ሊዲያ ሎሚኮቭስካ

ከ 5 ሰአት በፊት

ሊዲያ ሎሚኮቭስካ የ98 ዓመት አዛውንት ናቸው። የሩሲያ ወረራ በዓይናቸው ከተመለከቱት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት የከፋ ሆኖባቸዋል።

ደመ ነፍሳቸውን ማመንን ተምረዋል።

ለዚህም ነው የሩስያ ጦር በምስራቅ ዩክሬን ውስጥ ወደምትገኘው የትውልድ መንድራቸው ኦቼሬቲን ሲገባ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመሸሽ የወሰኑት።

በከባዱ የተኩስ ልውውጥ ወቅት ሊዲያ ከዘመዶቻቸው ተለያዩ። ነጠላ ጫማቸውን እንደተጫሙ ተስፋ ሳይቆርጡ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ጉዟቸውን ቀጠሉ።

“የምደገፈው እንጨት ይዤ መንገዴን ጀመርኩኩ። እውነት ለመናገር እግሮቼ እንደምንም ተሸክመውኝ ነበር እንጂ አልተሸከምኳቸውም!” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

10 ኪሎሜትር ገደማ ከተጓዙ በኋላም የዩክሬን ፖሊሶች ደርሰውላቸዋል።

“ምንም የቀረ ነገር የለም! ሁሉም እንዳልነበር ሆኗል!” ሲሉ ስለጉዟቸው ተናግረዋል።

በሩሲያ ጥቃት ምክንያት ትተውት የወጡት መንደር ቀስ በቀስ ወደ ገሃነምነት እየተለወጠ ነው።

ወደ መንደሯ በተጠጉ ቁጥር የጥይቱ እሳት የበለጠ እየጠነከረ ይሄዳል። አፓርታማዎች እና ቤቶች ቀስ በቀስ ወደ ፍርስራሽ እና አቧራ መለወጥ ይጀምራሉ።

ሊዲኣ 10 ኪሜ ገደማ በእግር ተጉዘዋል

“መራመድ ከጀመርኩ በኋላ ሁለት ጊዜ መተኛት ነበረብኝ። አንድ ጊዜ ሚዛኔን ስቼ ሳር ላይ ወድቄ ነበር። ተኝቼ ስነሳ መጓዜን ቀጠልኩኝ” ብለዋል ሊዲያ።

ከፖሊሶቹ አንዱ ዕድሜያቸው ስንት እንደሆነ ሲጠይቃቸው ” 48 ወይም 49 ቢሆንኝ ነው ስለው አላመነኝም!” ይላሉ እየሳቁ።

ከልጅ ልጃቸው ስቪትላና ጋር ከመገናኘታቸው በፊት ለተወሰነ እረፍት ወደ መጠለያ ቤት ተወስደው ነበር።

የሊዲያ መንደር በሩሲያ እጅ ወድቃለች

“አያቴ በመምጣቷ በጣም ደስተኛ ነኝ። ለረጅም ጊዜ ስንፈልጋት ነበር” ስትልም ከሊዲያ አጠገብ ተቀምጣ ተናግራለች።

ሊዲያ “ይህንን ሁለተኛ አልደግመውም” ሲሉ ስለአስገራሚ ጉዟቸው ነግረዋታል።

ስቪትላና “ሁለተኛ እንዳትደግሚው” ስትል አስረግጣ መልሳላቸዋለች።