የተፈናቀሉ ሰዎች

ከ 8 ሰአት በፊት

በከፍተኛ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ሳቢያ ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።

በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል 56 ሰዎች እንደሞቱ የተገለጸ ሲሆን፣ በሪዮ ግራንድ ደ ሱል 67 ሰዎች የደረሱበት እንዳልታወቀ ተገልጿል።

ወደ 25,000 ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እና የንጹህ ውሃ አቅርቦት ተቋርጦባቸዋል።

በቀጣይም ከፍተኛ ዝናብ ይጠበቃል።

ይህ የአየር ንብረት ለውጥ የተከሰተው ከመደበኛው ጊዜ የከፋ ሙቀት፣ ወበቅ እና ንፋስ በመከሰቱ ነው።

ከአጠቃላይ 497 ከተሞች ግማሹ አውሎ ንፋስ ገጥሟቸዋል። አውራ ጎዳናዎችና ድልድዮች ላይም ጉዳት ደርሷል።

የመሬት መንሸራተቱ ከውሃ ኃይል የሚያመነጭ ግድብ ላይ ጉዳት አድርሷል። ቤንቶ ጎንካልቭስ በተባለ ከተማ 30 ሰዎች ሞተዋል።

በውሃ መሙላት ምክንያት ሌላ ግድብም ይፈርሳል ተብሎ ተሰግቷል።

በፖርቶ አልግሬ ከመጠን በላይ በሞላ ወንዝ ምክንያት፣ መንገዶች በጎርፍ ተጥለቅልቀዋል። መንደሮችም ከውሃ ሥር ሰጥመዋል።

የፖርቶ አልግሬ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በረራዎችን አቁሟል።

አንድ ነዋሪ የደረሰው ጉዳት “ልብ ይሰብራል” ሲሉ ገልጸዋል።

ማሪያ ሉዊዝ የተባሉት ነዋሪ “የምኖርበት አካባቢ ነው። እዚ ላሉ ሰዎች በሙላ አዝናለሁ። ይሄ ሁሉ መሆኑ ያሳዝናል” ብለዋል።

የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉዊዝ ኢራሲዮ ሊላ ዳ ሲልቫ፣ ጉዳት የደረሰበትን አካባቢ ጎብኝነዋል።

ማዕከላዊ መንግሥቱ ድጋፍ እንደሚሰጥም ቃል ገብተዋል።

አምና በተነሳ ዝናብ የቀላቀለ አውሎ ነፋስ ሳቢያ 30 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

የብራዚል ብሔራዊ ሜትሮሎጂ እንደሚለው ከፍተኛ የዝናብ መጠን የኤል ኒኖ ውጤት ነው።