በአንድ የቀድሞ ሆስፒታል መታጠቢያ ቤት ውስጥ የምትኖረው ፋልዲላህ

ከ 5 ሰአት በፊት

በዓለማችን እኩልነት ከማይታይባቸው አገሮች አንዷ ናት ደቡብ አፍሪካ።

የአገሪቷ በርካታ ጥቁሮች በድህነት የሚማቅቁባት፣ ጥቂት ነጮች ተንደላቀው የሚኖሩባት።

የምጣኔ ሀብት አፓርታይድ የቀጠለባት።

የአንዳንዶቹ ደግሞ ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል የሚያስብል ነው።

ጀሚላ የምትኖርበት ስፍራ በአንድ ወቅት የአስከሬን ማስቀመጫ ክፍል፣ የፋልዲላህ ደግሞ መታጠቢያ ቤት ነበር። የቤቪል ደግሞ በአንድ ወቅት የስኳር መድኃኒቱን ሊወስድ የመጣበት ዶክተር ቢሮን መኖሪያ ቤቱ አድርጓል።

ሦስቱም በደቡብ አፍሪካዋ ኬፕታውን በሚገኝ የቀድሞ ሆስፒታል ውስጥ ኑሯቸውን አድርገዋል።

እነዚህ ነዋሪዎች በእንግሊዝኛው ‘ስኳተር’ ይሰኛሉ።

ይህም መንግሥት በተመጣጣኝ ዋጋ የመኖሪያ ቤት የመስጠት ግዴታውን ካልተወጣ በተቃውሞ እና ያለ ባለሥልጣናቱ ፍቃድ የሕዝብ ህንጻዎችን እና መገልገያዎችን መኖሪያ ማድረግ ነው ሃሳቡ።

የአገሪቱን ጥቁሮች ከሰው በታች ያደረገው የጨቋኙ አፓርታይድ ሥርዓት መገርሰስ ለበርካቶች የፖለቲካ መብቶች እና ነጻነትን አምጥቷል።

ሆኖም የበርካታ ጥቁሮች ኑሮ በተለይም መሠረታዊ በሆነው መኖሪያ ቤት ላይ ያለው ሁኔታ ምንም አለመቀየሩ የምጣኔ ሀብት አፓርታይድ መቀጠሉ ማሳያ ነው።

የበርካታ ሰዎች ሕይወት ከገበረበት ትግል በኋላ ሥልጣን የተቆጣጠረው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) በመኖሪያ ቤት ፖሊሲው የአፓርታይድን ሥርዓት ከመቀልበስ ይልቅ ሆን ብሎም ባይሆን አጠናክሮ ቀጥሎበታል።

ከሰባት ዓመታት በፊት ‘ሪክሌይም ዘ ሲቲ’ [ከተማችንን የራሳችንን እናድርግ] የተሰኘው እንቅስቃሴ ተሟጋቾች አገልግሎት ያቆመውን ውድስቶክ ሆስፒታልን ተቆጣጠሩ።

በርካታ ጥቁሮችን እና ድብልቅ ዘር ያላቸውን ደቡብ አፍሪካውያንን ከሥራ ዕድሎች እና ከመሠረታዊ አገልግሎቶች ያገለለውን ይህንን ፖሊሲም ለማስተካከል፤ በከተማዋ አማካኝ ቦታ ያለውን ህንጻ ተሟጋቾች እንደተቆጣጠሩ ከመሪዎቹ አንዱ የሆነው ቤቪል ሉካስ ያስረዳል።

“ጥቁር እና ድብልቅ ዘር ያላቸውን ደቡብ አፍሪካውያንን ወደ ከተማዋ ዳርቻ ገፍቶ በድህነት እንዲማቅቁ ያደረጓቸውን የዘረኝነት ሕጎች በደቡብ አፍሪካ የሰፈነው አዲሱ የኢኮኖሚ አፓርታይድ ተክቶታል” ሲል ቤቪል ለቢቢሲ ገልጿል።

