የነጭ ፎስፈረስ ጥቃት የፈጠረው ጭስ
የምስሉ መግለጫ,የነጭ ፎስፈረስ ጥቃት የፈጠረው ጭስ

ከ 7 ሰአት በፊት

ላለፉት ስድስት ወራት እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ ድንበር ላይ የነጭ ፎስፈረስ ጥቃቶችን ሰንዝራለች። ይህ ንጥረ ነገር መርዛማ ጋዝ ከመሆኑ አንጻር ለዐይን እና ለሳንባ ጎጂ ከመሆን ባለፈ ከባድ ቃጠሎ ሊያስከትልም ይችላል። በዚህ ምክንያትም በዓለም አቀፍ ሕጎች ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግበታል።

የእስራኤል ጦር በጋዛ እና በሊባኖስ በሚገኙ ታጣቂ ኃይሎች ላይ ይህን አወዛጋቢ መሣሪያ መጠቀማቸው ሕጋዊ ነው ብሏል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በበኩላቸው እንደ ጦር ወንጀል ታይቶ ሊመረመር ይገባዋል ሲሉ ይከራከራሉ። እስራኤል በሁለቱም አገራት ነጭ ፎስፈረስ መጠቀሟን በተመለከተ አሜሪካ ምርመራ እንደምታደርግ አስታውቃለች።

ይህን የመሰሉን ጋዝ ለሲቪሎች ቅርብ በሆኑ አካባቢዎች በመጠቀሙ የእስራኤል ጦር ዓለም አቀፍ ሕግን እየጣሰ ነው? ወይስ በጦርነት ወቅት የመጠቀም መብት አለው?

“እንደ ነጭ ጭጋግ ይጓዛል። መሬት ሲደርስ ግን ወደ ዱቄትነት ይለወጣል።”

አሊ አሕመድ ሳምራ ከደቡብ ሊባኖስ የመጣ የ48 ዓመት አርሶ አደር ነው። ጥቅምት 8/2016 ዓ.ም. እራሱን በጥቅጥቅ ነጭ ጭስ ውስጥ ተውጦ እንዳገኘው ይናገራል።

“ነጭ ሽንኩርት ነጭ ሽንኩርት ይሸታል ቢሉም ከዚያ በጣም የከፋ ሽታ አለው። ሽታውን መቋቋም የማይቻል ነበር። ከፍሳሽ ቆሻሻም ይከፋል” ብሏል።

አሊ አሕመድ

አሊ ስለነጭ ፎስፈረስ ጥቃትን እየገለጸ ነው።

ነጭ ፎስፎረስ በጣም ተቀጣጣይ እና መርዛማ ነው።

“እንባ ከዐይኖቻችን መፍሰስ ጀመረ። አፍ እና አፍንጫችንን በውሃ በራሰ ጨርቅ ባንሸፍን ኖሮ ዛሬ በሕይወት ላንኖር እንችላለን” ይላል አሊ።

ባለፈው መስከረም በጋዛ ከተጀመረው ጦርነት ወዲህ በእስራኤል እና በሊባኖስ ድንበር ላይ ግጭቱ ተባብሶ በሁለቱም ወገኖች ላይ ጉዳት በማድረስ በሺህዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀልም ምክንያት ሆኗል።

ከኢራን እና ከሐማስ ጋር ቁርኝት ያለው ሂዝቦላህ በዓለም ላይ ካሉት እጅግ በጣም ከታጠቁ መንግሥታዊ ካልሆኑ ኃይሎች አንዱ ነው።

በሂዝቦላህ ተዋጊዎች በየቀኑ በሚሰነዘረው የሮኬት እና የሰው አልባ አውሮፕላኖች የአየር ጥቃት ምክንያት የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት (አይዲኤፍ) የአጸፋ ምላሽ እየሰጠ ነው። ጦሩ ፎስፈረስን በመጠቀም ላይ ይገኛል።

ነጭ ፎስፎረስ ከቅርፊቱ ወጥቶ ከኦክሲጅን ጋር ሲገናኝ ወፍራም ጭስ ይፈጥራል። ይህ መሬት ላይ ላሉ ወታደሮች የጠላቶችን የዕይታ በመሸፈን አፋጣኝ ከለላ ይሰጣል።

