
ከ 5 ሰአት በፊት
በናይጄሪያ ሰሜናዊ ግዛት ውስጥ ለ100 ሴት ልጆች የተደገሰ ሠርግ አንዳንዶቹ ሴቶች ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ ናቸው በሚል ተሠርዟል።
በናይጄሪያዋ ኒጀር ግዛት አንድ ትልቅ ሠርግ ተደግሶ ነበር። አንድ መቶ ጥንዶችን ለመዳር የተዘጋጀው ሠርግ የዓለምን ትኩረት ለመሳብም በቅቷል።
በሰሜናዊ ናይጄሪያ እንደዚህ ዓይነት የጅምላ ሠርጎች የተለመዱ ናቸው። የአሁኑን ለየት የሚያደርገው ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ ሴት ታዳጊዎች ሊሞሸሩ ነው የሚለው ክስ ነው።
የጅምላ ሠርጉ በኒጀር ግዛት ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ በሆኑት መሐመድ አብዱልማሊክ ሳሪን-ዳጂ ገንዘብ ድጋፍ የተደረገለት ነው ተብሏል።
በተለይም ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ ታዳጊዎች በሠርጉ መካተታቸው ውዝግብን አስነስቷል።
የሴቶች ጉዳይ ሚኒስትር ኡጁ ኬኔዲ-ኦሃንዬይ ጣልቃ በመግባት ሠርጉ ላይ ምርመራ እንደሚካሄድ ቃል በመግባት አፈ ጉባኤውን ፍርድ ቤት ገትረዋቸዋል። ሠርጉም ለጊዜው እንዲቋረጥ ተደርጓል።
በዚህ ሳምንት የሚኒስትሩ ተወካይ ማኅበረሰቡን ጎብኝተው ነበር። 100ዎቹም ታዳጊ ሴት ልጆች በባህላዊ ገዢው ቤተ መንግስሥት ቀርበው ነበር። ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ ግን አልተገኙም ነበር።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንዳንድ የማኅበረሰቡ አባላት ግን በመጀመሪያው ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱ ሴቶች ውስት ወደ 38 የሚጠጉ ዕድሜያቸው ለትዳር ያልደረሱ እንደሆኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሕዝባዊ ተቃውሞውን ተከትሎ ከቢቢሲ ፒጂን ጋር ቆይታ ያደረጉት ሳርኪን-ዳጂ በመጀመሪያ ዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱትን ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ ሴቶች ዕድሜያቸው በደረሱ ሴቶች ተለውጠዋል የሚለውን ቅሬታ ውድቅ አድርጓል።
“የትኛዋም ሙሽራ አልተለወጠችም። ይህንን እኔ አላደርገውም” ሲሉ ተናግረዋል።
ሠርጉ መቋረጡን የሚገልጸው ዜና ሲሰሙ መዓት የወረደባቸው ያህል እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
“ወንበዴዎች በነጻ ከሚወስዷት ልጄ ብታገባ ይሻላል” በማለት የአንዷ ሙሽራ እናት የሆኑት አስማው ሼሁ ተናግረዋል።
ከጉልቢን ቦካ ማኅበረሰብ የመጡት እናት ሴት ልጃቸው 22 ዓመቷ እንደሆነ እና ለጋብቻ ፈቃደኛ መሆኗንም አስረግጠው ተናግረዋል።
- ለናይጄሪያ ወላጅ አልባ ታዳጊዎች የታቀደው የጅምላ ሰርግ ቁጣ አስነሳ18 ግንቦት 2024
- ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የጠቀሱት “ሌላ የጦርነት አዙሪት” ማንን ያሰጋል?27 ግንቦት 2024
