

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር)
ዜና ሀብት የሚያሸሹ ግለሰቦችን ለመቅጣት የሚያስችል አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑ ተነገረ
ቀን: May 5, 2024
የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሀብት ከአገር የሚያሸሹ ግለሰቦች ላይ አስፈላጊውን ቅጣት ለመጣል የሚያስችል አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ይህን የገለጸው በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት 15ኛው የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች ማኅበር ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በተካሄደ መድረክ ሲሆን፣ ከሁሉም የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
ኮሚሽኑ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በአገር ውስጥ ያለውን የሙስና ወንጀል ትግል እንደሚመራ የገለጹት የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር)፣ ‹‹ከአገር የሚሸሸውን ሀብት ለመቆጣጠር ሥራዎች መጠናከር ይገባቸዋል፡፡ ለዚህም ተገቢውን ቅጣት ለመጣል የሚያስችል አዋጅ እየተዘጋጀ ነው፤›› ብለዋል፡፡
አዋጁ ያካተታቸው ዝርዝር ጉዳዮች ወደፊት ይፋ እንደሚደረጉ ለሪፖርተር የገለጹት ሳሙኤል (ዶ/ር)፣ የፍትሕ ሚኒስቴርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን አንድ ላይ በመሆን በዋናነት አዋጁን እያዘጋጁ መሆናቸውንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም እየተሳተፉበት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ ፖሊስ፣ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎትና ሌሎችም ተቋማት በጋራ በመሆን የሚሸሹ ሀብቶችን ለመከላከል የጋራ ኮሚቴ መቋቋሙንም አስታውሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀረ ሙስና ስምምነትና የአፍሪካ ኅብረት የፀረ ሙስና መዋጊያ ስምምነትን ተግባራዊ እያደረገች መሆኑን፣ ከዚህ ባለፈም ወንጀሉን ለመከላከል በቀጣናው ውስጥ ያሉ አገሮች በጋራ መሥራት እንደሚገባቸው አስረድተዋል፡፡
ከአገር የሸሸ ሀብትን ከማስመለስ አኳያ አገሪቱ ያላት ቁጥጥር ደካማ በመሆኑ ድርጊቱ መበራከቱን፣ የፍትሕ ዘርፉ ከተጠናከረ ግን በርካታ የሀብት ማስመለስ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡ ይህም በብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ እየታየ ያለው አንደኛው ጉዳይ መሆኑንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
ከፍተኛ የሆነ ሀብት ከአገር እየሸሸ ከመሆኑም በላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የሙስና ድርጊት ለመከላከል እንዲቻል በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተቋቋመው ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ ጋር ኮሚሽኑ በጋራ እየሠራባቸው ያሉ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው ሳሙኤል (ዶ/ር)፣ ኮሚሽኑ የኮሚቴው አባል መሆኑን ገልጸው ‹‹መረጃ ማመንጨትና በፀረ ሙስና ትግሉ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ የጋራ ጉዳያችን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከዚያ ባለፈ እያንዳንዱ ተቋም የራሱን ተልዕኮ እንደሚያስፈጽምና የኮሚቴው ውሳኔዎች ውጤታማ መሆን እንዲችሉ እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡
የሙስና ወንጀል የሚፈጸመው በተለያዩ መንገዶች በመሆኑ ለመከላከል እንዲቻል፣ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባና ኃላፊነት እንዳለባቸው በውይይት መድረኩ የተገኙ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ተወካዮች አሳስበዋል፡፡ በተጨማሪም የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች ማኅበርን ለግንኙነት መሣሪያነት በመጠቀም፣ በቀጣናው አገሮች የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎችን መከላከል እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