
ከ 5 ሰአት በፊት
ካሜሩናዊቷ ሳይንቲስት ሜሪ ማኩዋቴ ከሳተላይት የሚገኝ መረጃን በመጠቀም በአደጋ ጊዜ ሰዎችን ለማዳን በሚደረገው ሩጫ ቀዳሚ ከሚባሉት አንዷ ናት።
ነገር ግን የአፍሪካ አገራት የራሳቸውን የሕዋ ምርምር ጣቢያ ማቋቋም አለባቸው ስትል ትሞግታለች።
ባለፈው መስከረም ማዕከላዊ ሞሮኮ በርዕደ-መሬት ስትመታ የ32 ዓመቷ ሳይንቲስት ስልክ በተደጋጋሚ መጥራት ጀመረ።
ምንም እንኳ እሷ የምትገኘው ከአደጋው ሥፍራ በሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቃ ቢሆንም፣ የሳተላይት ምሥል ተመልክታ የመተንተን ብቃቷ ተፈላጊ አድርጓታል።
“በሞሮኮ ተፈጥሯዊ አደጋ እንደደረሰ የሚጠቁሙ መልዕክቶች ከሥራ ባልደረቦቼ ሲደርሰኝ ነው ከእንቅልፌ የነቃሁት” ስትል ለቢቢሲ ትናገራለች።
ማኩዋቴ የምትገኘው በካሜሩን ዋና ከተማ ያውንዴ ነው።

መንግሥታዊ ላልሆነው ‘ሂዩማኒቴሪያን ኦፕንስትቲትማፕ ቲም’ የተሰኘ ድርጅት የጂዮስፓሻል ባለሙያ ሆና የምታገለግለው ማኩዋቴ ለአደጋ ጊዜ አገልግሎት ሰጪዎች መረጃ በማቀበል እገዛ ታደርጋለች።
ዓላማ እና መነቃቃተ የሚሰጠኝ ሥራ ነው ስትል ማኩዋቴ ትናገራለች።
“የሞሮኮውን አደጋ ስሰማ በጣም ደንግጬ ነበር። ነገር ግን አስፈላጊ የሚባሉ ካርታዎችን መዘረጋት ከቻልኩ የተወሰኑ ሰዎችን ሕይወት መታደግ እንደምችል አሰብኩ።”
ባለፈው መስከረም እንደ ድንበር አልባው የሐኪሞች ቡድን ያሉ እርዳታ ሰጪ ተቋማት እሷ ባዘጋጀችው ካርታ ተጠቅመው ማራካሽ እና ሌሎችም አካባቢዎች ያሉ ሰዎችን መድረስ ችለዋል።
የምትሠራው ካርታ ለሕዝቡ ክፍት ሆነው በይነ-መረብ ላይ ከተቀመጡ ምሥሎች የተውጣጣ ነው።
- ኢትዮጵያ ወደ ሕዋ የላከቻቸው ሳተላይቶች ሥራ ማቆማቸው ተገለጸ24 ጥቅምት 2023
- ጨረቃ ላይ ውሃ የሚፈልገው ዶ/ር ብርሃኑ ቡልቻ ማን ነው? ጨረቃስ ‘ሁለተኛ ቤታችን’ ትሆናለች?19 መስከረም 2022
- የህዋ ሕክምና ምርጥ ተማሪ ተብሎ የተሸለመው ኢትዮጵያዊው የቀድሞ አየር ኃይል አባል24 ሀምሌ 2023
ማኩዋቴ የምትሠራው ካርታ የዘርፉ ሰዎች ያልሆኑ በተለምዶ ከምናውቀው ዓይነት ካርታ በጣም ለየት ያለ ነው።
ካርታዎቹ በጣም ጥራት ያላቸው ሁሉንም ነገር በዝርዝር የሚያሳዩ ሆነው እሷ እና የሥራ ባልደረቦቿ ሕይወት አድን መረጃዎች ያካተቱባቸው ናቸው።
“በአደጋ ጊዜ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የሚፈልጉት መረጃ መንገዱ የት ነው፣ ወሃ ያለው የት ነው፣ ወንዝ አሊያም ገበያ ያለው የት ነው የሚለውን ነው” ትላለች።
ቢሆንም ሳተላይት ወደ ሕዋ ማምጠቅም ሆነ የሳተላይት ጣቢያ ማስተዳደር ዋጋው ከፍተኛ በመሆኑ የጂኦስፓሻል ባለሙያዎች የሚጠቀሙት ምሥል ዋጋ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል።
በለተይ ደግሞ የተፈጥሮ አደጋ በሚደርስበት ጊዜ እንዲያቀርቡ የሚጠየቁት ምሥል በአጭር ጊዜ መድረስ ስላለበት ዋጋው የበለጠ ከፍ ይላል።
“አደጋ ሲከሰት የሳተላይት አቅራቢ ደርጀቶችን የምንጠይቀው የትኛው ድርጀት ነው ጥራት ያላቸውን ምሥሎች በነፃ የሚያቀርበው ብለን ነው።”
አንዳንድ የሳተላይት ኩባንያዎች ለአደጋ ጊዜ ምሥሎችን በነፃ የሚያቀርቡ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ይህ ሲሆን፣ አይታይም።
