
ከ 5 ሰአት በፊት
በቅርቡ ከቬትናም የተሰማው የወንጀል ታሪክ ብዙዎችን ያነጋገረ ነው።
ቬትናማዊት ቢሊየነር ቾንግ ሚ ላን ተሰምቶ በማይታቅ ሁኔታ በ44 ቢሊዮን ዶላር የማጭበርበር ወንጀል ጥፋተኛ ተባለ ሞት ተፈርዶባታል።
ብዙዎችን ያስደነቀው የተላለፈባት የሞት ፍርድ ሳይሆን፣ እንዴት 44 ቢሊዮን ዶላር ማጭበርበር ይቻላል የሚለው ነበር።
ቼንግ ሚላን ይህ የኢትዮጵያን የሦስት ዓመት በጀት ሊሆን የሚችል ገንዘብ ማጭበርበር የቻለችው በ11 ዓመታት ውስጥ ሴይጎን ኮሜርሻል ከሚባል ባንክ በብድር መልክ በመውሰድ ነው።
ዐቃቤ ሕግ ተከሳሿ ካጨበረበረችው ገንዘብ መካከል 27 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነውን መልሶ ማግኘት የሚቻል አይሆንም ብሏል።
አስር የተለያዩ የቬትናም ግዛት ዐቃቢያ ሕጎች እና ከ200 በላይ ጠበቆች በተሳተፉበት የክስ ሂደት ከ2 ሺህ 700 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደርገዋል።
ስድስት ሺህ ኪሎ ግራም የሚመዝን ማስረጃ በ104 ሳጥኖች ተሰድረው ፍርድ ቤት ቀርበውባታል።
በ67 ዓመቷ ሴት በተከፈተው የክስ መዝገብ 85 ተከሳሾች አብረው የቀረቡ ሲሆን፣ ሁሉም ተከሳሾች ጥፋተኛ ተብለዋል። አራቱ የዕድሜ ልክ እስራት ሲፈረድባቸው ቀሪዎች ደግሞ ከ3 እስከ 20 ዓመት እስራት ተላልፎባቸዋል።
ለመሆኑ ከቬትናም አልፎ መላው ዓለምን ያነጋገረውን ወንጀል ፈጽማለች ስለተባች የ67 ዓመት ሴቷ ምን ይታወቃል?
ከተራ ነጋዴ ወደ ቢሊየነርነት
መኖሪያቸውን በቬትናም መዲና ካደረጉ ዝቅተኛ ቤተሰብ የተወለደችው ቾንግ ሚ ላን ወደ ቢሊየነርነት የተቀየረችበት መንገድ ብዙዎችን ያስደንቃል።
ግለሰቧ ከወላጅ እናቷ ጋር ገበያ መሃል ዳስ ጥላ ሸቀጥ ነበር የምትነግደው። ከዚያም የፀጉር ውበት መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ወደ መሸጥ ተሸጋገረች።
በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የመንግሥት ለውጥ የፈጠረውን ዕድል ተጠቅማ ከባለሥልጣናት ጋር በጥቅም በመተሳሰር ወደ ሪል ስቴት ንግድ ገባች።
ቾንግ ሚ ላን በ1990 አጋማሽ ቅንጡ መኖሪያ ቤቶችን፣ የገበያ ማዕከላትን እየገነባች በመሸጥ የበርካታ ሆቴሎች እና ምግብ ቤቶች ባለቤት መሆን ቻለች።
በእነዚህ የንግድ ሥራዎቿ ውስጥ ባለቤቷን ጨምሮ የቤተሰብ አባሎቿን በስፋት ታሳትፋለች።
በአሁኑ ወቅት የላን ቤተሰብ በቬትናም ቀዳሚው ባለጸጋ ቤተሰብ ነው።
ከላን የክስ ወንጀል ጋር ተያይዞ ፍርድ ቤት የቀረበች የእህቷ ልጅ 155 የባንክ ብድሮችን ለማግኘት 52 ኩባንያዎችን መመሥረቷን አምና ነበር።
ይሁን እንጂ በሲንጋዮ ንግድ ባንክ ውስጥ የነበራት ተሳትፎ መጨረሻዋን የከፋ አድርጎታል።
- ቬትናማዊቷ ቢሊየነር 44 ቢሊዮን ዶላር በማጭበርበር የሞት ፍርድ ተፈረደባቸው11 ሚያዚያ 2024
- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ ያልመለሱ ደንበኞቹን ፎቶ በቅርንጫፎቹ በር ላይ ይፋ ማድረግ ጀመረ5 ሚያዚያ 2024
- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞቹን ማንነት ይፋ ማውጣቱ እና የሚነሱ ሕጋዊ ጥያቄዎች4 ሚያዚያ 2024
ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው ከሆነ ይህች ሴት በሌሎች አገራት በተለያየ ስም በተከፈቱ ኩባንያዎች ከባንኩ ጠቅላላ ሃብት 90 በመቶ የሚሆነው ለዓመታት ተቆጣጥራ ቆይታለች ይላሉ።
ቾንግ ሚ ላን በባንኩ ውስጥ በነበራት ተሳትፎ ለግል ጥቅሟ 44 ቢሊዮን ዶላር አጭበርብራለች ተብላ የተከሰሰችው።
ባንኩ በእነዚህ ዓመታት ከሰጠው ብድር 93 በመቶ የሚሆነው በግለሰቧ ስም ለተከፈቱ የተለያዩ ኩባንያዎች ነው።
እአአ 2019 ላይ በአንድ አጋጣሚ የግል አሸከርካሪዋ ከባንኩ 180 ትሪሊዮን ዶንግ (የቬትናም ገንዘብ) ወይም 4 ቢሊዮን ዶላር ጥሬ ገንዘብ ከባንኩ ወጪ እንዲያደርግ አዛለች።
ተከሳሿ 2ሺህ ኪሎ ግራም የሚመዝነው ገንዘብ ከባንክ ወጪ አስደርጋ ከመኖሪያ ቤቷ ምድር ቤት ውስጥ አከማችታለች መባሉ የቬትናማውያንን አፍ በእጅ ያስከደነ ነበር።
ሌላኛው የቀረበባት ክስ በተለያየ ስም በከፈተቻቸው ኩባንያች የብድር ጥያቄዎች ፍቃድ እንዲያገኙ በባንኩ ውስጥ ያላትን ተጽእኖ ፈጣሪነት በመጠቀም የራሷን የሆኑ ሰዎች ሥልጣን እንዲይዙ አድርጋለች የሚል ነው።
ቾንግ ሚ ላን የምታቀርባቸው የብድር ጥያቄዎች እንዲፈቀዱ ትዕዛዝ ሲሰጡ ነበሩ የተባሉ የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ከፍተኛ ተቆጣጣሪ የ5 ሚሊዮን ዶላር ጉቦ ተቀብለዋል ተብለው የዕድሜ ልክ እስራት ተበይኖባቸዋል።
“ሕይወቴ ጨለመብኝ”
ቾንግ ሚ ላን ጥፋተኛ ከተባለችበት የማጭበርበር ወንጀል በተጨማሪ ሌላ የቦንድ ማጭበርበር ክስ ገና ይጠብቃታል።
ዕድሜያቸው ከ27 እስከ 60 የሚደርሱ ከ42 ሺህ በላይ ሰዎች በባንኩ በተሸጡ የተጭበረበሩ ቦንዶችን ገዝተዋል።
ከእነዚህ መካከል አንዱ የ48 ዓመቱ ጎልማሳ ዳንግ ትሩንግ ሎንግ ነው።
ይህ ግለሰብ ሴት ልጁን ከአገር ውጪ አስተምሮ ለቁም ነገር ለማብቃት በሚል የትምህር ወጪዋን ለመሸፈን ለሁለት አስርት ዓመታት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ሠርቶ 70 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በቦንድ መልክ ለማጠራቀም ነበር ያለመው።
“ለብቸኛዋ ልጄ ትምህርት ስል ሽርፍራፊ ሳንቲም ስቆጥብ ነው የኖርኩት። አሁን እንደ አዲስ ከምንም መጀመር ይኖርብኛል” በማለት ገንዘቡን መበላቱን ለቢቢሲ ተናግሯል።
ይህ አባት ይህን ያህል ገንዘብ መልሶ ለማግኘት መሥራት የሚያስችለው ጤና እንደሌለለው ይናገራል።
“ሕይወቴ ጨለመብኝ፤ የልጄ ሕልም በአጭር ተቀጨ” ብሏል በሐዘን።
ያልተመለሱ ጥያቄዎች
የቾንግ ሚ ላን የማጭበርበር ወንጀል ሲሰማ የብዙዎች ጥያቄ የነበረው ይህን ያህል መጠን ያለው ገንዘብ የማጭበርበር ወንጀል እንዴት ሳይታወቅ ለዓመታት ዘለቀ የሚለው ነው።
“ግራ አጋብቶኛል” ይላሉ በሲንጋፖር የቬትናም ጥናት ፕሮግራምን የሚመሩት ሊ ሆንግ ሂይፕ።
“ቾንግ ሚ ላን ውድ በሆኑ አካባቢዎች የቤት ግንባታ ልማት ሥራዎቿን ለማካሄድ ሲንጋዮ ንግድ ባንክን እንደግል ድርጅቷ አድርጋ ስትጠቀም መኖሯ ከማንም የተደበቀ አልነበረም” ይላሉ።
ለቬትናም ቅርብ የሆኑት የቀድሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ሠራተኛ ደግሞ የአገሪቱ የባንክ ሴክተር በሙስና የተጨማለቀ ስለሆነ፣ የአገሪቱ ባለሥልጣናትም በጥቅም ስለተሳሰሩ የቾንግ ሚ ላን ሴራ ለዓመታት ሊዘልቅ ችሏል ይላሉ።