አዲሱ የ3ዲ ሞዴል

ከ 5 ሰአት በፊት

ከዛሬ 75 ሺህ ዓመታት በፊት ከነበሩ የቅርብ ዘመዶቻችን አንዱን በአካለ ሥጋ ብናገኘው ምን ይመስል ይሆን?

የሳይንስ ሊቃውንት የኒያንደርታል ሴት በህይወት እያለች ምን እንደምትመስል የሚያሳይ አስደናቂ ምስል አዘጋጅተዋል።

መሠረት ያደረጉት ደግሞ በቁፋሮ የተገኘ ለስላሳ አጥንት ላይ ነው።

ተመራማሪዎች አጥንቶቹን እንደገና ከመገጣጠማቸው በፊት ማጠናከር ነበረባቸው።

በኋላም ባለሙያዎች ልዩ የ3ዲ ሞዴል ለማዘጋጀት በቁ።

ሞዴሌ ቢቢሲ ስቱዲዮስ ለኔትፍሊክስ ባዘጋጀው እና ‘የኒያንደርታልስ ምስጢሮች’ በሚለው ዘጋቢ ፊልም ላይ ለዕይታ ቀርቧል።

የዘጋቢው ፊልም ዓላማ ከ40 ሺህ ዓመታት በፊት ስለጠፉት የሰው ዘሮች ስለሚታወቁ ነገሮች ለመመርመር ነው።

ቅርጹ ለእነዚህ ሰዎች ፊት ያዘጋጅላቸዋል።

“ከማንነታቸው ጋር እንድንገናኝ የምትረዳን ይመስለኛል” ሲሉ በኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ፓሌአትሮፖሎጂስት የሆኑት ዶክተር ኤማ ፖሜሮይ ተናግረዋል።

“ከየትኛውም አካል ጋር መሥራት መቻል በጣም አስደሳች እና ትልቅ ዕድል ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዶ/ር ኤማ

ሞዴሉ የተሠራበት የራስ ቅል በኢራቅ ኩርዲስታን ሻኒዳር ዋሻ ውስጥ የተገኘ ነው። እአአ በ1950ዎቹ ቢያንስ 10 የሚደርሱ የኒያንደርታል ወንዶች፣ ሴቶች እና ህጻናት ቅሪተ አካል የተገኙበት ድንቅ ቦታ ነው።

እአአ በ2015 አንድ የብሪቲሽ ቡድን በኩርድ ባለስልጣናት ግብዣ ቀረበለት።

ብዙም ሳይቆይ ሻኒዳር ዚ የሚል ስያሜ የተሰጠው እና አከርካሪ፣ ትከሻ ፣ ክንዶች እና እጆችን ጨምሮ የግለሰቡን የላይኛው አካል ያካተተ አዲስ ቅሪተ አካል አገኙ።

የራስ ቅሉ ወደ 2 ሴንቲ ሜትር ገደማ ተጨፍልቋል። ይህም ከበርካታ ዓመታት በፊት ከዋሻው ላይ በወደቀ ድንጋይ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ።

በሻኒዳር አዲሱን ቁፋሮ የመሩት የካምብሪጅ ዩኒቨርሰቲው ፕሮፌሰር ግሬም ባርከር “ራስ ቅሉ ልክ እንደ ፒዛ ጠፍጣፋ ነበር” ብለዋል።

“ከዚያ አሁን ወደምታየው መሸጋገር በጣም አስደናቂ ጉዞ ነው። አንዳንድ ጊዜ እንደ አርኪኦሎጂስት የተለየ ነገር ላታገኝ ትችላለህ። ያለፈውን ነገር በመዳሰስህም ትገረማለህ። ልዩ የሆነ ነገር ምን እንደሆነ እንረሳዋለን።”

የሻኒዳር ዋሻ

በአካባቢው የጥንታዊ ቅርሶች ቢሮ ፈቃድ፣ የራስ ቅሉ ስብርባሪዎች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ተወስደው እንዲገጣጠሙ ተደረገ።

