ቲክቶክ

ከ 5 ሰአት በፊት

በዩናይትድ ስቴትስ ኮንግረስ በኩል የጸደቀው ረቂቅ ሕግ ቲክ ቶክን በአሜሪካ ውስጥ የሚያግድ መሆኑን የተቃወችው ቻይና ውሳኔውንም ፍትሃዊ አይደለም ብላዋለች።

ባለፉት ዓመታትም በቻይና ኩባንያ ባለቤትነት የተያዘው መተግበሪያ ከደኅንነት ጋር በተያያዘ የውዝግብ ምክንያት ሲሆን ተደጋግሞ ታይቷል።

በብዙ ምዕራባውያን አገራት ያሉ ባለሥልጣናት፣ ፖለቲከኞች እና የደኅንነት ሠራተኞች እና ሌሎችም ቲክ ቶክን ስልካቸው ላይ እንዳይጭኑት ታግደዋል።

ሦስቱ ዋና ዋና የቲክ ቶክ የሳይበር ስጋቶች ምንድን ናቸው? ኩባንያውስ ምን ምላሽ ሰጠ?

1. ቲክ ቶክ ‘ከልክ ያለፈ’ መረጃ ይሰበስባል

የቲክቶክ መተግበሪያ የሚሰበስበው መረጃ “ከኢንዱስትሪው አሠራር ጋር የተጣጣመ ነው” ብሏል።

ተቺዎች በበኩላቸው ቲክቶክ ከፍተኛ መጠን ያለው መረጃ እየሰበሰበ መሆኑን አንስተው በተደጋጋሚ ወቀሳ ያቀርባሉ። በአውስተራሊያ የሳይበር ኩባንያ ኢንተርኔት2.0 ተመራማሪዎች ከሁለት ዓመት በፊት የታተመውን ሪፖርት እንደ ማስረጃ ይጠቀሳሉ።

ተመራማሪዎቹ የመተግበሪያውን ኮድ አጥንተው “ከመጠን ያለፈ መረጃ እንደሚሰበስብ” ዘግበዋል። ተጠቃሚዎች የት አካባቢ እንዳሉ፣ በምን ዓይነት ስልክ ወይም ኮምፒውተር እንደሚጠቀሙ እና ምን ዓይነት ሌሎች መተግበሪያዎችን እንደጫኑ ዝርዝር መረጃ ይሰበስባል ብለዋል።

ሲቲዝን ላብም ተመሳሳይ ጥናት አድርጓል። “ከሌሎች ታዋቂ የማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎች ጋር ሲወዳደር ቲክ ቶክ የተጠቃሚን ባህሪ ለመከታተል ተመሳሳይ መረጃ ዎችን ይሰበስባል” ሲል ደምድሟል።

የጆርጂያ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ባለፈው ዓመት ባወጣው ዘገባ “ዋናው ቁም ነገር እንደ አብዛኞቹ የማኅበራዊ ሚዲያ እና የሞባይል መተግበሪያዎች ተመሳሳይ ነገር ያደርጋሉ” ብሏል።

2. ቲክ ቶክን ተጠቅሞ የቻይና መንግሥት ሊሰልል ይችላል

ኩባንያው ሙሉ በሙሉ ራሱን የቻለ መሆኑን ቲክ ቶክ ይገልጻል። “የተጠቃሚ መረጃን ለቻይና መንግሥት አላቀረብንም፤ ብንጠየቅም አንሰጥም” ብሏል።

ምንም እንኳን የግላዊ መረጃ ባለሙያዎችን ቢያበሳጭም አብዛኞቻችን ከማኅበራዊ ሚዲያ አውታሮች ጋር የግል መረጃን የማስተላለፍ ስምምነትን እንቀበላለን።

አገልግሎታቸውን በነጻ እንዲሰጡን ስለእኛ መረጃ ይሰበስባሉ። ይህንንም በመድረኮቻቸው ላይ ማስታወቂያዎችን ለመሸጥ ይጠቀሙበታል ወይም ሌላ ቦታ ማስታወቂያ ሊያቀርቡልን ለሚሞክሩ ድርጅቶች መረጃችንን ይሸጣሉ።

የቲክ ቶክ ባለቤት ባይት ዳንስ ሲሆን፣ መቀመጫውንም ቤይጂንግ ላይ ያደረገ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ነው።

ይህም አሜሪካዊ ያልሆነ ዋና መተግበሪያ ነው። ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ስናፕቻት እና ዩቲዩብን እንደ ምሳሌ ካነሳን ደግሞ ሁሉም ተመሳሳይ መጠን ያለው ዳታ ይሰበስባሉ፤ ኩባንያዎቹ ደግሞ የአሜሪካ ናቸው።

