ኪቪኪ ከስድስት ዓመት በላይ ታስሯል

ከ 5 ሰአት በፊት

በአውሮፓ በጣም ከሚፈለጉ ወንጀለኞች አንዱ የነበረው ታዋቂው መንታፊ የ33 ሺህ ታማሚዎችን የተሰረቁ መረጃዎች በመጠቀም በማጭበርበሩ በእስር ተቀጥቷል።

የጁሊየስ ኪቪማኪ መታሰር ለ11 ዓመታት ዘለቀውን የመንታፊነት ተግባር ከፍጻሜው አድርሷል። ግለሰቡ ገና በ13 ዓመቱ ነበር በታዳጊዎች የመንታፊ ቡድን ውስጥ በመንቀሳቀስ ታዋቂ ለመሆን የበቃው።

ቲና ከተለመደው የፊንላንድ ሳውና በኋላ አየር እየወሰደች ነበር ስልኳ መልዕክት እንደደረሳት ያሳወቃት።

ስሟን፣ የማህበራዊ ዋስትና ቁጥሯን እና ሌሎች የግል ዝርዝሮችን የያዘ ነግር ግን ማንነታቸው ከማይታወቅ ላኪ የመጣ ኢሜይል መልዕክት ነበር።

“መጀመሪያ ላይ በነበረው ጨዋነት እና ትህትና ተገረምኩኝ” ብላለች።

“ውድ ወይዘሮ ፓሪካ” ሲል በጀመረው ኢሜይል ላኪው የግል መረጃዋን ታካሚ ከነበረችበት የሳይኮቴራፒ ማዕከል እንዳገኘ ገልጿል። ኢሜይል ላኪው እሷን በቀጥታ የሚያነጋግሯት ማዕከሉ የግል መረጃው መሰረቁን ችላ በማለቱ መሆኑን አሳወቃት።

ለሁለት ዓመታት በማዕከሉ እጅ ገቡ የግል የህክምና ታሪኮቿ አሁን ባልታወቀ ሰው እጅ ላይ ናቸው።

በ24 ሰዓት ውስጥ ገንዘብ ካልከፈለች ሁሉንም በበይነመረብ እንደሚያትመው ዛተ።

“ይህ የሚያንገላታ ስሜት ነበር። አንድ ሰው የግል መረጃዬን እንደወረረ እና የህክምና ማስረጃዬ ተጠቅሞ ገንዘብ ለማግኘት እየሞከረ እንደሆነ አስብ ነበር” ትላለች።

ይህ የገጠማት ቲና ብቻ እንዳልሆነች በፍጥነት ተገነዘበች።

ቲና ፓሪካ ከቶጎጂዎች መካከል ናት

የሌሎች 33 ሺህ ታማሚዎች መረጃዎችም ተዘርፈዋል። በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ እንዲከፍሉ ተጠይቀዋል። ይህም በፊንላንድ የወንጀል ታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተጎጂዎች የተካተቱበት ነው።

ከቫስታሞ ሳይኮቴራፒ የተሰረቀው መረጃ የህጻናትን ጨምሮ የበርካቶችን ጥልቅ ሚስጥሮችን ይዟል። ከጋብቻ ውጭ ከተፈጸሙ ግንኙነቶች እስከ ወንጀሎች የተናዘዙባቸው መረጃዎችንም ያቀፈ ነበር።

በጥቃቱ ላይ ጥናት ያደረገው የፊንላንድ የሳይበር ደህንነት ድርጅት ዊትሴክዩር ባልደረባው ሚኮ ሃይፖነን ክስተቱ በአገሪቱ አስደንጋጭ እና ለቀናት ርዕሰ ዜና መሆን የቻለ ነበር ብሏል።

“በዚህ ደረጃ የሚደረግ ጥቃት ለፊንላንድ አደጋ ነው። ሁሉም ሰው ቢያንስ አንድ ጉዳት የደረሰበትን ሰው ያውቅ ነበር” ብሏል።

ይህ ሁሉ የሆነው እአአ በ2020 በኮሮና ወረርሽኝ እንቅስቃሴ በተከለከለበትወ ወቅት ነበር። በሳይበር-ደህንነት ዓለምም ድንጋጤ ፈጥሯል።

