ቀሲስ በላይ መኮንን

2 ግንቦት 2024, 13:48 EAT

በሐሰተኛ ሰነድ ከአፍሪካ ኅብረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት ገንዘብ ለማውጣት በመሞከር የተጠረጠሩት ቀሲስ በላይ መኮንን እና ሌሎች ሁለት ተጠርጣሪዎች ላይ የክስ መመሥረቻ 15 ቀናት በፍርድ ቤት መፈቀዱን ጠበቃ አቶ ቱሊ ባይሳ ለቢቢሲ ተናገሩ።

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው ዛሬ ሐሙስ 24/ 2016 ዓ. ም. ረፋድ ላይ በነበረው የፍርድ ቤት ውሎው ነው።

ቀሲስ በላይ እንዲሁም አብረው በቁጥጥር ሥር የዋሉት አጃቢያቸው እና ሹፌራቸው ዛሬ ለሦስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት፤ ባለፈው ሳምንት በነበረው ችሎት ፍርድ ቤቱ ለመርማሪ ፖሊስ ስምንት ተጨማሪ የምርመራ ቀናት በመፍቀዱ ነው።

እነ ቀሲስ በላይ የተጠረጠሩት በአፍሪካ ኅብረት ስም የተዘጋጀ ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀም በኅብረቱ ዋና መሥሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርጫፍ ስድስት ሚሊዮን 50 ሺህ ዶላር ለማውጣት ሞክረዋል በሚል ነው።

ባለፈው ሳምንት በነበረው ችሎት መርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ ቀናት የተፈቀደለት ቀሲስ በላይ ቤት ውስጥ ባደረገው ብርበራ ያገኘው ሽጉጥ ፈቃድ ያለው ስለመሆኑ ለማጣራት፣ ሌሎች ስድስት ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ እንዲሁም ለባንክ እና “ለተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች” ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ ለመጠበቅ በሚል ነበር።

በዛሬው ችሎት ላይ መርማሪ ፖሊስ የሚያደርገውን ምርመራ እንዳጠናቀቀ ለፍርድ ቤቱ መግለጹን የቀሲስ በላይ ጠበቃ አቶ ቱሊ ተናግረዋል።

ከዐቃቤ ሕግ ጋር አብሮ የቀረበው መርማሪ ፖሊስ፤ ዐቃቤ ሕግ ክስ መመሥረቻ ተጨማሪ ቀናት እንደሚያስፈልገው ለፍርድ ቤቱ ደብዳቤ መጻፉን እንደጠቀሰ ጠበቃው አስረድተዋል።

ዐቃቤ ሕግ በደብዳቤው፤ “ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበት ወንጀል በሐሰተኛ ሰነድ መገልገል እና የሙስና ወንጀል ስለሆነ ክስ እስከሚመሠረት 15 ቀን የክስ መመሥረቻ ጊዜ እንዲሰጠኝ” ብሎ መጠየቁ እንደተገለጸም አቶ ቱሊ ተናግረዋል።

ዐቃቤ ሕግ በደብዳቤው እነ ቀሲስ በላይ የተጠረጠሩት “በሐሰተኛ ሰነድ በመገልገል፣ የሙስና ወንጅል በመፈጸም እና በከባድ አታላይነት” እንደሆነ መጥቀሱን የሚናገሩት ጠበቃው፤ ተጨማሪ ቀናት እንዲፈቀድ የጠየቀው እነዚህ ድርጊቶች “በየትኛው አንቀጽ ሥር ይወድቃሉ የሚለውን በደንብ አጣርቶ ክስ ለለመሥረት” እንደሆነ ዐቃቤ ሕግ መግለጹን አስረድተዋል።

በተጨማሪም ክስ እስከሚመሠረት ድረስ ተጠርጣሪዎቹ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥ መጠየቁን አክለዋል።