ይህም በተወሰኑ ሁኔታዎች ውስጥ በጣም ውጤታማ እና ሕጋዊ ወታደራዊ ስልት ነው። ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር ግን በግጭቶች ወቅት ሲቪሎችን መጠበቅ የሁሉም ወገኖች ኃላፊነት ነው።

የነጭ ፎስፈረስ ጭስ
የምስሉ መግለጫ,የነጭ ፎስፈረስ ጭስ

የሂዝቦላህ ተዋጊዎች ከሁለት እስከ አራት ሰዎች ባላቸው አነስተኛ ቡድኖች እንደሚንቀሳቀሱ ይታወቃል። ጫካውን እንደሽፋን በመጠቀም ሚሳኤሎችን እና ሮኬቶችን ከድንበር ባሻገር ወደሚገኙ የእስራኤል ጦር አባላት ይተኩሳሉ። ተዋጊዎቹን በጢስ ማጥለቅለቅን እስራኤላውያን እንደ አንድ ዒላማ ማሳኪያ መንገድ እየተጠቀሙበት ሊሆን ይችላል።

ጥቅምት አጋማሽ አካባቢ የአሊ መንደር በፎስፈረስ በተመታበት ወቅት በአካባቢው ምንም የታጠቁ ቡድኖች እንዳልነበሩ ተናግሯል።

“ሂዝቦላህ ቢኖር ኖሮ ሰዎች መሞት ስለማይፈልጉ ከአካባቢው እንዲለቁ ይነግሯቸው ነበር። ሂዝቦላህ ግን አልነበረም” ብሏል።

ወደ ድሃይራ ቀድመው ከደረሱት በጎ ፈቃደኛ የህክምና ባለሙያዎች መካከል አንዱ ካሊድ ቁራይተም ነበር።

“ራሳችውን የሳቱ ሰዎችን ማስወጣት ጀመርን። ሰዎችን ለመርዳት እየሞከረን ባለበት ወቅት የነፍስ አድን ቡድኑ ጥቃት ደረሰበት” ሲል ካሊድ ተናግሯል።

“ሦስት ጊዜ ተኮሱብን። ሰዎችን እንዳንረዳ ለማስቆም ወይም የፍርሃት ድባብ ለመፍጠር የታለመ ነው” ብሏል።

ካሊድ ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎችን ጣሊያን ወደሚባለው ሆስፒታል ማዛወሩን ያስታውሳል። ከእነዚህ ውስጥ አባቱ ኢብራሂምም ይገኙበታል።

የ65 ዓመቱ ኢብራሂም በከባድ የመተንፈስ ችግር ምክንያት ለሦስት ቀናት ሆስፒታል ቆይቷል። ህክምናውን የሰጣቸው ዶ/ር መሐመድ ሙስጠፋ ለነጭ ፎስፎረስ የተጋለጡ ብዙ ታካሚዎችን እንዳከመ ተናግሯል።

“ታካሚዎች በከባድ የመታፈን፣ የበዛ ላብ፣ ሥር የሰደደ ትውከት እና ያልተስተካከለ የልብ ምት እያሳዩ መጥተዋል። ነጭ ሽንኩርት ነጭ ሽንኩርት ይሸታሉ። የደም ውጤታቸውም ለነጭ ፎስፈረስ መጋለጣቸውን አረጋግጧል” ብሏል ዶ/ር መሐመድ።

የነጭ ፎስፈረስ ጭስ
የምስሉ መግለጫ,የነጭ ፎስፈረስ ጭስ

ኢብራሂም ከሦስት ወራት በኋላም ዐይኖቹ እንደቀሉ ናቸው። በእጆቹ እና በእግሮቹ ላይ ያለው ቆዳ በሽፍታ ከመሸፈን ባለፈ መላጥ ጀምረዋል። ይህ ሁሉ በነጭ ፎስፈረስ ምክንያት እንደሆነ ሐኪሞቹ ነግረውታል።