- በናይጄሪያ 10 ሰዎች ተገድለው ከ160 የማያንሱ ሰዎች ታግተው ተወሰዱ27 ግንቦት 2024
በሽፍቶች ምክንያት ከተከሰተው የፀጥታ ችግር እና ከተስፋፋው እገታ አንጻር ልጃቸውን ከመዳር ውጪ ሌላ አማራጭ የላቸውም።
ሽፍታዎች አግተዋት ወደማታውቀው ቦታ ከሚወስዷት በክብር አግብታ የት እንዳለች እና በምን ሁኔታ ላይ እንዳለች ማወቅን ይመርጣሉ።
ሌሎችንም ሴት ልጆቻቸውን በተመሳሳይ ምክንያት ነው ለመዳር የተገደዱት። ድህነትም ሌላው ምክንያት መሆኑን ልብ ይሏል።
“ልጄ መንታ አላት። ምንም ነገር ስላልነበረን መንትያ እህቷን ባለፈው ዓመት ዳርናት። 80 ሺህ የናይጄሪያ ናይራ (54.7 ዶላር) ተሰጥቶናል” ሲሉ ስለጋብቻው ተናግረዋል።
እንደ አስማው ያሉ እናቶች በአካባቢው በዝተዋል። ብዙዎቹ ባሎቻቸው በሽፍቶች የተገደሉባቸው እና ልጆቻቸው ታፍነው የተወሰዱ ናቸው። ብዙዎቹ በእገታ ላይ ይገኛሉ።
በሕይወት የተረፉት ቤተሰቦቻቸው ደግሞ ልጆቻቸውን የማስተማር አቅም የሌላቸውም። አንዳንዶቹም ለመኖር ሲሉ ቤታቸውን ይሸጣሉ ብለዋል።
በኒጀር ግዛት በተለይም ከዋና ከተማዋ ርቀው በሚገኙ ማኅበረሰቦች ዘንድ እገታ እና የሽፍቶች ጥቃት አዲስ አይደለም።
የማኅበረሰቡ ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት አሰቃቂ የሚባሉ ጥቃቶች እና እገታዎች በሳምንት ከሦስት እስከ አምስት ጊዜ ይፈጸማሉ።
ባለፉት ሁለት ወራት ግን ይህ ቁጥር ቀንሷል።

የደኅንነት ስጋት ያስከተለው ጣጣ
የኒጀር ግዛት ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አብዱልማሊክ ሳሪን-ዳጂ ለቢቢሲ ፒድጂን እንደተናገሩት ለ100ዎቹ ታዳጊ ሴት ልጆች የታቀደው የጅምላ ጋብቻ ከአንድ መንደር አስተዳዳሪ ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ ነው።
ባሏ በሽፍቶች ታግቶ ሁለት ሚሊዮን ናይራ እንድትከፍል ስለተጠየቀች ሚስትም አስተዳዳሪው ለአፈ-ጉባኤው ነግረው ነበር።
በስምንት ቀናት ውስጥ ገንዘቡን ለመሰብሰብ በማሰብ የባሏን ሞተር ሳይክልን ጨምሮ ቤተሰቡ ያለውን ሁሉ አሟጣ ሸጠች። አጋቾቹ ግን በዚህ አላበቃ ብለው ተጨማሪ አንድ ሚሊዮን ናይራ ጠየቁ።
ቀሪውን ክፍያ ለመፈጸም ግን የምትሸጠው ነገር አልነበራትም።
በስድስት ወራት ውስጥ ሁለት ሴት ልጆቿን ለመዳር በዝግጅት ላይ የነበረችው እናት አማቾቿን ጠርታ የተለመደውን ክፍያ ፈጽመው ልጆቹን በአንዴ እንደምትድርላቸው ነገረቻቸው።
ሁለቱ ወንድ ሙሽሮች ቀሪውን አንድ ሚሊዮን ናይራ ለመክፈል ቻሉ።
ግለሰቡ በአካባቢው የፀጥታ ሥራ ከመንግሥት ጋር ተብበሮ እንደሚሠራ ያወቁት አጋቾቹ ባሏን ገደሉት።
ወንዶቹ ሙሽሮች ደግሞ ጋብቻው በታቀደው መሠረት እንዲከናወን ወይም የከፈሉት ገንዘብ እንዲመለስላቸው ጠየቁ።
ሳርካን-ዳጂ እንደሚሉት ከሆነ ታሪኩ ስላሳዘናቸው ለጋብቻው ማስፈጸሚያ ሁለት ሚሊዮን ናይራ ለሴትዋ ሰጡ።
በተደረገላት እገዛ በጣም ደስ የተሰኘችው እናት ለመንደሩ አስተዳዳሪ እና ለአካባቢው ኢማም ያገኘችውን እርዳታ ነገረቻቸው።
