ኒካ ሻካራሚ

ከ 3 ሰአት በፊት

የኢራን የጸጥታ ኃይል አባላት የሆኑ ግለሰቦች የ16 ዓመቷን የመንግሥት ተቃዋሚ ታዳጊ ወሲባዊ ጥቃት ፈጽመው እንደገደሏት ቢቢሲ በምርመራ ዘገባ ማውጣቱን ተከትሎ ኢራን በጋዜጠኞች እና ተሟጋቾች ላይ ክስ መሰረተች።

ክስ የተመሰረተባቸው ግለሰቦች ቢቢሲ በአውሮፓውያኑ 2022 ህይወቷ ባለፈው ኒካ ሻካራሚ ግድያን አስመልክቶ ለሰራው ዘገባ ያናገራቸው ጋዜጠኞች ተካትተውበታል።

በኢራን የፍትህ አካል የሚተዳደረው ሚዛን የተሰኘው የዜና ወኪል የታዳጊዋን ግድያ አስመልክቶ ቢቢሲ አይ የሰራውን የምርመራ ዘገባ “ሃሰተኛ፣ ትክክል ያልሆነ እና በበርካታ ስህተቶች” የተሞላ ሲል ገልጾታል።

የኢራን የፍትህ ሚኒስቴር ክስ የመሰረተባቸውን ጋዜጠኞች እና ተሟጋቾች “የህብረተሰቡን ስነ ልቦናዊ ደኅንነት እያናጉ” ነው ብሎ ቢፈርጃቸውም ማንነታቸውን ግን ግልጽ አላደረገም።

ነገር ግን ቢቢሲ በሰራው ዘገባ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ሁለት ኢራናውያን ጋዜጠኞች አቃቤ ህግ ክስ እንደከፈተባቸው ተናግረዋል።

መሐመድ ፓርሲ የተባለው ጋዜጠኛ የቴህራን አቃቤ ህግ ቢሮ “ስለ ኒካ ሻካራሚ እና ስለ አገዳደሏ ዝርዝር መረጃዎችን” የያዘ ዘገባ በማውጣት ክስ እንደመሰረተበት በኤክስ ገጹ አስፍሯል።

ሌላኛው ጋዜጠኛ ማርዚይ ማህሙዲ በበኩሉ “ክሱም ሆነ ዝርዝሮቹ አይታወቁም” ሲል አጋርቷል።

የኢራን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ቫሂዲ የቢቢሲ የምርመራ ግኝቶችን የኢራን ጠላቶች ሴራ ሲሉ ያጣጣሉ ሲሆን በዚህም በይፋ አስተያየት የሰጡ የመጀመሪያው ባለስልጣን ሆነዋል።

“ጠላቶች እና አጋር ሚዲያዎች በስነ ልቦና ለማሸነፍ ሃሰተኛ እና የማይጨበጡ ዘገባዎችን እየሰሩ ነው” ሲሉ ሚኒስትሩ ከምክር ቤት ስብሰባ ወጥተው ለጋዜጠኞች መግለጻቸውን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ሚኒስትሩ ዘገባውን በአሜሪካ ውስጥ እየተቀጣጠለ ያለው የፍልስጤም ደጋፊዎች ተቃውሞ እንዲሁም ኢራን ባለፈው ወር ላይ ካደረሰችው የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃትን በተመለከተ ትኩረትን ለማስቀልበስ የተደረገ ሙከራ ነው ሲሉም ተችተዋል።

ሚኒስትሩም ሆነ የኢራን የፍትህ አካላት በሰጡት መግለጫዎች ቢቢሲ የሰጠው አስተያየት የለም።

ኒካ ሻካራሚ የተሰኝችው ታዳጊ ከሁለት ዓመት በፊት የኢራንን መንግሥት ያስደነገጠው “ሴት፣ ህይወት፣ ነጻነት” የተሰኘው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ምልክት ሆና ነበር።

ለዚህ ብሔራዊ ተቃውሞ መቀስቀስ መነሻ የሆነው ሂጃብሽን በአግባቡ አልለበሽም በሚል ማህሳ አሚኒ የተባለች የ22 ዓመት ሴት በኢራን ስነ ምግባር ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውላ ህይወቷ ማለፉን ተከትሎ ነው።

ይህንንም ተከትሎ ታዳጊዋ በቴህራን በተካሄደ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ሂጃብዋን በእሳት ስታቃጥል እንዲሁም ሌሎች ተቃዋሚዎች ደግሞ “ሞት ለአምባገነኑ” እያሉ ሲዘምሩ ነበር።

ማምሻውን ለጓደኛዋ የደህንንት ኃይሎች እየተከታተሏት እንደሆነ ከተናገረች በኋላ ጠፋች። ከጠፋች ከሳምንት በኋላ ቤተሰቧ አስከሬኗን በሬሳ ማቆያ ውስጥ አገኙት። ጭንቅላቷ እንደተደበደበ ቤተሰቦቿ ገልጸው ባለስልጣናቱ ከህንጻ ጣሪያ በመዝለል ራሷን አጥፍታለች የሚለውን አስተያየት ውድቅ አድርገዋል።

ቢቢሲ በቅርቡ ያወጣው የምርመራ ዘገባ የእስላማዊ የአብዮት ጥበቃ ጓድ የኒካ ክስ ችሎት አስመልክቶ ያቀረባባትን ክስ የያዘ ሾልኮ የወጣ ሰነድ መሰረት አድርጎ ነው።

በዚህ ሾልኮ በወጣው ሰነድ መሰረት ታዳጊዋ የአብዮት ጥበቃ ባሰማራቸው ልዩ ኃይል ተይዛ እንደነበር አካቷል። የልዩ ኃይሉ አባላት በአንድ መኪና ውስጥ ይዘዋት በነበረባት ወቅት ያደረሱባትን ነገሮች ዝርዝር ይህ ሰነድ ይዟል።

ከነዚህም መካከል አንደኛው ግለሰብ በላይዋ ላይ ተቀምጦ እንደነበር እና እንደደፈራት፣ እጇ ቢታሰርም እንደታገለቻቸቸው፣ በዚህም የተነሳ እስከትሞት ድረስ በቆመጥ ዱላ እንደበደቧት እና በመጨረሻም የጥበቃ ጓዱ አስከሬኗን እንዲጥሉት ትዕዛዝ መተላለፉን ዝርዝር ይዟል።