
ከ 5 ሰአት በፊት
በኅዳር 22 ቀትር፣ በርከት ያሉ ፍልስጤማዊ ሕጻናት በዌስት ባንክ ጎዳና አብረው ይጫወቱ ነበር።
ድንገት ሁለቱ ወደቁ። ከእስራኤል ወታደሮች በተተኮሰባቸው ጥይት ነበር የተገደሉት።
ባሲል 15 ዓመቱ ነበር፤ አደም ደግሞ ገና የ8 ዓመት አዳጊ።
ቢቢሲ በዚያች ዕለት በትክክል ምን እንደተፈጠረ ለመመርመር ሞክሯል።
ዌስት ባንክ በእስራኤል በኃይል ከተያዘ ግማሽ ምዕተ ዓመት አልፎታል።
አዳጊዎቹ ባሲልና አደም እንዴት ተገደሉ ለሚለው ምላሽ ለመሻት ቢቢሲ የስልክና የሲሲቲቪ ምሥሎችን፣ የእሰራኤል ወታደሮችን እንቅስቃሴ፣ የዐይን እማኞችን፣ የክስተቱን ዝርዝር ምርመራ ውጤቶችን ፈትሿል።
ቢቢሲ በሰበሰበውና በመረመረው መሠረት በእርግጥም በእስራኤል ጦር የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመ አመላካች ሆኖ አግኝቷቸዋል።
ቢቢሲ ያደራጀው መረጃ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ጥበቃና የጸረ ሽብር ባልደረባ የሆኑትን ቤን ሾልን የፍልጤማዊው ሕጻን አደም ግድያ በእርግጥም የ“ጦር ወንጀል” ተብሎ ሊበየን እንደሚችል አረጋግጦላቸዋል።
ሌላው የሕግ አዋቂ ዶ/ር ሎውረንስ ሂል የተፈጸመው ተኩስ ‘የዘፈቀደ ግድያ’’ ሲሉ በይነውታል።
የእስራኤል መከላከያ በበኩሉ ልጆቹ የተገደሉበት ሁኔታ በምርመራ ላይ ነው ይላል። ሆኖም ጥይት በቀጥታ የሚተኮሰው ቀጥተኛ አደጋና ስጋት ሲኖር ወይም አንድን ወንጀለኛ ለመያዝ ሌሎች አማራጮች ሁሉ ሲሟጠጡ እንደሆነ ያምናል።
ሐማስ ጥቃት ከፈጸመባት ቅጽበት ጀምሮ በዌስት ባንክ በፍስጤማዊያን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
ቢቢሲ ባገኘው መረጃ መሠረት የፍልስጤማዊያን ቤቶች ላይ ሆን ተብሎ ጸያፍ ስድቦች እንዲጻፉ ሆነዋል። ሰላማዊ ፍልስጤማዊ ዜጎች ጦር መሣሪያ እየተደገነባቸው አካባቢውን ለቀው ወደ ዮርዳኖስ እንዲሰደዱ ዛቻና ማስፈራሪያ ደርሶባቸዋል።
የአንድ ታጣቂ ነበር የተባለ ፍልስጤማዊ ሰውነቱ ደግሞ ኢ ሰብአዊ በሆነ መልኩ እንዲቆራረጥ ተደርጓል።

የባሲልና አደም ጉዳይ
ቢቢሲ የሁለቱ አዳጊዎች ግድያ በብዙ መልክና አንጻር ለማየትና ለመተንተን ሞክሯል።
አንድ የዓይን እማኝ እንደሚለው በቅርብ ርቀት በጄኒን የስደተኞች መጠለያ ካምፕ የእሰራኤል ወታደሮች ተኩስ ይሰማ ነበር።
ትንሹ አደም የእግር ኳስ አፍቃሪና የአርጀንቲናዊው የኳስ ኮከብ ሜሲ አድናቂ ነበር። ያን ቀትር ከታላቅ ወንድሙ ባሃ ጋር አብሮ ነበር።
ሲሲቲቪ ካሜራ እንዳሳየው በድምሩ በዚያ ጎዳና ላይ በወቅቱ ኳስ ይጫወቱ የነበሩ 9 ልጆች ነበሩ። ሲሲቲቪው ካሜራው በ360 ዲግሪ ቅኝት ያለውን ሁኔታ ያሳያል።