የአፓርታይድ መገርሰስን ተከትሎ ለነጮች ብቻ በነበሩት የከተማ ማዕከላዊ ስፍራዎች መንቀሳቀስ ቢችሉም አከራዮች የሚጠይቁት ገንዘብ የሚቀመስ ስላልሆነም ለጥቁሮች በእነዚህ ስፍራዎች መኖር የሚታሰብ አይደለም።

ለጀሚላ ዳቪድስ የመኖሪያ ስፍራ ማዕከላዊ መሆኑ መሠረታዊ ነው ትላለች።

“ወደዚህ የመጣሁት ኦቲስቲክ በሆነው ልጄ ምክንያት ነው። የልጄ ትምህርት ቤት በአቅራቢያው ነው የሚገኘው። ሁሉም ነገር ለእሱ ተመችቶታል” በማለት ታስረዳለች።

ተሟጋቾቹ ለመኖሪያነት የተቆጣጠሩት ሆስፒታል
የምስሉ መግለጫ,ተሟጋቾቹ ለመኖሪያነት የተቆጣጠሩት ሆስፒታል

በዚህም የተነሳ ቤተሰቧን በቀድሞ የሆስፒታሉ አስከሬን ማስቀመጫ ክፍል አስፍራለች። ሌላኛዋ በዚህ ሆስፒታል መኖሪያዋን ያደረገችው ፋልዲላ ፒተርሰን የሆስፒታሉን መታጠቢያ ቤት ወደ መኖሪያ ቀይራለዋለች። ሽንት ቤቱ ያለበትን አካባቢ ወደ ኩሽና እና እጅ መታጠቢያውን ደግሞ ወደ መኝታ ቤት እንደቀየረችው ለቢቢሲ አሳይታለች።

ከዚህ ቀደም “በዓመት ውስጥ 10 ጊዜ ያህል በአከራዮች ከመኖሪያዋ እንደወጣች” ታስረዳለች። ነገር ግን በዚህ ሆስፒታል ኑሯዋን ካደረገች በኋላ “ሕይወቴን ለማሻሻል ዕድል አግኝቻለሁ። ለከተማውም ቅርብ ስለሆነ በነጻነት እንድንቀሳቀስ እና ሥራዬንም በቀላሉ እንዳከናውን አድርጎኛል” ትላለች።

የከተማው አስተዳደር ይህ የቀድሞ ሆስፒታል ለመኖሪያ ስፍራነት መልማት እንደሚችል ቢስማማም፤ አሁን ያሉት ነዋሪዎች ግን ሕገወጥ ናቸው በማለት ከፈረጀ በኋላ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት ሊለቁ ይገባል ይላል።

ኤኤንሲ ከ30 ዓመት በፊት ሥልጣን ሲቆጣጠር በአፓርታይድ ሥርዓት ምክንያት ምቹ መኖሪያ ለተነፈገው አብዛኛው ጥቁር ሕዝብ መኖሪያ ቤት እሰጣለሁ በሚል የነጻነት ቻርተር በተሰኘው ፖሊሲው ቃል ገብቶ ነበር።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከሦስት ሚሊዮን በላይ መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ የተወሰኑትን በነጻ ወይም ከገበያ በታች በሆነ ዋጋ እንዲከራዩ አድርጓል።

ነገር ግን የመንግሥት ቤቶችን ለማግኘት ረጅም ዓመታትን መጠበቅ ግድ ይላል።

ፋልዲላህም ሆነ ጀሚላ 30 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ጠብቀዋል። አብዛኞቹ መኖሪያ ቤቶች የተገነቡት መሬት ርካሽ በሆነበት ከመሃል ከተማ ርቀው ነው። ይህም ሁኔታ በአፓርታይድ ወቅት የነበረውን ሥርዓት በማስቀጠል አሁንም ሃብታም በሚባሉ ሰፈሮች የሚኖሩት ነጮች ናቸው።

