
ከ 4 ሰአት በፊት
የሰሜን ኮሪያን ፕሮፓጋንዳ ማሽን ለዘመናት ሲዘውሩ የነበሩት ሰው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
ኪም ኪ ናም መሞታቸው የተነገረው ትናንት ሲሆን 94 ዓመት ደፍነው ነበር።
የሞታቸው ምክንያት የዕድሜ መግፋትና ይህን ተከትሎ የመጣ የጤና መጓደል ነው ተብሏል።
ኪም ኪ ናም ከፈረንጆቹ 2022 ጀምሮ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሕክምና ሲከታተሉ ቆይተዋል።
ኪም ኪ ናም ለዐሥርታት የሰሜን ኮሪያን የፕሮፓጋንዳ ክፍል ሰጥ-ቀጥ-ለጥ አድርገው ሲመሩ የቆዩ ጉምቱ ባለሥልጣን ነበሩ።
በተለይም የሰሜን ኮሪያ አባት ለሚባሉት ኪም ኢል ሱንግም ሆነ እርሳቸው ለተኩት ኪም ጆንግ ኢል ቅርብ የነበሩ ናቸው።
በቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ላይ የሰሜን ኮሪያው የአሁኑ መሪ ኪም ጆንግ ኡን መገኘታቸው ሰውዬው ምን ያህል ለኪም ቤተሰብ ቅርብ መሆናቸውን ማሳያ ነው።
ታላቁ መሪ ኪም በሰውየው ቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር “ኪም ኪ ናም ለአገራቸው የነበራቸው ታማኝነት ወደር አልነበረውም” ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል።
የደቡብ ኮሪያ ሚዲያ ሰውየውን ከናዚ ጀርመን የፕሮፓጋንዳ ሚኒስትር ጆሴፍ ጎብልስ ጋር አነጻጽሮ ዘገባ ሠርቷል።
የሂትለር ቀኝ እጅ የነበረው ጆሴፍ ጎብልስ “ዉሸትን እውነት እስክትመስል ድረስ ደጋግማት-እውነት ትሆን ዘንድ” በሚለው ፍልስፍናው ይታወቃል።
ኪም ኪ ናም ምንም እንኳ በደም የገዥው ኪም ቤተሰብ ባይሆኑም ቤተሰቡንና ሥርዓቱን በሙሉ ታማኝነት ነው ያገለገሉት።
በፈረንጆቹ 1966 በፕዮንግያንግ ”የፕሮፓጋንዳና ሕዝብ ማነቃቂያ መሥሪያ ቤት” ሥራ የጀመሩት ኪም ኪ ናም በምክትል ኃላፊነት አገልግለዋል።
ከዚያ በኋላ መሥሪያ ቤቱን በከፍተኛ ኃላፊነት ያገለገሉ ሲሆን የአሁኑ የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም አባት ጋር ወዳጅ ነበሩ።
- የሰሜን ኮሪያው ኪም ሴት ልጅ ለ5ኛ ጊዜ በአደባባይ መታየቷ ለምን አነጋጋሪ ሆነ?12 የካቲት 2023
- የሰሜን ኮሪያዋ ኃያል ሴት ማን ናት?18 መጋቢት 2021
- የሴት ልጅ ግርዛትን የተመለከተው አወዛጋቢው የኢትዮጵያ ዑለማዎች ውሳኔከ 5 ሰአት በፊት
አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚሉት ኪም ኪ ናም ከኪም ጆን ኢል (የአሁኑ የአገሪቱ መሪ አባት) ጋር አብሮ መዝናናትና አንድ ሁለት እስከመባባል የሚያደርስ ወዳጅነት ነበራቸው።
በ1970 የአገሪቱ ዋንኛ የፕሮፓጋንዳ ጋዜጣ ለሆነው ”ሮዶንግ ሲንሙን” ኃላፊ ተደርገው ተሾመዋል።
ከዚያ በኋላ ሰሜን ኮሪያ ከኪም ኢል ሱንግ ወደ ኪም ጆንግ ኢል ሽግግር ስታደርግ ይህንኑ ሂደት አሳልጠዋል።
በሰሜን ኮሪያ የነበሩ መፈክሮችና ለፖለቲካ ቅስቀሳ የዋሉ ኅትመቶች ፈጣሪና ደራሲ ሆነው የቆዩት ኪም ኪ ናም በሥነ ጥበብ፣ በጋዜጣና በቴሌቪዥን የፕሮፓጋንዳ አስተባባሪና መሪም ነበሩ።
በፈረንጆቹ በ2015 የአገሪቱ ሚዲያ ረዥም፣ መልከ መልካም መነጽር ያደረጉ ዕድሜያቸው በ80ዎቹ የሚገመት ሰው ከኪም ጆንግ ኡንና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው ጋር ሆነው ማስታወሻ ሲይዙ አሳየ።
እኚያ ሰው ኪም ኪ ናም ነበሩ።
በፈረንጆቹ 2010 ኪም ኪ ናም ጡረታ ከወጡ በኋላ ከፍተኛውን የፕሮፓጋንዳ ኃላፊነት ለኪም ኦን ጁን እህት፣ ኪም ዮ ጆንግ አስረክበዋል።
አሁንም ይህ የፕሮፓጋንዳ ክፍል የሚዘወረው በኒህ ኃያል ሴት ነው።
ኪም ኪ ናም በጡረታ ላይ ሳሉም አልፎ አልፎ በገዢው ቤተሰብ አንዳንድ መሰናዶዎች ተጋብዘው ይታዩ ነበር።