የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ጥቃቱን መፈጸሙን አምኗል

ከ 4 ሰአት በፊት

ሐማስ ባስወነጨፋቸው ሮኬቶች ምክንያት እስራኤል የጋዛ የእርዳታ መሸጋገሪያ የሆነውን የከረም ሻሎምን መዝጋቷን አስታወቀች።

እስራኤል በጥቃቱ ሦስት ወታደሮቿ መገደላቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውን ተናግራለች።

መሻገሪያው የምግብ እና የህክምና አቅርቦቶችን ጨምሮ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ጋዛ ከሚገቡባቸው ጥቂት መንገዶች አንዱ ነው።

በግብጽ የሚገኙ አሸማጋዮች በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ እና በሐማስ የተያዙ ታጋቾችን ለማስፈታት ያለመ የሁለት ቀናት ውይይት አድርገዋል።

ውይይቱ እሑድ መጠናቀቁን ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው ሐማስ የልዑካን ቡድኑ ከካይሮ ወደ ኳታር በማቅናት ከአመራሮቹ ጋር እንደሚመክር አስታውቋል።

በሽምግልናው ጥረቶች ላይ የተሳተፉት የሲአይኤ ኃላፊ ዊልያም በርንስ ለተጨማሪ ውይይት ከግብጽ ዋና ከተማ ወደ ዶሃ ማቅናታቸውን ዘገባዎች ጠቁመዋል።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ ታጋቾች እንዲፈቱ፤ ለ40 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና በእስራኤል እስር ቤቶች የሚገኙ በርካታ የፍልስጤም እስረኞችን መፍታትን ያካተተ እንደነበር ይታመናል።

ሐማስ አሁን የቀረበውን ሃሳብ “በአዎንታዊ መልኩ” መመልከቱን ገልጾ፤ ዋናው ነገር ግን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ዘላቂ ወይስ ጊዜያዊ ይሆናል የሚለው ነው ብሏል።

ቡድኑ ማንኛውም ስምምነት ጦርነቱን ለማቆም የተለየ ቁርጠኝነት ሊኖረው እንደሚገባ አጥብቆ እየተናገረ ቢሆንም የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግን ሃሳቡን እሑድ ዕለት ውድቅ አድርገውታል።

“የእስራኤል መንግሥት ይህንን (የሐማስ ጥያቄ) መቀበል አይችልም። የሐማስ ብርጌዶች ከዋሻዎቻቸው ወጥተው ጋዛን እንደገና የሚቆጣጠሩበት፤ ወታደራዊ መሠረተ ልማታቸውን መልሰው የሚገነቡበትን እና ዜጎችን ወደ ማስፈራራት የሚመለሱበትን ሁኔታ ለመቀበል ዝግጁ አይደለንም” ብለዋል።

“ይህ ለእስራኤል መንግስት አስከፊ ሽንፈት ይሆናል” ሲሉም አክለዋል።

የአሁኑ ጦርነት የጀመረው መስከረም 26 የሐማስ ታጣቂዎች የጋዛን ድንበር አቋርጠው ወደ እስራኤል በመግባት አንድ ሺህ 200 ሰዎችን ገድለው ከ250 በላይ ታጋቾችን ከወሰዱ በኋላ ነው። ቡድኑ በብዙ ምዕራባውያን አገራት በአሸባሪነት ተፈርጇል።

የእስራኤል ጦር በጋዛ እያካሄደ ባለው የማያባራ እና የተቀናጀ ጥቃት ከ34 ሺህ 600 በላይ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ ከ77 ሺህ 900 በላይ መቂሰላቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

ናታንያሁ በጋዛ ደቡባዊ ከተማ ራፋህ ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረውን ጥቃት እንዲቀጥሉ የጥምረት መንግስታቸው የቀኝ ዘመም አባላት ግፊት እያደረጉባቸው ነው። በሰሜናዊ እና መካከለኛው ጋዛ አካባቢዎች የሚካሄደውን ጦርነት ሸሽተው 1.4 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች በራፋህ ተጠልለዋል።

አሜሪካ በሲቪል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ የሚችለውን የራፋህ ወረራ ለመደገፍ ፍቃደኛ አትመስልም። እስራኤል በመጀመሪያ የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያንን ለመጠበቅ ያወጣችውን ዕቅድ የማየት ፍላጎት አላት።

የእስራኤል መንግሥት በአገር ውስጥም ከፍተኛ ጫና ገጥሞታል።

መስከረም 26 በሐማስ ከታገቱት 252 ታጋቾች መካከል 128ቱ እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም። ከእነዚህ መካከል ቢያንስ 34ቱ ሞተዋል ተብሎ ይገመታል።

የሐማስ ታጣቂ ክንፍ የሆነው አልቃሳም ብርጌድ በከረም ሻሎም ማቋረጫ ላይ ጥቃቱን የፈጸመ መሆኑን እና በአጭር ርቀት ሮኬቶች ወታደሮችን ዒላማ ማድረጉን አስታውቋል።

በደቡባዊ ጋዛ ከሚገኘው ራፋህ ማቋረጫ አካባቢ ከከረም ሻሎም 3.6 ኪሜ ርቀት ላይ10 ሚሳኤሎች መተኮሳቸውን የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት አስታውቋል።

የሚሳኤል ማስወንጨፊያው ከሲቪሎች መጠለያ 350 ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝ እና በአካባቢው ከሚገኝ የወታደራዊ ማዕከል ጋር ጥቃት እንደፈጸመበት የእስራኤል ጦር ጠቅሷል።

“የአሸባሪው ድርጅት የሰብአዊ መገልገያዎችን እና ቦታዎችን ሽፋን ማድረጉን እና የጋዛን ሲቪል ህዝብ እንደጋሻ መጠቀሙን የሚያሳይ ሌላ ግልጽ ምሳሌ” ሲልም ጥቃቱን ገልጾታል።

የተኩስ አቁም ድርድሩ ለወራት ምንም ውጤት ሳያስገኝ የቀጠለ ሲሆን ከህዳር ወር መገባደጃ ጀምሮም ውጊያው ከመቀጠሉም ባለፈ ታጋቾችንም ማስፈታት አልተቻለም።

አዲስ ስምምነት ይደረሳል ተብሎ በተደጋጋሚ ተስፋ ቢደረግም ተቀባይነት ሳያገኝ ውድቅ ሆኗል።