ተጥሏል።

ፕ/ር ጆሴፍ ሆሊ የተባሉ መምህር “መማርም መሥራትም የማይችሉ ተማሪዎች አሉኝ። 16 መምህራን እንዴት ተማሪዎቻቸውን መደገፍ እንደሚችሉ ይጠይቁኛል” ብለዋል።

ለተማሪዎቹና መምህራኑ ጥያቄ ምላሽ ያላገኙት ፕሮፌሰር ተቃውሟቸውን ለማሰማት አደባባይ ወጥተዋል።

ፖሊስ ወደ ዩኒቨርስቲው እንዲገባ መደረጉ በዩኒቨርስቲው ያላቸውን እምነት እንደሸረሸፈው ተናግረዋል። “አሳፋሪ” ሲሉም ድርጊቱን አውግዘዋል።

ፖሊሶች “ድንገት መጡብን። ተገፍተናል። ተደብድበናል። እጄን ጠፍንገው አስረውኝ ከፍተኛ ሕመም ውስጥ ነኝ” ሲሉ ገልጸዋል።

የኒው ዮርክ ፖሊስ ግን ኃይል እንዳልተጠቀመ በመግለጽ ክሶቹን አስተባብሏል።

ለቀጣይ ቀናትም በዩኒቨርስቲው ፖሊሶች የሚቆዩ ይሆናል።

የ31 ዓመቷ የጋዜጠኝነት ተመራቂ ተማሪ ሜጋን ቦስ እንዳለችው ፖሊሶች “ቁጡና ኃይለኛ” ነበሩ።

ፖሊስ በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ 109 እና በሲቲ ኮሌጅ ኦፍ ኒው ዮርክ 173 ሰዎችን ማሰሩን ገልጿል።

የፖሊስ ኮሚሽነር ኤድዋርድ ካባን “የሕዝብ ደኅንነት ዋነኛ ጉዳያችን ነው። ሥራችንን እንድንሠራ ነው የተጠራነው” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።