“ምናልባት በዓለማችን ላይ ካሉት ከተሞች እኩልነት የሌለበት እና በተገለለ ሁኔታ የሚኖሩበት እንደ ኬፕታውን ዓይነት ቦታ አይገኝም” ይላሉ የከተማ ፖሊሲ ተመራማሪ የሆኑት ኒክ ቡደልንደር።

ቅኝ ገዥ ሰፋሪዎች ናቸው ከተማዋን ዲዛይን ያደረጉት፤ ይህንን ለመቀልበስ መንግሥት ሆን ብሎ ጣልቃ ሊገባ እንደሚገባም ነው ተመራማሪው የሚናገሩት።

“ከአፓርታይድ መገርሰስ በኋላ በኬፕታውን ማዕከላዊ ሰፈሮች አንድ የመንግሥት ተመጣጣኝ መኖሪያ ቤት አልተገነባም” ሲሉ ያስረዳሉ።

የመኖሪያ ቤቶች ክፍተትን ለመሙላት አንዳንድ ግዛቶችን የሚያስተዳድረው ዲሞክራቲክ አሊያንስ ለከተማ ሥራዎች እና አገልግሎቶች ቅርብ በሆኑ የመንግሥት መሬት ላይ “የተሻለ የመኖሪያ ቤት” ሞዴል እየገነባሁ ነው ይላል።

እየገነባሁ ነው የሚለው የኮንራዲ ፓርክ ፕሮጀክት የቀድሞ ሆስፒታል ነው።

የመጀመሪያው ምዕራፍ የአስተዳደሩ ድጎማዎች እንዲሁም በገበያ ዋጋ የሚሸጡ ቤቶችን ያቀረበ ሲሆን፣ ሁለተኛው ምዕራፍም በመገንባት ላይ ነው።

በሆስፒታሉ በአንድ ቢሮ ውስጥ የሚኖረው ቤቪል
የምስሉ መግለጫ,በሆስፒታሉ በአንድ ቢሮ ውስጥ የሚኖረው ቤቪል

የግዛቲቱ መሠረተ ልማት ሚኒስትር ቴርቱስ ሲመርስ 600 ሺህ የሚሆኑ ነዋሪዎች እገዛን እየጠበቁ እንደሆኑ ጠቅሰው 29 ተመሳሳይ የማኅበራዊ ቤቶች ፕሮጀክቶችን ለመሥራት የሰፋ ዕቅድ መያዙን ይናገራሉ።

ነገር ግን ያላቸው በጀት አነስተኛ መሆኑን አምነው ከግሉ ዘርፍ አጋርነት ያስፈልጋል ይላሉ።

ምንም እንኳን የመኖሪያ ቤት ፖሊሲ የአገሪቱ ትልቅ ጉዳይ ቢሆንም፣ የዲኤ ማኒፌስቶ ይህንን አላካተተም።

በሃብታሟ ኬፕታውን ዳርቻ በርካታ ጥቁሮች በድህነት እና በተጨናነቀ ሁኔታ የሚኖሩባት ካየሊትሻ ሰፈር አሁንም የከተማዋ እውነታ ነው።

በርካቶቹ በአፓርታይድ ሥርዓት ከነበረው የአያቶቻቸው እና የወላጆቻቸው ኑሮ በምንም መልኩ በተሻለ ሁኔታ ላይ አይደሉም።

ነዋሪዎች ገና ጎህ ሳይቀድ ነው ለሥራ ወደ ከተማ መጓዝ ያለባቸው። በየቀኑ 30 ኪሎሜትር መጓዝ ይኖርባቸዋል ሥራ ቦታቸው ለመድረስ።

ውድ የሆነ የባቡር ጉዞ፣ ሚኒባስ ታክሲ ወይም አስተማማኝ ያልሆኑ እና ብዙ ጊዜ ደኅንነታቸው ያልተጠበቁ ትራንስፖርቶችንም ለመጠቀም ይገደዳሉ።

ኖሊዬማ ተተኮሜ ለአምስት አስርት ዓመታት በዚህ ስፍራ ኖረዋል። ውሃ የሚያገኙት ከጋራ ቦኖ ሲሆን፣ መጸዳጃ ቤታቸውም የሕዝብ ነው።