“ለምሳሌ የሞሮኮው አደጋ ሲደርስ የነበረን ምስል የተወሰኑ ሥፍራዎችን ብቻ የሚያሳይ ነው። በዚያ ላይ ከጨረስን በኋላ እነዚህን ምሥሎች ማግኘት አንችልም።”

ሞሮኮ የራሷ ሳተላይት አላት። ማኩዋቴ በርካታ የአፍሪካ አገራት የራሳቸውን ሳተላይት ወደ ጠፈር እንዲያመጥቁ ትመክራለች። ይህ ከሆነ ሥራችን ይቀላል የሚል መልዕክት አላት።
የሳተላይት ምሥሎች ለአደጋ ጊዜ ብቻ አይደለም የሚጠቅሙት። የሳተላይት ምሥሎች ለግብርና፣ የሕዝብ ቁጥር ለውጥን ለመተነተን እንዲሁም እንደ ውሃ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመቆጣጠር ይረዳሉ።
“አንድ አገር የራሷ ሳተላይት አላት ማለት ለምጅሎች አትከፈልም ማለት ነው” ትላለች ወጣቷ ሳይንቲስት።
አንድ የሳተላይት ምሥል በስኩዌር ኪሎ ሜትር እስከ 25 ዶላር ይሸጣል። ለምሳሌ የሌጎስን ጥራቱን የጠበቀ የሳተላይት ምስል ለማግኘት 80 ሺህ ዶላር ሊጠይቅ ይችላል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኒውስፔስ አፍሪካ ኮንፈረንስ በአንጎላዋ ዋና ከተማ ሉዋንዳ ተካሂዷል። ማኩዋቴ በሥፍራው ለተሰበሰቡ የዘርፉ ባለሙያዎች ፓን-አፍሪካን ትብብር ያስፈልጋል የሚል መልዕክት ስታስተላልፍ ነበር።
ስብሰባው ኢንቨስተሮች እና ባለሙያዎች የሕዋ ቴክኖሎጂ አህጉሪቱን እንዴት ሊጠቅማት ይችላል የሚለውን ሐሳብ የሚያንሸራሽሩበት ነው።
ስፔስ ኢን አፍሪካ የተሰኘው አማካሪ ተቋም እንደሚለው የአፍሪካ ሕዋ ኢንዱስትሪ በአውሮፓውያኑ 2026 20 ቢሊዮን ዶላር ሊያወጣ ይችላል ይላል።
ነገር ግን ከዚህ ገንዘብ አብዛኛው የሚመጣው አገልግሎታቸውን ለአፍሪካ ከሚሸጡ የውጭ ኩባንያዎች ነው።
“እስቲ አስቡት 10 በመቶውን ወስደን የአፍሪካ ኩባንያዎች ላይ መዋዕለ-ንዋይ ብናፈስ” የሚሉት የአንጎላ ብሔራዊ ሕዋ ፕሮግራም ኃላፊ ዶ/ር ዞላና ጃዎ ናቸው።
ኃላፊው ልክ እንደ ማኩዋቴ የአፍሪካ አገራት አስተማማኝ የሆነ መረጃ ለማግኘት የሳተላይት ዘርፉ ላይ ማተኮር አለባቸው ይላሉ።
ደቡብ አፍሪካ እና ግብፅ በርካታ ሳተላይት ወደ ጠፈር የላኩ የአፍሪካ አገራት ናቸው። ሁለቱም አገራት እያንዳንዳቸው 13 ሳተላይቶችን አምጥቀዋል።
ደቡብ አፍሪካ ሳተላይቷን የምትጠቀመው የማዕድን ማውጣት ሂደትን ለመቆጣጠር እና የማይቆራረጥ ኢንተርኔት እና የስልክ አገልግሎት ለመስጠት እንደሆነ ማኩዋቴ ትናገራለች።
ግብፅ ደግሞ የቴሌኮሚዩኒኬሽን ሳተላይቶች ማምጠቋ ከአረብ አገራት የሚድያ ፈርጥ ሆና መገኘት እንደምትፈልግ የሚያሳይ ነው።
ከኢንቨስትመንት ባለፈ ለአፍሪካ ሕዋ ዘርፍ ትልቁ ማነቆ የሆነው ጉዳይ ትምህርት ነው።
“አሱ ነው በጣም እየጎዳን ያለው” ይላሉ ዶ/ር ጃዎ። ማኩዋቴ ደግሞ ቀጣዩ ሕልሟ ይህንን ጉዳይ መዳሰስ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2019 ከናይጄሪያው አፍሪካን ሪጅናል ሴንተር ፎር ስፔስ ሳይንስ ኤንድ ቴክኖሎጂ በጆዮማቲክስ ማስተርስ ዲግሪዋን አግኝታለች።
“ይህ ፕሮግራም ካሜሩን ውስጥ የለም። ለዚህ ነው ከናይጄሪያ ስመለስ ሁሉም ሰው ይህን እንዲያውቀው የፈለግኩት” ትላለች።
ነገር ግን ይህን ትምህርት በምትወስድ ጊዜ ያስተዋለችው ሌላ ነገር በሳይንሱ ዘርፍ ያሉ አፍሪካዊ ሴቶች ቁጥር አናሳ መሆኑን ነው።
“ክፍሉ ውስጥ ከነበርነው 35 ተማሪዎች ሴቶቹ ሦስት ብቻ ነበርን። ከዚያ በፊት አንድ ወይም ሁለት ሴቶች ነበሩ።”