ኢሜይሎቹ ተጽዕኖ ፈጣን እና አስከፊ ነበሩ።

ጠበቃው ጄኒ ራይስኪዮ ከተጎጂዎች መካከል 2 ሺህ 600 የሚሆኑትን ትወክላለች።

የታካሚዎች መረጃ በበይነ መረብ ላይ ከታተመ በኋላ ህይወታቸውን ያጠፉ ሰዎች እንደተገናኙ ለፍርድ ቤት ተናግራለች። ለተጎጂዎች ፍርድ ቤት ውስጥ ለአንድ ደቂቃ የማሰቢያ ጊዜ እንዲደረግም መርታለች።

አጭበርባሪው በበይነ መረብ ‘ራንሰም ማን’ በመባል ብቻ ይታወቃል። ተጎጂዎች በ24 ሰአት ውስጥ 200 ዩሮ እንዲከፍሉት ይጠይል።

ቀነ ገደቡ ካለፈ ወደ 500 ዩሮ ከፍ ያደርገዋል። ካልሆነ በበይነ መረብ ያትመዋል።

በጣም መዘግየታቸውን ያልተረዱ ወደ 20 የሚጠጉ ሰዎች ከፍለውታል። ራንሰም ማን ግን ሙሉውን መረጃ አውጥቶት ነበር።

ሁሉም መረጃ ዛሬም በይነ መረብ ላይ አለ።

ሚኮ እና ባልደረቦቹ መንታፊውን በመከታተል ፖሊስን ለመርዳት ሲሞክሩ አሳልፈዋል። መንታፊው ከፊንላንድ ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁሙ ሐሳቦች ብቅ ማለት ጀመሩ።

በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ከሚባሉት የፖሊስ ምርመራዎች አንዱ የሆነው ምርመራ አቅጣጫውን በሳይበር ወንጀል ውስጥ ታዋቂ ወደሆነው ፊንላንዳዊ ወጣት ይጠቁም ጀመር።

ኪቪማኪ ስካይ ኒውስ ላይ ቃለመጠይቅ አድርጓል

የዘኪል የወንጀል ተሳትፎ

ዘኪል በሚል ራሱን የሚጠራው በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኘው የመረጃ መንታፊ ኪቪማኪ ተብሎ ይታወቃል። ጥንቃቄ በማድረግ የታወቀ ሰው አይደለም።

በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ እያለ ስለ መንታፊነቱ እና ምዝበራው የቻለውን ያህል መፎከር ይቀናው ነበር።

እአአ በ2010ዎቹ እጅግ በጣም ንቁ በሆነው የታዳጊ ወጣቶች የመንታፊ ቡድን ውስጥ ተካቶ ነበር። እንደ ሊዛርድ ስኳድ እና ሃክ ዘ ፕላኔት ባሉ መንታፊ ቡድኖች ውስጥ በመሳተፍ ይታወቃል።

ኪቪማኪ እአአ በ2014፣ በ17 ዓመቱ ተይዞ በ50 ሺህ 700 የምንተፋ ወንጀሎች ጥፋተኛ እስከተባለበት ጊዜ ድረስ በደርዘን የሚቆጠሩ ከፍተኛ ጥቃቶችን ያከናወነ ዋነኛው መንታፊ ነበር።

በአወዛጋቢ ሁኔታ ግን አልታሰረም። ያለእስር የተጣለበት የሁለት ዓመት ቅጣት በብዙ ተተችቷል።

ኪቪማኪ እና አጋሮቹ ሌሎች አገራትንም ዒላማቸው ያደርጋሉ የሚል ስጋትም ነበር።

እንደ አፍላ እኩዮቹ ሁሉ ኪቪማኪም ፖሊሶች እንደፈለገ ከመሆን እንዲያቆሙት የፈቀደ አይመስልም። ታስሮ ቅጣቱ ከመተላለፉ በፊት ከየትኛውም ወጣት የመንታፊ ቡድን ያላደረገውን በጣም ድፍረት የተሞላበት ጥቃት ፈጽሟል።

እሱ እና ሊዛርድ ስኳድ በገና ዋዜማ እና በገና ቀን ሁለቱን ትላልቅ የጌም መተግበሪያዎች ዒላማቸው አደረጉ።

ፕሌይስቴሽን እና ኤክስቦክስ ባልተወሳሰቡ ነገር ግን አገልግሎትን በሚከለክል ቴክኒክ ሥራ አቆሙ።

በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ጌሞቹን ማውረድ፣ አዲስ ጌሞችን መመዝገብ ወይም ከጓደኞቻቸው ጋር በበይነመረብ መጫወት እንዳይችሉ ሆኑ።

