
7 ግንቦት 2024, 08:10 EAT
ተሻሽሏል ከ 1 ሰአት በፊት
የእስራኤል ጦር በምስራቃዊ ራፋህ የማያባራ ጥቃት ሌሊቱን ከፈጸመ በኋላ ጋዛን እና ግብጽን የሚያገናኛቸውን የድንበር ማቋረጫ ራፋህን መቆጣጠሩን አስታወቀ።
እስራኤል ሰላማዊ ዜጎች እንዲወጡ ካስጠነቀቀች ከአንድ ቀን በኋላ እርዳታ ወደ ጋዛ በሚገባበት በኩል ታንኮቿን አሰልፋለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሐማስ የተስማማበትን የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት “ከእስራኤል መሠረታዊ መስፈርቶች የራቀ” ቢሆንም ድርድሩ ይቀጥላል ሲሉ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህንን የገለጹት ሐማስ የኳታር እና የግብጽ ሸምጋዮች ያቀረቡትን የእርቅ ስምምነት መቀበሉን ተከትሎ ነው።
የፍልስጤም ተደራዳሪ አባላት “አሁን ውሳኔው የእስራኤል ነው” ብለዋል።
የእስራኤል የጦር ካቢኔ እስራኤል በራፋህ እየፈጸመችው ያለው ጥቃት እንዲቀጥል ትዕዛዝ ቢያስተላልፍም ለድርዱሩ ልዑካኑን ወደ ካይሮ እንደሚልክ አስታውቋል።
ቀደም ሲል የእስራኤል ጦር ፍልስጤማውያን የራፋህን ምሥራቃዊ ክፍል ለቀው እንዲወጡ ካስጠነቀቀ በኋላ በግብጽ ድንበር ላይ በምትገኘው ከተማ የአየር ጥቃት ፈጽሟል።
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ሰኞ ዕለት በተሽከርካሪዎች ወይም በጋሪ ታጭቀው ሲወጡ ታይተዋል።
እስራኤል 1.4 ሚሊዮን ሰዎች በሚኖሩባት ከተማ ላይ “በሐማስ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት” ልትሰነዝር እንደምትችል ስታስፈራራ ቆይታለች። የከተማዋ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ከሌሎች የጋዛ አካባቢዎች ጥቃቶችን ሸሽተው የተጠለሉባት ናት።
ሰኞ ዕለት የናታንያሁ ጽህፈት ቤት ባወጠው መግለጫ “የሐማስ ሃሳብ ከእስራኤል መሠረታዊ ፍላጎቶች የራቀ ቢሆንም፤ በእስራኤል ተቀባይነት በሚያገኝ ሁኔታ ከስምምነት ለመድረስ የሚያስችለውን ዕድል ለመጠቀም እስራኤል የተደራዳሪ ልዑካንን ትልካለች” ብሏል።
የእስራኤል የጦር ካቢኔ “ዓላማችንን ለማሳካት እና በሐማስ ላይ ወታደራዊ ጫና በማሳደር ታጋቾችን ለማስለቀቅ፤ የሐማስ ወታደራዊ እና የአስተዳደራዊ አቅምን ለማጥፋት እና ወደፊትም ጋዛ የእስራኤል ላይ ስጋት እንዳትሆን” የራፋህ ዘመቻ እንዲቀጥል ወስኗል ሲል አክሏል።
ሐማስ የፖለቲካ መሪው እስማኤል ሃኒዬህ ቀደም ሲል ለኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር እና ለግብጽ የስለላ ኃላፊ “የተኩስ አቁም ስምምነትን በተመለከተ ያቀረቡትን ሃሳብ መቀበላቸውን” የሚገልጽ መግለጫ አውጥተዋል።
- የወጪ ገደቡ እጅ ያጠራቸውን የኢትዮጵያ ክለቦች ይታደግ ይሆን?ከ 7 ሰአት በፊት
- የሽግግር ፍትህ ኢትዮጵያን እስከ የት ያሻግራታል?6 ግንቦት 2024
- አሜሪካዊው ወታደር በሩሲያ በስርቆት ወንጀል ተከሰሰከ 7 ሰአት በፊት
ሐማስ ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ “የጥቃት እንቅስቃሴን እስከመጨረሻው” ለማስቆም መስማማቱን ጉዳዩን የሚያውቁ ከፍተኛ የፍልስጤም ባለስልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህም ሐማስ የትጥቅ ትግሉን ሊያቆም እንደሚችል ፍንጭ ቢሰጥም ተጨማሪ ዝርዝር መግለጫ አልተሰጠም። ስምምነቱ በሁለት ምዕራፍ የተከፈለ ነው።
በመጀመሪያው ምዕራፍ በእስር ላይ የሚገኙትን ሴት የእስራኤል ወታደሮች ከእስር መልቀቅን ያካትታል። በእያንዳንዱ ወታደርም የዕድሜ ልክ የተፈረደባቸውን ጨምሮ በእስራኤል እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ 50 ፍልስጤማውያን እስረኞች ይፈታሉ።
በዚህ ጊዜ የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ውስጥ ይቆያሉ። የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሥራ ላይ በዋለ በ11 ቀናት ውስጥ እስራኤል በግዛቱ መሃል የሚገኙትን ወታደራዊ ተቋሞቿን በማፈራረስ ከሳላህ አል-ዲን መንገድ እና ከባህር ዳርቻው መንገድ ትወጣለች።
ከ11 ቀናት በኋላም የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን ወደ ሰሜን ጋዛ እንዲመለሱ ይፈቀድላቸዋል።
እንደ ባለሥልጣኑ ገለጻ ከሆነ ገለጻ በሁለተኛው ምዕራፍ “ዘላቂ የመረጋጋት ጊዜ” እና የጋዛን እገዳ ሙሉ በሙሉ ማንሳትን ያጠቃልላል።
ከኳታር እና ከግብጽ ጋር በአደራዳሪነት ስትሠራ የቆየችው አሜሪካ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር በኩል የሐማስን ምላሽ እየገመገመች እና “ከአጋሮቻችን ጋር እየተወያየን ነው” ብላለች።
የአሁኑ ጦርነት የጀመረው መስከረም 26 የሐማስ ታጣቂዎች ወደ ደቡብ እስራኤል ዘልቀው በመግባት ወደ አንድ ሺህ 200 የሚጠጉ ሰዎችን ከገደሉ እና ከ250 በላይ ታጋቾችን ከወሰዱ በኋላ ነው።
እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ እያደረገች ባለው የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት 34ሺህ 683 ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል፤ 70ሺህ 18 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስትር እንደሚለው ከሟቾቹ መካከል የሚበዙት ሴቶችና ሕጻናት ናቸው።
ከዚህ ቀደም ኳታር ሁለቱን ተዋጊዎች አሸማግላ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ተደርጎ፣ 105 እስራኤላዊ ታጋቾች መለቀቃቸው አይዘነጋም።