“ከ1970ዎቹ ጀምሮ ጦርነት ውስጥ ኖረናል። እንደዚህ ዓይነት ነገር ግን አልነበረም። ለቤታችን ቀረብ ብሎ ፍንዳታዎች ነበሩ” ብሏል ኢብራሂም።

ለመሸሽ ሲሞክር አንደኛው ፍንዳታ ከመኪናው በስድስት ሜትሮች ርቀት ላይ መውደቁን ተናግሯል። የእስራኤል ጦር የስለላ ድሮኖችም ከላይ ሲያንዣብብቡ ነበር።

“ሊያዩን ይችሉ ነበር። በግዴለሽነት እየተኮሱ ነበር” ብሏል ኢብራሂም።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል “ቢያንስ ዘጠኝ ሰላማዊ ሰዎችን ያቆሰለ እና ቁሶችን ያወደመ እንዲሁም በሕገ-ወጥ መንገድ የተደረገ ጥቃት በመሆኑ” በዳሂራ ላይ የተፈጸመው ጥቃት እንደ ጦር ወንጀል መመርመር አለበት ብሏል።

ነጭ ፎስፈረስ ‘በግዴለሽነት’ እና ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ጥቅም ላይ መዋሉን ለተሰጠው ምስክርነት የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት “ጦራችን መመሪያዎች ነጭ ፎስፈረስ ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ጥቅም ላይ እንዳይውል ያስገድዳል” ሲል ምላሽ ጦሩ ሰጥቷል።

የነጭ ፎስፈረስ ጥቅም ላይ ስለመዋሉ ማረጋገጫ

በአሊ መንደር ላይ ከደረሰው ጥቃት በኋላ ሪፖርቶች በበይነ መረብ መውጣት ጀመሩ። የእስራኤል ጦር መጀመሪያ ላይ ነጭ ፎስፎረስ መጠቀሙን አስተባብሏል። በኋላ ግን “በዓለም አቀፍ ሕጎች መሠረት” መጠቀሙን አምኗል።

ቢቢሲ ማስረጃዎቹን በማጣራት ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ነጭ ፎስፎረስ በዳሂራ እና በድንበር አካባቢ ባሉ ሌሎች ሦስት መንደሮች ጥቅም ላይ መዋሉን ማረጋገጥ ችሏል።

ቢቢሲ በሁለት ሲቪል ቤቶች መካከል የወደቀ ቁርጥራጭ ላይ ማጣሪያ አድርጓል። ምርመራው የተደረገው በታዋቂ የኬሚስትሪ ፕሮፌሰር ነው። በፀጥታ ስጋት ምክንያት ፕሮፌሰሩ ማንነቱ እንዳይገለጽ ጠይቋል።

ፕሮፌሰሩ የጋዝ ጭንብል እና የሰውነት መከላከያ ልብስ አጥልቆ በብረት ቁርጥራጮቹ ላይ ምርመራ አድርጓል።

“ይህ የ155 ሚሊሜትር የሆዊተዘር ጥይት አካል ነው። ኤም825ኤ1 የሚለው መረጃ የሚያመለክተው የነጭ ፎስፈረስ ጥይት ነው። ስሪቱም የአሜሪካ ነው” ብሏል።

እሳት ወደ ቁርጥራጮቹ ቀረብ ሲያደርግ በፍጥነት ይያያዛል።

“ይህን ቁሳቁስ በቆዳዎ ላይ በሚጣበቅበት ጊዜ ከልብስዎ ላይ ለማስወገድ ሲሞክሩ ያስቡት።”

ከ30 ቀናት በኋላ ጭምር የነጭ ፎስፎረስ ቅሪቶች ሊቀጣጠሉ ይችላሉ።

እስራኤል ሰዎችን ከድንበር አካባቢዎች ለማባረር ሆን ብላ ነጭ ፎስፈረስ ትጠቀማለች ሲል ካሊድ ይከሳል።

“ቆንጆ የገጠር ኑሮ ነበረን” ሲል ተናግሯል። “የወይራ ዛፎችን እና የአቮካዶ የአትክልት ቦታዎችን ለማቃጠል ሆን ብለው በደን የተሸፈኑ አካባቢዎችን በፎስፈረስ ቦምብ ማጥፋት ጀመሩ።”

“ጦራችን በሊባኖስ ውስጥ ያሉ ሰላማዊ ዜጎችን ከድንበር ለማራቅ ፎስፈረስ ጥቅም ላይ ያውላል የሚለውን ክስ በሙሉ ውድቅ ያደርጋል” ሲል እስራኤል ጦር ምላሽ ሰጥቷል።

የመሳሪያው ቅሪት
የምስሉ መግለጫ,የመሳሪያው ቅሪት

እስራኤል ሕግ ጥሳለች?