ከሚያገኟት ደሞዛቸው ሩቡን በአትክልተኝነት ሥራቸው ወደተቀጠሩበት ስፍራ ለመጓጓዝ ያጠፉታል።

አንዳንድ ጎረቤቶቻቸው ከሚያገኙት ግማሽ ያህሉን የሚከፍሉት ለትራንስፖርት ነው።

ምርጫው ይህንን ይለውጣል ብለውም አይጠብቁም። ከዚህም በፊትም በነበሩ ምርጫዎች ቢመርጡም ምንም የመጣ ነገር ስለሌለ “እንደደከማቸው እና እንደማይመርጡም” የሚናገሩት ተሰላችተው ነው።

በምርጫ የተሰላቹት ኖሊዬማ ተተኮሜ
የምስሉ መግለጫ,በምርጫ የተሰላቹት ኖሊዬማ ተተኮሜ

ከነጻነት በኋላ የተከተለው የከፋ ሥራ እጦት፣ የምጣኔ ሀብት እኩልነት አለመስፈን፣ በከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ፣ ሙስና እና ሁከት ለሦስት አስርት ዓመታት አብላጫ ድምጽ ይዞ የቀጠለው ኤኤንሲ በዘንድሮው ምርጫ በበላይነቱ እንደማይቀጥል አመልካች ነው።

የአገሪቱ ሦስተኛው ትልቁ ፓርቲ ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ (ኢኤፍኤፍ) አሁንም በጥቂቶች የተያዘውን የአገሪቱን አንጡራ ሃብት እንደገና ለማከፋፈል ስር ነቀል ዕቅድ አቅርቧል።

በርካታ ወጣቶች ያሉበት ይህ ፓርቲ ለሦስት አስርት ዓመታት የኤኤንሲ ውድቀት የታየበትን ሁኔታ ለማስተካከል እየሞከረ እንደሆነ ያስረዳል።

ከእነዚህም በተጨማሪ በኬፕታውን ሌላ ራይዝ ምዛንሲ የተሰኘ ፓርቲም እውቅና እያገኘ ይገኛል።

“ደቡብ አፍሪካውያን በሥራ ቦታቸው አቅራቢያ ባሉ ቅርብ ሰፈሮች መኖር አለባቸው ብለን እናምናለን” ሲሉ የፓርቲው አገር አቀፍ መሪ ሶንግዞ ዚቢ የተናገሩ ሲሆን፣ ዲኤ እና ኤኤንሲ ፓርቲዎች ይህንን ባማከለ መልኩ የነዋሪዎችን ችግር መቅረፍ አልቻሉም ሲሉም ወቅሰዋቸዋል።

የኤኤንሲ ያለፉት ሰላሳ ዓመታት አገዛዝ ባጨለመው ሙስና፣ ወይም ሥልጣንን ያለአግባብ ለጥቅም በማዋል እየተወቀሰ ባለበት ወቅት ገና በሥልጣን ያልተፈተነው ራይዝ ምዛንሲ ብቅ ብሏል።

የቀድሞው የአፓርታይድ ታጋይ የነበረው ቤቪል አሁንም ለማኅበራዊ ትግል መታገሉን አላቆመም።

በትግሉ ውጤት ልቡ ቢያዝንም በወደፊቱ ተስፋ አይቆርጥም፤ አሁንም አማራጮች አሉ ይላል። ምርጫ ደግሞ አንደኛው በሕዝብ እጅ ውስጥ ያለ አማራጭ ነው ይላል።

ባለሥልጣናቱ የአፓርታይድ ውርስ የሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ ሊሰሩ እንደሚገባም ያስረዳል።

“ችግሮቹ የማይፈቱ ከሆነ ወደ ማኅበራዊ አለመረጋጋት እና ቀውስ ሊያስከትል ይችላል። ሰዎች ቤት አልባ ሆነው መጠለያ ባጡበት ወቅት ለምን አይነሱም?” ሲል ይጠይቃል።