የአሜሪካ ሕግ አውጪዎችም ሆኑ የሌሎች አገራት በእነዚህ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሰበሰቡ መረጃዎች ብሔራዊ ደኅንነትን አደጋ ላይ ሊጥሉ ለሚችሉ መጥፎ ጥቅሞች ሊውሉ አይገባም የሚል አንድ ሃሳብ ላይ ደርሰዋል።

እአአ በ2020 ዶናልድ ትራምፕ ባስተላለፉት ውሳኔ የቲክ ቶክ መረጃ አሰባሰብ ቻይና “የፌዴራል ሠራተኞችን እና ተቀጣሪዎችን እንድትከታተል፣ የግል መረጃን ለማጥመድ እና የድርጅት ስለላ እንድትሠራ” ሊፈቅድላት ይችላል ብለዋል።

የቲክ ቶክ ባለቤት ባይት ዳንስ
የምስሉ መግለጫ,የቲክ ቶክ ባለቤት ባይት ዳንስ

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ይህ ንድፈ ሃሳባዊ ስጋት ብቻ ሆኖ እስካሁን ዘልቋል። በ2017 በወጣው ግልጽ ያልሆነው የቻይና ሕግ ግን ፍርሃትን ቀስቀሷል።

በቻይና ብሔራዊ መረጃ ሕግ አንቀጽ 7 መሠረት ሁሉም የቻይና ድርጅቶች እና ዜጎች የአገሪቱን የስለላ ጥረት “መደገፍ፣ መርዳት እና መተባበር” አለባቸው ይላል።

ይህ ሕግ ቲክ ቶክን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የቻይና ኩባንያዎች በሚጠራጠሩ ሰዎች ተደጋግሞ ይጠቀሳል።

የጆርጂያ የቴክኖሎጂ ተቋም ተመራማሪዎች ግን ሕጉ ከአውድ ውጪ የተወሰደ ነው ብለው ይከራከራሉ። ሕጉ የተጠቃሚዎችን እና የግል ኩባንያዎችን መብት የሚጠብቁ አንቀጾችንም እንደሚያካትት ልብ ማለት ያስፈልጋል ብለዋል።

የቲክ ቶክ ሥራ አስፈጻሚዎች ከ2020 ጀምሮ ቻይናውያን ሠራተኞች ቻይናውያን ያልሆኑ ተጠቃሚዎችን መረጃ ማግኘት እንደማይችሉ ደጋግመው ገልጸዋል።

እአአአ በ2022 ግን ባይት ዳንስ አንድ ጉዳይ አምኗል። ቤይጂንግ የከተሙ በርካታ ሠራተኞቹ በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ ቢያንስ ሁለት ጋዜጠኞችን መረጃ ሲከታተሉ ነበር። በዚህም ያሉበትን ቦታ እና ለመገናኛ ብዙኃን መረጃ አሳልፈው በመስጠት የተጠረጠሩትን የቲክ ቶክ ሠራተኞችን ስለማግኘታቸው ሲከታተሉ እንደነበር አምኗል።

በኋላም መረጃውን የተከታተሉት ሠራተኞች ተሰናብተዋል ሲሉ የቲክ ቶክ ቃል አቀባይ ገልጸዋል።

ኩባንያው የተጠቃሚ መረጃ በቻይና ውስጥ ተከማችቶ እንደማያውቅ አስታውቆ፤ ለአሜሪካ የተጠቃሚዎች ቴክሳስ ውስጥ፤ ለአውሮፓ ዜጎች መረጃ ደግሞ ሌሎች ማዕከላትን እየገነባ መሆኑን አጥብቆ ተናግሯል።

የትኛውም የማኅበራዊ ሚዲያ ባላደረገው መንገድ በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ ደግሞ ኩባንያው ገለልተኛ የሳይበር-ደኅንነት ኩባንያ በማቋቋም በአውሮፓ ድረ-ገጾቹ ላይ ሁሉንም የመረጃዎች አጠቃቀምን ይቆጣጠራል።

“የአውሮፓ ተጠቃሚዎቻችን መረጃ በልዩ ሁኔታ በተዘጋጀ አካባቢ የተጠበቀ ነው። መረጃ ሊያገኙ የሚችሉት በገለልተኛው አካል ማረጋገጫ የሚሰጣቸው ሠራተኞች ብቻ ናቸው” ብሏል።

3. ቲክ ቶክ ‘አስተሳሰብ ለማስቀየር’ ሊውል ይችላል

የማኅበረሰቡ መመሪያዎች “በማኅበረሰባችን ወይም በሕዝብ ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ የተሳሳቱ መረጃዎችን ይከለክላሉ። ይህም ትክክለኛ ያልሆነ ባህሪን ያካትታል” ሲል ቲክ ቶክ ተከራክሯል።

የፌደራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ዳይሬክተር የሆኑት ክሪስቶፈር ራይ እአአ በ2022 ለአሜሪካ ሕግ አውጪዎች “የቻይና መንግሥት… ለተጽእኖ ፈጠራ ሥራዎች ጥቅም ላይ ሊውል ስለሚችል የሚቆጣጠረው ክፍል አለ” ሲሉ ገልጸዋል።

በቻይና ውስጥ ብቻ የሚገኘው የቲክ ቶክ እህት መተግበሪያ ዱይን በከፍተኛ ሁኔታ ሳንሱር የተደረገበት ሲሆን፣ ትምህርታዊ እና ጤናማ ጉዳዮችን ብቻ ለወጣት ተጠቃሚዎች በስፋት እንዲሰራጩበት ማበረታታቱ ስጋቶቹን የበለጠ ከፍ አድርጓል።

ሁሉም ማኅበራዊ ሚዲያዎች ቻይና ውስጥ ከፍተኛ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል። የኢንተርኔት ፖሊስ ሠራዊት አባላት መንግሥትን የሚተች ወይም የፖለቲካ አለመረጋጋትን የሚያነሳሳ ይዘትን ይሰርዛል።

ቲክ ቶክ ወደ ሕዝቡ በደረሰበት ሰሞን በመተግበሪያው ላይ ከፍተኛ ሳንሱር ነበር። በአሜሪካ የምትኖር ተጠቃሚ ቤይጂንግ በዢንጂያንግ ሙስሊሞች ላይ ስላላት አያያዝ በመናገሯ አካውንቷ ታግዷል። ከከፋ ተቃውሞ በኋላ ቲክ ቶክ ይቅርታ ጠይቆ አካውነቷን መልሶታል።

የሲቲዝን ላብ ተመራማሪዎች የቲክ ቶክን እና የዱይንን አነጻጽረዋል። ቲክ ቶክ ተመሳሳይ ፖለቲካዊ ሳንሱር አይተገብርም ብለው ደምድመዋል።

ተመራማሪዎች በ2021 እንዳሉት ከሆነ “መድረኩ ግልጽ የሆነ ድኅረ ሳንሱርን አስገዳጅ አላደረገም” ብለዋል።

የጆርጂያ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች እንደ የታይዋን ነጻነት ወይም በቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ላይ የተሰነዘሩ ቀልዶችን እና መሰል ርዕሰ ጉዳዮችን ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ፈልገዋል።

“በሁሉም ዘርፍ ውስጥ ያሉ ቪዲዮዎች በቲክ ቶክ ላይ በቀላሉ ይገኛሉ። ብዙዎቹም ታዋቂ እና በሰፊው የሚጋሩ ናቸው” ሲሉ ደምድመዋል።

ቲክቶክ

ንድፈ ሃሳባዊ አደጋ

አጠቃላይ ሥዕሉ እንግዲህ ከንድፈ ሃሳባዊ ፍርሃት እና ንድፈ ሃሳባዊ ስጋት ጋር የተቆራኘ ነው።

ተቺዎች ቲክ ቶክ “በአደጋ ወቅት የሚመዘዝ ነው” ብለው ይከራከራሉ። ምንም ጉዳት የሌለው ቢመስልም በግጭት ጊዜ ግን ኃይለኛ መሳሪያ ሊሆን ይችላል ሲሉ በምሳሌ ይጠቅሳሉ።

መተግበሪያው በሕንድ ውስጥ ታግዷል። አገሪቱ በ2020 በመተግበሪያው እና በሌሎች በርካታ የቻይና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እርምጃ ወስዳለች።

የአሜሪካ እገዳ ግን ተልቅ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል። ምክንያት ከተባለ ደግሞ የአሜሪካ አጋሮች ብዙውን ጊዜ ከዋሽንግተን ጋር ተመሳሳይ ውሳኔዎችን አብረው ስለሚወስዱ ነው።

ለምሳሌም አሜሪካ የቻይናውን ግዙፍ የቴሌኮም ኩባንያ ሁዋዌን በ5ጂ መሠረተ ልማት ውስጥ እንዳይሠማራ ስታግድ ሌሎች አገራትም ተከትለዋታል። ይህ ግን የተጨበጠ ስጋት ላይ ተመሥርቶ የተወሰደ እርምጃ አልነበረም።

እነዚህ አደጋዎች የአንድ አካል ብቻ መሆናቸው ልብ ሊባል ይገባል። ቻይና ስለአሜሪካ መተግበሪያዎች መጨነቅ የለባትም። ምክንያቱም መተግበሪያዎቹ የቻይና ዜጎች ጋር እንዳይደርሱ ከታገዱ ዓመታትን አስቆጥረዋል።