የሊዛርድ ስኳድ አባላት በመመንተፋቸው ይኮራሉ

ኪቪማኪ የዓለምን የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት እንደተደረገበት ማወቁ ቀልቡን ሳበው እና ከስካይ ኒውስ ጋር የቴሌቪዥን ቃለ መጠይቅ ለማድርግ ፈቀደ። በወቅቱ በጥቃቱ ዙሪያ ምንም ጸጸት አላሳየም።

ሌላ የዘኪል ሊዛርድ ባልደረባ ለቢቢሲ እንደተናገረው ከሆነ ኪቪማኪ ተቀናቃኞቹን ለመበቀል እና ችሎታውን ለማሳየት የሚወድ በቀለኛ ታዳጊ ነበር።

“በሚያደርገው ነገር በጣም ጎበዝ ነበር። ስለሚያስከትለው ውጤት ምንም ደንታ አልነበረውም። ሁልጊዜም ከሌሎች የበለጠ ተጉዞ ለማጥቃት ይፈልጋል” ብሏል።

“በእሱ ላይ ትኩረት መደረጉ ሳይረብሸው የቦምብ ዛቻዎችን ያደርጋል። ድምጽ ሳይቀይርም እራሱን ይደውላል” ሲል ራያን ተናግሯል። ባለሥልጣናት ዘንድ ቤተሰቡ ስም ስለማይታወቅ ስሙን መስጠት አይፈልግም።

ኪቪማኪ ከፍርዱ በኋላ ከትንንሽ ጠለፋዎች ጋር ስሙ ከመነሳቱ ውጭ ከቫስታሞ ጥቃት ጋርነስሙ እስኪያያዝ ድረስ ለዓመታት ጠፍቶ ነበር።

ኪቪማኪ በሄልሲን ኪረደድ ቤት

ቀይ ማስጠንቀቂያ ወጥቷል

የኢንተርፖል ቀይ ማስጠንቀቂያ እንዲያወጣ ለማድረግ የፊንላንድ ፖሊስ ማስረጃ ለመሰብሰብ ወደ ሁለት ዓመት ገደማ ፈጅቶበታል።

በአውሮፓ በጣም ከሚፈለጉ ወንጀለኞች አንዱ ለመሆንም በቃ። 25 ዓመት የሆነው ወጣት የት እንዳለ ማንም አያውቅም።

ባለፈው የካቲት ወር በፓሪስ የሚገኙ ፖሊሶች ቤት ውስጥ ግጭት መፈጠሩን የሚገልጽ የስልክ ጥሪ ካገኙ በኋላ ወደ አንድ መኖሪያ ቤት ይሄዳሉ። ኪቪማኪን በሃሰተኛ ስምና በተጭበረበሩ የመታወቂያ ሰነዶች ሲኖር አግኝተውታል።

በፍጥነት ወደ ፊንላንድ ተላልፎ ተሰጠ። እዚያም ፖሊሶች በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ ከታዩት ከፍተኛ ክሶች አንዱን ማዘጋጀት ጀመሩ።

የህግ ባለሙያው ማርኮ ሌፖነን የሦስት ዓመት ጉዳዩን የመራው ሲሆን ከሥራ ህይወቱ ትልቁ እንደሆነም ተናግሯል። “በአንድ ወቅት በጉዳዩ ላይ ከ200 በላይ ፖሊሶች ሲሠሩ ነበር። በጣም የብዙ የተጎጂዎችን መረጃዎች እና ታሪኮች የማየት ከባድ ምርመራ ነበር” ብሏል።

የኪቪማኪ የፍርድ ሂደት የአገሪቱን ጋዜጠኞች እና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ትልቅ ትኩረት ነበር።

በመጀመሪያ ቀን ፍርድ ቤት ውሎው ንጹህነቱን በፍጹም በእርጋታ ከመናገር ባለፈ እና አልፎ አልፎ ቀልዶችን በዝምታ ለተዋጠው ፍርድ ቤት ተናግሯል።