መቶ ሜትር አካባቢ ርቆ ስድስት ብረት ለበስ የእስራኤል ተሽከርካሪዎች ታጥፈው ፍልስጤማዊያን ልጆቹ ወደሚጫወቱበት ጎዳና ተጠጉ።
በስልክ የተቀረጸ ምሥል እንደሚያሳየው ልክ በዚህች ቅጽበት የወታደሮቹ ብረት ተሽከርካሪ አንድ በር ተከፈተ። ውስጥ ያለው ወታደር ቀጥታ ወደ ልጆቹ ማየት በሚችልበት ርቀት ላይ ነበር።
ልጅ ባሲል ወደ ጎዳናው መሀል ገባ። አደም 12 ሜትር ያህል ከወታደሮቹ ርቆ ይታያል። ከዚያ መሮጥ ጀመረ።
ወዲያውኑ በትንሹ 11 ጥይቶች ወደ አዳጊው አቅጣጫ ተተኮሱ።
ቢቢሲ እንዳረጋገጠው ጥይቶቹ ሰፊ ቦታን አካለዋል ወይም አዳርሰዋል።
4 ጥይቶች ከብት የተሠራ ስልክ እንጨት መተው ወድቀዋል። 2 ጥይቶች ሕንጻ መሣሪያ መሸጫ ተንሸራታች የሱቅ በር ላይ ተሰክተዋል። አንድ ጥይት ተምዘግዝጎ የቆመ መኪና የፊት መጋጫ ላይ አርፏል። ሌላው ጥይት ደግሞ የደረጃ መወጣጫ ላይ።
ቢቢሲ የተመለከተው የሐኪም ሪፖርት ሁለቱ ጥይቶች ሕጻኑን ባሲልን ደረቱ ላይ መተው ጥለውታል።
ሌላኛው በእስራኤል ወታደሮች የተተኮሰ ጥይት የ8 ዓመቱን አደምን ከጀርባ ጭንቅላቱን መተው ጥለውታል።
አደም እየሮጠ ነበር። የሱ ታላቅ ባሃ፣ ታናሽ ወንድሙ አደም በጥይት አናቱን መመታቱንና መውደቁን ካስተዋለ በኋላ በደመ ነፍስ ሰውነቱን እየጎተተ ሊያድነው ሲሞክር ይታያል። የአምቡላስ ያለህ እያለ ሲጮህ ይሰማል።
ወንድሙን የጎተተበት ጎዳና የደም ዳና መንገዱ ላይ ምልክት ሠርቶ ይታያል።
ነገር ግን አልተረፈም። ባሃ እንደሚለው ወንድሙ አደምና ጓደኛው ባሲል እዚያው በቅጽበት ነው የሞቱት።
አዳጊው ባሂ ለቢቢሲ እያለቀሰ ሲናገር እንዲህ አለ፦ “ደንግጬ ስለነበር ስለራሴ ነፍስ የማስብበት ጊዜም አልነበረኝም። ላናግረው ነበር የምሞክረው “አደም! አንተን’ኮ ነው አደም! እያልኩ ብጣራው ሊሰማኝ አልቻለም። ነፍሱ ከሥጋው እየተለየችው ነበር።”
ባሲል በጥይት ከመመታቱ በፊት አንዳች ነገር በእጁ ያወዛውዝ ነበር። ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም። የእስራኤል መከላከያ ኃይል በኋላ ላይ ባጋራው ምሥል ባሲል በእጁ ይዞት የነበረው ፈንጂ እንደነበር ለማመላከት ሞክሯል።
ቢቢሲ በበኩሉ መረጃዎችን ለበርካታ ባለሙያዎች አጋርቶ የተረዳው ባሲል ይዞት የነበረው ነገር ፈንጂ እንዳልሆነ ነው።
ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ የጦር ወንጀል መርማሪዎችን፣ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ባለሙያዎችን፥ ገለልተኛ መርማሪዎችን፣ የጸረ ሽብር ባለሙያዎችን ሁሉ አማክሯል።
