ሰልፍ

ከ 9 ሰአት በፊት

የጋዛ የተኩስ አቁም ንግግር እየተካሄደ ባለበት ወቅት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን የታገቱ ሰዎች እንዲመለሱ የሚጠይቅ ሰልፍ አከናውነዋል።

በቴል አቪቭ አደባባይ የወጡት ሰልፈኞች “ጦርነት የተገረመ ነው። ሕይወት ግን ቅዱስ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጦርነቱን ለማራዘም እየሞከሩ ነው ሲሉም ወቅሰዋል።

የሐማስ አሸማጋዮች ለምክክር ካይሮ ገብተዋል።

እስካሁን አዲስ ነገር እንደሌለ ገልጸው ቀጣይ ውይይቶች እንደሚኖሩ አክለዋል።

አደራዳሪዎቹ ግብፅ እና ኳታር ናቸው። እስራኤል በጋዛ ድብደባ መፈጸም እንድታቆምና ታጋቾች ነጻ እንዲወጡ ለማስቻል ንግግር እየተካሄደ ይገኛል።

ስምምነቱ ጊዜያዊ ይሆናል ወይስ ዘላቂ የሚለው ዋነኛ ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል።

ለ40 ቀናት የተኩስ አቁም ተደርጎ ታጋቾች እንደሚለቀቁና ከእስራኤል እስር ቤቶች ፍልስጤማውያን እስረኞች እንደሚፈቱ ይጠበቃል።

የሐማስ መሪ ኢስማኤል ሀንያህ አማካሪ እንዳሉት፣ አሁን የቀረበውን ሐሳብ “በትኩረት እያጤኑት” ነው።

ስምምነት ላይ መድረስ የሚቻለው እስራኤል ከጋዛ ስትወጣና ጦርነቱ ሲያከትም መሆኑን ገልጸዋል።

ስማቸው የማይጠቀስ የእስራኤል ባለሥልጣን እስራኤል “በማንኛውም ሁኔታ ጦርነቱን አታቆምም” ሲሉ ለመገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል።

“ለጊዜው ታጋቾች ለማሰስቀቅ የተኩስ አቁም እፎይታ ኖረም አልኖረም የእስራኤል ጦር ራፋ ገብቶ የቀረውን የሐማስ ታጣቂ ያጠፋል” ማለታቸው ተዘግቧል።

አሜሪካ አዲስ ጥቃት ሲፈጸም ድጋፏን ለመቀጠል እምብዛም ፈቃድ አላሳየችም። አሜሪካ ፍልስጤማውያን እንዳይጎዱ የሚያደርግና የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያንን የሚጠብቅ ዕቅድ ማየት እንደምትሻ ገልጻለች።

በሐማስ ከታገቱ 252 ሰዎች መካከል 128 ያህሉ አሁንም የት እንዳሉ አይታወቅም። 34ቱ እንደሞቱ ይታመናል።

ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡት አንዷ የሆነችው ማታሊ ኤልዶር “ታጋቾችን ባጠቃላይ ማስመለስ አለብን” ብላለች።

አንዳንድ ተቃዋሚዎች ቴል አቪቭ በሚገኘው ወታደራዊ መቀመጫ ኪርያ አካባቢ ነው የተሰባሰቡት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተኩስ አቁም ሐሳቡን አልገፉበትም ብለው ይወቅሳሉ።

የእስራኤል የጦርነት ካቢኔ አባል ቤኒ ጋንትዝ “ገና ዝርዝር ምላሽ አልተሰጠም። ሲሰጥ ካቢኔው ይወያያል” ብልዋል።

ለወራት ያህል የተኩስ አቁም ለማድረግ ውይይት ቢደረግም እምብዛም ፍሬያማ አልሆነም።

አሁን እየተደረገ ላለው ድርድር ቅርብ የሆኑ የቢቢሲ ምንጭ እንደገለጹት፣ ድርድሩ ውስብስብ ሲሆን፣ አንዳች ስምምነት ላይ ለመድረስ ቀናት ሊወስድ ይችላል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የምግብ ፕሮግራም ኃላፊ ሲድኒ መኬን፣ ጋዛ ወደ አጠቃላይ ረሃብ እያመራ እንዳለ ተናግረዋል።

“እየጠየቅን ያለነው የተኩስ አቁም ነው። እርዳታ ማዘዋወር መቻል ነው የጠየቅነው” ብለዋል።