ነጭ ፎስፎረስ እንደ ኬሚካል መሳሪያ አልተመደበም። ተቀጣጣይ መሳሪያ የሚለው ውስጥ ስለመመደቡ እንኳን አከራካሪ ነው።

በተባበሩት መንግሥታት የመደበኛ የጦር መሳሪያዎች ስምምነት (ሲሲደብሊው) መሠረት እሳት ለመፍጠር ወይም ሰዎችን ለማቃጠል በተዘጋጁ የጦር መሳሪያዎች ላይ ገደቦች አሉ።

እስራኤልን ጨምሮ አብዛኞቹ አገራት ግን ነጭ ፎስፎረስ በዋነኝነት እሳትን ለመፍጠር ሳይሆን፣ የጭስ መጋረጃ ለመፍጠር ጥቅም ላይ ከዋለ ሕጉ ተግባራዊ አይደረግበትም።

ሂዩማን ራይትስ ዋች ግን በዚህ አይስማማም። በሲሲደብሊው ውስጥ በጣም ብዙ “ክፍተቶች” አሉ ይላሉ።

“ሕጉ በተለይም ተቀጣጣይ የጦር መሣሪያዎችን ከሚገልጸው ዝርዝር ጋር በተያያዘ ብዙ ክፍተቶች አሉበት። በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ መሠረት ግን ሁሉም አካላት በሲቪል ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስወገድ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። በተለይም ነጭ ፎስፎረስ ያላቸውን መሳሪያዎች ሲጠቀሙ” ሲሉ የተቋሙ ተመራማሪ ራምዚ ካይስ ተናግረዋል።

እስራኤል ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግን መጣሷን በማረጋገጥ ረገድ አንድ “የማስረጃ ግጭት አለ” ሲሉ ገለልተኛው የሕግ ባለሙያ እና ወታደራዊው ኤክስፐርት ፕሮፌሰር ቢል በዝቢ ገልጸዋል።

“እስራኤላውያን ዓላማቸው የጭስ መጋረጃ መፍጠር ነው ይላሉ። የመንደሮቹ ነዋሪዎች ደግሞ ምንም ዓይነት ታጣቂዎች ስላልነበሩ የጭስ መጋረጃ ለመፍጠር በቂ ምክንያት አልነበረም ይላሉ። ነጭ ፎስፈረስ ጥቅም ላይ የዋለው ለዚህ ዓላማ ነበር? መልሱን ለማወቅ ጥቃቱ እንዲፈጸም ባዘዙት ሰዎች አዕምሮ ውስጥ መሆንን ይጠይቃል” ብለዋል።

“ተመጣጣኝነትም” ቁልፍ ነገር ነው ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

“እየተነጋገርን ያለነው ከጥቃቱ በፊት ሊያገኙ ያሰቡት ውጤት ከጠበቁት የሲቪል ጉዳት እና በሲቪል ንብረቶች ላይ ከሚደርሰው ጉዳት መጠን በላይ መሆኑን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው።”

ይህም ቢሆን ግን ጥቃቱ ላይ በሚወስኑት ሰዎች አዕምሮ ውስጥ ያለው እና ዒላማቸው ምንድነው በሚለው ይወሰናል ብለዋል።

በዳሂራ ዒላማው ምን እንደሆነ የተጠየቀው የእስራኤል ጦር “እነዚህ በምሥጢር የሚያዙ የአሰራር መመሪያዎች ናቸው” ሲል ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥቷል።

የነጭ ፎስፈረስ ጭስ