በእሱ ላይ የቀረበው ማስረጃ ግን እጅግ በጣም ብዙ ነበር።

የኪቪማኪን የባንክ አካውንት የተሰረቀውን መረጃ ለማውረድ ጥቅም ላይ መዋሉ ወሳኝ ነገር ነበር ብሏል ሌፖነን።

የፖሊስ መኮንኖች ኪቪማኪ በበይነ መረብ ከለጠፈው ምስል ጀርባ መኖሩን ለማሳየት አዲስ የፎረንሲክስ ቴክኒኮችን ተጠቅመዋል።

ፖሊሲ ከልጥፎቹ ጀርባ የኪቪከኪ አሻራ እንዳለበት ደርሶበታል

“በመድረኩ ላይ የሚለጥፈው ይህ ማንነቱ ያልታወቀ ሰው ኪቪማኪ መሆኑን ማረጋገጥ ችለናል። የማይታመን ቢሆንም የምታውቀውን እያንዳንዱን መንገድ መጠቀም እና የማታውቀውን መሞከር እንዳለብህ ያሳያል” ሲል ሌፖነን ተናግሯል።

በመጨረሻም ዳኞቹ በሁሉም ክሶች ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ብይን ሰጥተዋል።

ፍርድ ቤቱ እንዳለው ኪቪማኪ ከ30 ሺህ በላይ ለሚሆኑት ለእያንዳንዱ ተጎጂዎች ወንጀሎች ጥፋተኛ ነበር።

በከባድ የዳታ ጥሰት፣ በከባድ የማጭበርበር ሙከራ፣ 9 ሺህ 231 የግል መረጃን የሚጥስ መረጃ በማሰራጨት፣ 20 ሺህ 745 የማጭበርበር ሙከራ እና በ20 ከባድ ማጭበርበር ወንጀል ተከሷል።

ከከፍተኛው የሰባት ዓመት እስራት ውስጥ የስድስት ዓመት ከሦስት ወር እስራት ተፈርዶበታል።

በእስራት ያሳለፈው ተቀንሶ እና በፊንላንድ ህግ መሠረት ከተላለፈበት እስራት ግማሹ ብቻ ተፈጻሚ ሊሆንበት ይችላል።

እንደ ቲና ለመሳሰሉት ተጎጂዎች ግን ይህ መቼም ቢሆን በቂ አይደለም።

“በጣም ብዙ ሰዎች በዚህ በብዙ መንገዶች ተጎድተዋል። 33 ሺህ ማለት ብዙ ተጠቂዎች ናቸው። ጤናችንን ይነካል። አንዳንዶቹ መረጃውን በተጠቀሙ ሰዎች የገንዘብ ማጭበርበሮች ዒላማ ሆነዋል” ትላለች።

እሷ እና ሌሎች ተጎጂዎች ከጉዳዩ ካሣ ስለመኖሩ ለማየት እየጠበቁ ናቸው ።

ኪቪማኪ ከአንድ ተጎጂ ቡድን ጋር ከፍርድ ቤት ውጭ ጉዳዩን ለመፍታት በመርህ ደረጃ ተስማምቷል። ሌሎች ግን በእሱ ወይም በቫስታሞ ላይ የፍትሐ ብሔር ክስ ለመመስረት እያቀዱ ነው።

የሳይኮቴራፒ ኩባንያው አሁን ከስራ ውጭ ሆኗል። መስራቹ የታካሚዎቹን መረጃ መጠበቅ ባለመቻሉ የእስር ቅጣት ተጥሎበታል። ኪቪማኪ በቢትኮይን ያለውን የገንዘብ መጠን ለፖሊስ አልተናገረም። ቢትኮይኑን የሚከፍትበትን የዲጂታል መረጃዎቹን እንደረሳም ተናግሯል።

ራይስኮ መንግስት መግባት ይችል ይሆናል ብላ ተስፋ ታደርጋለች። በእያንዳንዱ ላይ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ ለመገመት ተጨማሪ ወራት ሊወስድ ይችላል ብላለች።

ወደፊት እንደዚህ ያሉ የጅምላ መመንተፍ ጉዳዮችን ለመቋቋም ሕጉ እንዲቀየር ጥሪችም እየቀረቡ ነው።

“ይህ ለፊንላንድ ታሪካዊ ነው። ምክንያቱም የእኛ ስርዓት ይህን ያህል መጠን ላላቸው ተጎጂዎች ዝግጁ አይደለም። የቫስታሞ ምንተፋ ለእነዚህ ትልልቅ ጉዳዮች መዘጋጀት እንዳለብን ጠቁሞናል። ስለዚህ የለውጥ እንደሚኖር ተስፋ አደርጋለሁ። ይህ በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም” ብላለች።