ለፍርድ ቤቱ የቀረበውን ጥያቄ የተቃወሙት የተከሳሽ ጠበቃዎች በበኩላቸው፤ ተጨማሪ ቀን መፈቀድ እንደሌለበት አንስተው መከራከራቸውን አንስተዋል።

አቶ ቱሊ እንደሚያስረዱት በጠበቆች በኩል የተነሳነው አንዱ መከራከሪያ በዐቃቤ ሕግ ደብዳቤ ላይ የተጠቀሰው “የሙስና ወንጀል በመፈጸም” የሚለውን የተመለከተ ነው።

ጠበቆች፤ “ደንበኞቻችን እስካሁን ድረስ የተመረመሩት በሙስና ወንጀል አይደለም፤ ሐሰተኛ ሰነድ መገልገል የሚል ብቻ ነበር” በማለት እንደተከራከሩ አቶ ቱሊ ተናግረዋል።

ጠበቆች፤ “ተሞከረ የተባለው ነገር በራሱ የሙስና ወንጀልን የሚያቋቁም ነገር አይደለም። ከሙስና ጋር የሚገናኝ ነገር አይደለም። ምክንያቱም ደንበኞቻችን የመንግስት ባለሥልጣን አይደሉም፣ ሙከራ ተደርጎበታል የተባለውም የአፍሪካ ኅብረት ገንዘብ እንጂ የመንግሥት አይደለም” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውን ጠቅሰዋል።

ሐሰተኛ ሰነድ መገልገል የሚለውን በተመለከተም “ደንበኞቻችን ሰነዱ ላይ የፈረሙት ነገር የለም፣ ሰነዱም ላይ እነሱን የሚጠቅስ ምንም ነገር የለም” የሚል መከራከሪያ መቅረቡን አቶ ቱሊ ተናግረዋል።

ጠበቆች፤ “ሙስና ተብሎ የመጣው አስተያየት ደንበኞቻችን የዋስትና መብት እንዳያገኙ ለማስከልከል ስለሆነ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብት ፈቅዱ [ተጠርጣሪዎች] ውጪ ሆነው፣ ክስ የሚያሥመሰርት ነገር ካለ ዐቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሠርት ካልሆነም እንዲዘጋልን” ሲሉ ፍርድ ቤቱ መጠየቃቸውን አክለዋል።

የሙስና ወንጀልን በተመለከተ ከጠበቆች በኩል ለተነሳው መከራከሪያ ምላሽ የሰጠው ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ፤ ገንዘብ የማውጣት ሙከራ የተደረገው የመንግሥት የልማት ድርጅት በሆነው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ እንደነበረ አንስቷል ተብሏል።

ዐቃቤ ሕግ፤ “[ገንዘቡ] ወጥቶ ቢሆን ኖሮ፤ መልሶ የሚከፍለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስለሆነ ተታላይ ወይም ተጎጂ የሚሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው” ማለቱን ጠበቃው ገልጸዋል።

የዐቃቤ ሕግ እና የተከሳሽ ጠበቆችን ክርክር ያዳመጠው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ ዐቃቤ ሕግ የጠየቀውን 15 የክስ መመሥረቻ ቀናት መፍቀዱን ጠበቃው አቶ ቱሊ ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ. ም. ባወጣውና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንቱ ሊወጣ የነበረው ስድስት ሚሊዮን ዶላር ሳይሳካ መቅረቱን በገለጸበት መግለጫ፣ ጉዳዩን “ከፍተኛ ሥፍራ ሰጥቶ” እየተከታተለው እንደሆነ ገልጿል።

አክሎም፣ ሚያዝያ 7 ቀን 2016 ዓ. ም. “የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኛ ባልሆነ አካል የክፍያ ትዕዛዞች ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ” እንደገቡና “ከግንባታና የውሃ ቁፋሮ ሥራ” ጋር ለተያያዘ ክፍያ በሚል ገንዘቡ ሊወጣ እንደነበር ገልጿል።