
3 ግንቦት 2024, 17:34 EAT
የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀንን አስመልከቶ ዲፕሎማቲክ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ 18 አገራት፣ አሜሪካን እና የአውሮጳ ሕብረት አባል አገራትን ጨምሮ “ሥራቸውን ሲሰሩ ፍትሀዊ ባልሆነ መልኩ የታሰሩ” ጋዜጠኞች እንዲለቀቁ ሲሉ በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠየቁ።
ይህንን መግለጫም ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ኢትዮጵያ ከአጋሮቿ እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ገንቢ የሆነ መስተጋብር እንዳላት ጠቅሶ “ እኔ አውቅልሀለሁ የሚል የጋራ መግለጫ ለሁለትዮሽ ግንኙነት የሚበጅ አይደለም፤ እንዲሁም በአገሪቱ ያለውን የሕግ የበላይነትን ማስከበር ዝቅ የሚያደርግ ነው” ሲል አጣጥሎታል።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚህ መግለጫው ላይ “ [ኤምባሲዎቻቸው] በሚገኝበት አገር ጋር እንዲህ ያለ ግንኙነት ፍሬያማ ያልሆነ እና ከተለመደው የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚቃረን ነው” ሲል ገልጾታል።
በጋራ መግለጫ ያወጡት የምዕራብ አገራት ሜይ 3 የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን መሆኑን አስታውሰው “የፕሬስ ነጻነት አስፈላጊነት እንዲሁም እውነትን ለመዘገብ ያለመታከት የሚሰሩ መገናኛ ብዙኀንን እና ጋዜጠኞችን የመከላከል አስፈላጊነትን ያስታውሳል” ብለዋል።
አክለውም የመናገር ነጻነት እና የፕሬስ ነጻነት መከበር ያለባቸው የሰው ልጅ ሰብዓዊ መብቶች ናቸው ብለዋል።
ነገር ግን በኢትዮጵያ “ጋዜጠኞች ስራቸውን በመስራታቸው ብቻ የሚስፈራሩበት እንዲሁም ያለፍትህ የሚታሰሩበት አጋጣሚዎች አሉ። የዛሬውንም ቀን በጉዳዩ ላይ ያለውን ለመናገር እና እንዲለቀቁ በመጠየቅ እናስበዋለን” ብለዋል።
- በመስቀል ላይ የሚፈጸም ስቅላት እንዴት እና የት ተጀመረ?3 ግንቦት 2024
- እስራኤል በዌስት ባንክ በአንድ ሕጻን ላይ የፈጸመችው ግድያ የጦር ወንጀል ሊኾን እንደሚችል የቢቢሲ ምርመራ አመላከተ3 ግንቦት 2024
- በጋዛ እየተፈጸመ ባለው ጥቃት ምክንያት ቱርክ ከእስራኤል ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት አቋረጠች3 ግንቦት 2024
አክለውም “ የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀንን አስበን ስንውል ጋዜጠኞች በነጻነት ያለምንም የእከሰሳለሁ ፍራቻ የሚዘግቡበት ዓለምለመፍጠር ለመስራት [ቃል በመግባት ነው]። ”
ሲፒጄ በቅርቡ ባወጣው መረጃ መሰረት ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ ኤርትራን እና ግብጽን ተከትላ ጋዜጠኞችን በማሰር ቀዳሚ ከሆነ የአህጉሪቱ አገራት መካከል መድቧታል።
ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ (አርኤስኤፍ) በበኩሉ በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ 15 ጋዜጠኞች መታሰራቸውን መመዝገቡን ጠቅሶ ከ180 አገራት 141ኛ ሲል አስቀምጧታል።
ድርጅቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያን በ2023፣ 131ኛ እና በ2022 114ኛ አድርጎ የመደበ ሲሆን ይህ የዘንድሮ ምደባው በአገሪቱ የፕሬስ ነጻነት እየወረደ መምጣቱን ያሳያል።
18 አገራት በጋራ በመሆን ባወጡት በዚህ መግለጫ የአውሮጳ ሕብረት፣ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን፣ ኦስትርያ፣ ፊንላንድ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ዴንማርክ፣ ቤልጂየም፣ ኖርዌይ፣ አየርላንድ፣ ኒውዚላንድ፣ አውስትራልያ፣ ስፔይን፣ ኔዘርላንድስ፣ ስዊዲን ይገኙበታል።