አንዳንዶች ትንታኒያቸውን ስማቸው ሳይጠቀስ እንዲጻፍ ነው የፈለጉት።
ቤን ሾል የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶችና የጸረ ሽብር ልዩ ባልደረባ ሲሆን ባሲል በእርግጥም ፈንጂ ይዞ ከነበረ የእስራኤል ወታደሮች ሊተኩሱበት የሚያስችል የሕግ ማእቀፍ አለ ይላል።
“ይሁንና ልጅ አደም የተገደለበት ሁኔታ ግን የዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ጥሰት ነው። ሆን ተብሎ ነው የተገደለው። በዘፈቀደ ነው የተተኮሰበት። ስለዚህም የጦር ወንጀል ነው” ይላል ቤን ሾል
ዶክተር ሎውረንስ ሂል በብሪስተል ዩኒቨርስቲ የዓለም አቀፍ ሕጎች ፕሮፌሰር ናቸው።
“የእስራኤል ወታደሮች በብረት ለበስ ተሽከርካሪ ውስጥ ናቸው። (በሕጻኑ ላይ ስጋት እንኳ ቢኖርባቸው መኪናቸውን እየነዱ ዞር ማለት ይችላሉ። እነርሱ ግን ማድረግ የመረጡት ልጆቹ ላይ በዘፈቀደ መተኮስን ነው። ይህ ደግሞ ዓለም አቀፍ የመብት ጥሰትና ወንጀል ነው፥” ይላሉ።
የእስራኤል መከላከያ በበኩሉ ቦምብ ነበር የያዙት። ጥቃት ሊያደርሱብን ነበር። ለዚያ ነው የተኮስንባቸው ሲል ይከራከራል።
ነገር ግን ቢቢሲ በመረመረው የተንቀሳቃሽ ምሥል መሠረት እንዲሁም የዓይን እማኞችን በማናገር፣ አደም ምንም አይነት መሣሪያ እንዳልያዘ ተረድቷል።
አደም እየተጫወተ ነበር፥ ወታደሮቹን ሲያይ ለመሸሽ ሞከረ፣ በዚያው ቅጽበት በእስራኤል ወታደሮች ከኋላ በጥይት ተመታ።
የእስራኤል መከላከያ ነገሩን እየመረመርኩት ነው ይላል።
ሆኖም ቢቢሲ መረጃውን ያሳያቸው የቀድሞ የእስራኤል መከላከያ ባልደቦች እንደሚሉት የእስራኤል የሕግ ሥርዓት ወንጀሉን የፈጸሙትን ወታደሮች ተጠያቂ አያደርጋቸውም።
የሽ ዲን ከሚባል የእስራኤል የሰብአዊ መብት ድርጅት በተገኘ መረጃ ከእንዲህ ዓይነት በእስራኤል ወታደሮች ከሚፈጸሙ ወንጀሎች አንድ እጅ የሚሆኑት እንኳ የክስ ፋይል አይከፈትባቸውም።

በሐማስ የሚመራው ጤና ሚኒስትር ባወጣው መረጃ እስከ አሁን 34ሺህ ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል። ይህም የሐማስን መብረቃዊ ጥቃት ተከትሎ በእስራኤል በተከፈተ መጠነ ሰፊ ጥቃት ነው።
ሐማስ 1200 ሰዎችን ገድሎ፣ 253 የሚሆኑትን አግቶ መውሰዱ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ የእስራኤል ጦር በዌስት ባንክ ጥቃቱን በማጠናከሩ ከፍተኛ ሕጻናት የተገደሉበት ዓመት ሆኗል።
ዩኒሴፍ እንዳለው በፈረንጆቹ 2023 ብቻ በዌስት ባንክ 124 ሕጻናት ተገድለዋል። 85 የሚሆኑት የተገደሉት የሐማስን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በወሰደችው እርምጃ ነው።