ውስብስብ የሆነው ሥራ ለማጠናቀቅ ከአንድ ዓመት በላይ ፈጅቷል።

የተገጣጠመው የራስ ቅሉ በየአቅጣጫው ፎቶ እንዲነሳ ተደረገ። ይህም በ3ዲ ህትመት ስመጥር ለሆኑት የደች አርቲስቶች አድሪ እና አልፎንስ ኬኒስ ተሰጠ።

አርቲስቶቹ የጥንት ሰዎችን በ3ዲ በማዘጋጀት ተክነውበታል።

ሴት መሆኗን እርግጠኛ ናቸው።

የዳሌ አጥንቶች ለማረጋገጥ ቢረዱም ከላይኛው የሰውነት ክፍል ጋር አልተገኙም።

ይልቁንም ተመራማሪዎቹ ከሴት ዘረመል ጋር በተያያዙ እና ጥርስ ውስጥ በሚገኙ የተወሰኑ ዋና ዋና ፕሮቲኖች ላይ ተመርኩዘው ሴት መሆኗን አረጋግጠዋል።

የቅሪተ አካሉ ቁመት አነስተኛ መሆኑም ድጋፍ ይሰጠዋል።

ስንት ዓመቷ ነው?

በ40ዎቹ አጋማሽ ላይ እንደሞተች ይገመታል። ይህንንም እስከ ሥሩ ድረስ በበሰበሱ ጥርሶቿ መለየት ይቻላል።

“ጥርሶች በዚህ ደረጃ በሚበሰብሱበት ጊዜ እንደቀድሞው ማኘክ አይሆንለትም። በመሆኑንም እንደቀደመው መብላት አትችልም” ሲሉ ዶ/ር ፖሜሮይ ተናግረዋል።

“ሌሎች የጥርስ ጤንነት መጓደል ምልክቶች አሉ። አንዳንድ ኢንፌክሽኖች እና የድድ በሽታም ነበሩ። በወቅቱ ወደ ተፈጥሯዊ የህይወቷ መጨረሻ እየደረሰች ነበር ብዬ አስባለሁ።”

ጥንታዊ ሰዎች

ኒያንደርታሎችን ከእኛ ዝርያ ጋር በማነጻጸር አደገኛ እና ያልተወሳሰቡ እንደሆኑ አድርገው ሳይንቲስቶች ለረዥም ጊዜ ይቆጥሩ ነበር።

አነዚህ አመለካከቶች ግን በሻኒዳር ከተገኙት ቅሪተ አካሎች በኋላ ተለውጠዋል።

ዋሻው የቀብር ስርዓት ስለመኖሩ ማሳያ ነው።

አስከሬኖች ከረዥም የድንጋይ ምሰሶ አጠገብ ባለው ጉድጓድ ውስጥ በጥንቃቄ ተቀምጠዋል። ሁሉም አስከሬኖች የተቀመጡበት መንገድ ተመሳሳይ ነው።

እነማን እንደሆኑ ለማወቅ ይረዱናል

አንዳንዶች እነዚህ ኒያንደርታሎች አበቦችን ተከትለው ዋሻዎቹ ውስጥ የገቡ ሊሆኑ እንደሚችሉ እንዲከራከሩ አድርጓቸዋል።

ይህም ምናልባት መንፈሳዊ መነቃቃትን ወይንም ሃይማኖትንም ሊያመለክት ይችላል።

የብሪታንያ ተመራማሪዎች ቡድን ግን የአበባው ብናኝ እዚያ የተገኘው ንቦች ወይም ደግሞ በአስሬኑ ላይ ከተቀመጡ የአበባ ቅርንጫፎች ሊሆን እንደሚችል ያስባሉ።

“በአበቦቹ ምክንያት ሳይሆን ቅርንጫፎቹ እራሳቸው ጅቦችን ወደ አስከሬኑ እንዳይገቡ መከላከል ይችሉ ነበር” ሲሉ የሊቨርፑል ጆን ሞሬስ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባው ፕሮፌሰር ክሪስ ሃንት ተናግረዋል።

“ቀብር የሚለውን ቃል ለመጠቀም አልደፍርም። ከቀሳውስት እና ከቤተክርስቲያን ሃሳብ ለመራቅም ‘ማስቀመጥ’ የሚለውን ቃል የምጠቀም ይመስለኛል። ይህንን ወግ እንደያዙት ምንም ጥርጥር የለውም” ብለዋል።