አስተዳዳሪው እና ኢማሙ ደግሞ ተመሳሳይ ችግር ላለባቸው 270 ገደማ አባወራዎች ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ተማጽኖ አቀረቡ።
“ሴት ልጆቻቸውን ለመዳር እርዳታ የሚያስፈልጋቸው 270 አባወራዎች እንዳሉ ተነግሮኝ ነበር። እያንዳንዳቸው ከ400 ሺህ እስከ 450 ሺህ ናይራ ወጪ ይፈልጋሉ። እኔ መደገፍ የምችለው 100 ሰዎችን ብቻ ነው። ከራሴ 50 ሚሊዮን ናይራ ወጪ በማድረግ ደገፍኳቸው። ይህንን ሳደርግ ሙሽሮችንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን ሳላውቅ በበጎ ፈቃድ ነው” ብለዋል።
ምንም እንኳን በተፈጠሩት ውዝግቦች ማዘናቸውን ለቢቢሲ ቢናገሩም “ሁሉም ነገር በመፈታቱ ደግሞ ደስተኛ ነኝ” ብለዋል።
ሊዳሩ የነበሩትን ሴቶችን ዕድሜ ለማወቅ እና ጋብቻውን ለመፈጸም ፈቃደኛ ስለመሆናቸው ምርመራ ለማድረግ የሴቶች ጉዳይ ሚኒስትር አንድ ቡድን ወደ ኒጀር ግዛት ልኳል።

‘ትምህርት አንፈልግም የሙያ ድጋፍ ይደረግልን’
ቡድኑ ከመድረሱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የአካባቢው ባለሥልጣናት 100ዎቹን ሴቶች ከተለያዩ ማኅበረሰቦች እና መንደሮቻቸው አሰባሰቧቸው።
ይህንን ያደረጉት ለሚኒስትሩ ተወካዮች በይፋ ለማሳየት ነው።
ቡድኑ በኮንታጎራ መስተዳደር ወደሚገኘው የኤሚሩ ቤተ መንግሥት ሲደርስ ግን ከሕዝቡ ተቀባይነት አላገኘም።
በቤተ መንግሥቱ የነበረው ውጥረት የረገበው የሚኒስትሩ ተወካይ አዳጂ ኡስማን “እኛ ሠርጉን ለማቆም አልመጣንም። እኛ የመጣነው ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ ሴቶች መኖራቸውን እና ፈቃደኛ መሆናቸውን ለማየት ነው” ሲሉ ነው።
ከሴቶቹ መካከል ወደ ትምህርት ቤት መመለስ የሚፈልጉ ካሉ ነጻ የትምህርት ዕድል እንደሚያገኙ እና የሙያ ትምህርት ፍላጎት ያላቸውም እንደሚሰለጥኑ አክለው ገለጹ።
ኡስማን በሃውሳ ቋንቋ “ለታዳጊ ሴቶች ድጋፍ ለማድረግ የመለየት እና መረጃቸውን የመሰብሰብ ሥራ እናከናውናለን” ሲሉ ሕዝቡ አጨበጨበ።
ሴቶቹን በምርጫቸው የመለየት ሥራ ሲከናወን አንዳቸውም ወደ ትምህርት ቤት የመሄድ ፍላጎት አልነበራቸውም።
ሁሉም የሙያ ሥልጠና መውሰድን መርጠዋል። አንዳንዶቹ የልብስ ስፌት ፍላጎት ሲያሳዩ አብዛኛዎቹ ደግሞ በእርሻ መሰማራትን ምርጫቸው አድርገዋል።
ሴቶቹ ትዳር ሲመሠርቱ የተመቻቸ ሕይወት እንዲኖራቸው ለማድረግ የፌደራል መንግሥቱ በሴቶች ጉዳይ ሚኒስትር በኩል ድጋፍ እስኪያደርግላቸው ድረስ ጅምላ ጋብቻው መሰረዙን የሚኒስትሩ ተወካዮች ገልጸዋል።
የሚኒስትሩ ተወካዮች በትዳር ውስጥ በተመቻቸ ሁኔታ እንዲኖሩ ለማድረግ በፌዴራል መንግሥት በሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት የድጋፍ መርሃ ግብር እስኪያጠናቅቅ ድረስ የጅምላ ጋብቻ አይካሄድም ይላሉ።
ለቢቢሲ ፒጂን በደረሰው መረጃ መሠረት ግን ከሴቶች ጉዳይ ሚኒስትር ፍላጎት በተለየ መልኩ በተለያዩ አካባቢዎች ሠርጉ በጅምላም ባይሆን በተናጥል በግለሰብ ደረጃ እየተከናወነ ይገኛል።