በፈረንጆቹ 2024 ደግሞ እስራኤል በኃይል በያዘቻቸው የፍልስጤም ግዛቶች 36 ሕጻናት ተገድለዋል።
በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ዌስትባንክ የጦር ቀጠና ስላልሆነች ወታደሮች የሚገዙበት ሕግም በዚያ መጠን የተገደበ መሆን ይኖርበታል።
ወታደሮች ጥይት ከመተኮሳቸው በፊት ለሕይወታቸው አደጋ የመሰለ ነገር ሲገጥማቸው ማድረግ ያለባቸውን የቀድሞ የእሰራኤል ወታደር ለቢቢሲ አጋርቷል።
አንደኛ በአረብኛ ወይም በሂብሩ ቋንቋ የቃል ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ ተጠርጣሪው ለዚህ አልታዘዝ ካለ አስለቃሽ ጭስ መጠቀም፥ በዚህም ማይመለስ ከሆነና አደገኛ መስሎ ከታየ እግር ላይ ተኩሶ ማቁሰል ይመከራል።
ቀጥታ ለመግደል ከመተኮስ በፊት እነዚህ ሂደቶች መኖር አለባቸው።
የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር፣ ቢቢሲ በዌስት ባንክ ስለተገደሉ ሕጻናት የሕክምና ሰነዶችን እንዲመለከት ልዩ ፈቃድ ሰጥቶት ይህንኑ አደርጓል።
ሰነዶቹ 112 ሕጻናት መገደላቸውን ያሳያሉ። ዕድሜያቸው ደግሞ ከ2 ዓመት እስከ 17 ይሆናል።
ሁሉም የተገደሉት በእስራኤል ጥይት ተተኩሶባቸው ነው። ይህም በፈረንጆች ከጥር 2003 እስከ 2004 ጥር ድረስ ነው።
ቢቢሲ ልጆቹ የተገደሉበትን ሁኔታ እርግጡን ሊያውቅ አልቻለም።ምናልባት አንዳንዶቹ ለእስራኤል ወታደሮች የሕይወት አደጋ ደቅነውም ይሆን ይሆናል።
ነገር ግን የሕክምና ትንታኔዎች እንዳስረዱት 98 ከመቶ የሚሆኑት ሕጻናት በጥይት የተመቱት ከወገብ በላይ ነው።
ይህ ማለት ወታደሮቹ ልጆቹን ለማስጠንቀቅ ሳይሆን ለመግደል ብለው እንደተኮሱ ማሳያ ሊሆን ይችላል።
ቢቢሲ ለ5 ሳምንታት በዌስት ባንክ ባደረገው ቆይታና ምርመራ የእስራኤል ወታደሮችን ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ በርካታ መረጃዎችን ማግኘት ችሏል።
ለምሳሌ ቢቢሲ የ45 ሰዓታት የፈጀ፣ በቱልካርም የስደተኛ ጣቢያው የተደረገ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ተመልክቷል።
በርካታ ፍልስጤማዊያን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከዚህ ኦፕሬሽን በኋላ መሣሪያ ግንባራቸው ላይ እየተደገነ ወደ ጆርዳን እንዲጠፉ ተነግሯቸዋል።
የእስራኤል መከላከያ ነገሩን እመረምራለሁ ብሏል።
- የአፍሪካ ኅብረት በሕገ ወጥ መንገድ ከንግድ ባንክ አካውንቱ ሊወጣ የነበረው ስድስት ሚሊዮን ዶላር አለመሳካቱን ገለጸ2 ግንቦት 2024
- በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ‘ስልታዊ የዘር ጭፍጨፋ’ አዝማሚያ እንዳለው የአውሮፓ የፍትሕና ሕግ ማዕከል የተባለ ድርጅት አስታወቀ2 ግንቦት 2024
- በእስራኤል ጥቃት ከተገደለች እናት ማህጸን በሕይወት ወጥታ የነበረችው ጨቅላ አረፈች26 ሚያዚያ 2024
ሃይታም የሚባል የ12 ዓመት ሕጻን፣ ዜግነቱ ካናዳዊ-ፍልስጤማዊ የሆነ፥ የእስራኤል ወታደሮች ቢላ አንገቱ ላይ አስጠግተው እንዳስፈራሩት ለቢቢሲ ተናግሯል።
ቢቢሲ ይህ ክስተት እውነት ስለመሆኑ ከወንድሙና ከአባቱ ማረጋገጥ ችሏል።
ዶክተር ኢራን ዳይመንድ በኢየሩሳሌም የዲያኮኒያ ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ጥበቃ ማዕከል ባልደረባ ናቸው።
በቱልካርም ስደተኞች ጣቢያ በእስራኤል ወታደሮች የተፈጸሙት ተግባራት የዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥሱ ናቸው ይላሉ።
ይህም ልጆችን በቢላ ማስፈራራትን ይጨምራል።
በዚህ ካምፕ ውስጥ በተደረገ ሌላ ወታደራዊ ኦፕሬሽን፣ የእስራኤል ወታደሮች አንድን የፍልስጤም ተዋጊ ነው የተባለ ወጣት ከደሉት በኋላ አስክሬኑ ላይ ሲሸኑበት ነበር። ጎዳና ላይ ይጎትቱም ነበር።
ቢቢሲ ይህን ከዐይን ምሥክሮች ሰምቷል።
ቢቢሲ የዚህን አስክሬን ተጠፍሮ የታሰረበትን ገመድ እንዲሁም ደሙ የፈሰሰበትን ልብሱን ተመልክቷል።
ቢቢሲ በዚህ ጉዳይ ላይ ፕሮፌሰር ማክሮ ሳሶሊን አነጋግሯል። በጄኔቫ ዩኒቨርስቲ የዓለም አቀፍ ሕጎች ከፍተኛ ተመራማሪ ናቸው።
“በሕጋዊ ሁኔታ እንኳ ተገድለው ቢሆን አስክሬኖች ክቡር ናቸው። የተፈጸመው ነገር ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስና ምናልባትም የጦር ወንጀል የሚባል ነው” ይላሉ።
የእስራኤል መከላከያ እንደሚለው ግለሰቡ ፈንጂ ይዞ ስለነበር ወታደሮች ለራሳቸው ጥንቃቄ ሲሉ ነው ጠፍንገው ያሰሩት።
ቢቢሲ ያሰናዳቸውን መረጃዎች የተመለከቱ የቀድሞ የእሰራኤል ወታደሮች “አይዲኤፍ በዌስትባንክ የፈጸማቸው ሕገ ወጥ ተግባራት ምናልባት ሌላ የፍልስጤሞች ወታደራዊ ታጣቂ ኃይል እንዲወለድ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
“ፍልስጤማዊያን ከዚህ ወዲያ እንደ ቀደመው ጊዜ ከእሰራኤል ወታደሮች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ጤናማ ይሆናል ብሎ ማሰብ የዋህነት ወይም ደግሞ ቂላቂልነት ነው የሚሆነው። ” ይላል ቢቢሲ ያነጋገረው አንድ የቀድሞው የእስራኤል መከላከያ አባል።
“ነገሮች ደግሞ እየባሰባቸው እየሄዱ ነው። “