
ከ 5 ሰአት በፊት
ጁልየስ ማሌማ የሚታወቀው ደንብ በመጣስ ነው።
በምክር ቤት የሚያደርገው አዝናኝ ንግግር በማኅበራዊ ሚዲያ ቶሎ ይሰራጫል። ከ11 ዓመታት በፊት የፈጠረው ፓርቲ ከደቡብ አፍሪካ ትልልቅ ፓርቲዎች አንዱ ነው። በአህጉሪቱም ዕውቅናን አትርፏል።
ማሌማ ጠንካራ ነው። ሥር ነቀል ለውጥን ያቀነቅናል። በዚህም ውክልና ያላገኙ ደቡብ አፍሪካውያንን ትኩረት አግኝቷል።
ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ (ኢኤፍኤፍ) ይባላል የሚመራው ፓርቲ። ጁልየስ ማሌማ 43 ዓመቱ ነው።
በእርግጥ ብዙ ተቺዎች አሉት። ሁለት ጊዜ የጥላቻ ንግግር በማድረግ ተከሷል። ተቺዎቹ ዕድሎችን ለመጠቀም የሚጠባበቅ ነው ሲሉ ይነቅፉታል።
ስለ ማሌማ የተከፋፈለ አስተያየት ቢኖርም ፓርቲው ለውጥ ያመጣባቸው ፖሊሲዎች አሉ።
በአውሮፓውያኑ 2012 ነበር ከገዢው ኤኤንሲ ፓርቲ ተባረረው። በፓርቲው ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን በማሳየት የሚመራው ፓርቲ እውነተኛ የኤኤንሲ ተረካቢ እንደሆነ ይናገራል።
‘ጁጁ’ በሚል ስም የሚጠራው ማሌማ የፓርቲው ቀዳሚ ትኩረት በደቡብ አፍሪካ የሰፈነውን እኩልነት ማጣት መቀልበስ ነው።
ሃብት ከጥቂት ነጮች እጅ ወደ አብዛኛው ጥቁር ሕዝብ እጅ እንዲገባ ይሻል።
በ2019 ምርጫ ፓርቲው ኢኤፍኤፍ 11 በመቶ ድምጽ አግኝቶ፣ በምክር ቤት 44 መቀመጫዎች አግኝቷል።
በዘንድሮው ምርጫም ተመሳሳይ ውጤት ሊመጣ እንደሚችል ይገመታል።
ኤኤንሲ ከ50 በመቶ በታች ድምጽ ሊያመጣና ከፍተኛ የምክር ቤት መቀመጫ ቁጥር ሊያጣ ይችላል ተብሏል። ይህም በ30 ዓመታት ውስጥ ዝቅተኛው ነው።
በምክር ቤት ያላቸው መቀመጫ አነስተኛ ቢሆንም በቀላሉ ዕይታ ውስጥ የሚገባው የማሌማ ፓርቲ ነው።
ለደቡብ አፍሪካ ሠራተኞች ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት ቀይ የሠራተኞች ልብስ ለብሰው ምክር ቤት ይገባሉ።
ምክር ቤት ውስጥ ድብድብ ተቀስቀሶ፣ ውይይት ረግጠው ወጥተውም ያውቃሉ።
- ከሠራተኞች ኅብረት መሪነት ወደ የናጠጠ ሃብታምነት የተሸጋገረው የፕሬዝዳንት ራማፎሳ ጉዞ28 ግንቦት 2024
- ስቲንሄዘን: ደቡብ አፍሪካን ‘ለማዳን’ ቃል የገቡት ግለሰብ26 ግንቦት 2024
- በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚገኙባት የደቡብ አፍሪካ ምርጫ ስምንት ቁልፍ ጉዳዮች23 ግንቦት 2024
ማሌማ በፖለቲካ ሕይወቱ ውዝግብ በማስነሳት ይታወቃሉ። ከሴቶች መብት ተሟጋቾች፣ ከነጭ አርሶ አደሮች እና ከራሱ ፓርቲ አመራሮች ጋርም ተጣልቶ ያውቃል።
በ2010 እና 2011 (እአአ) በጥላቻ ንግግር ክስ ጥፋተኛ ተብሏል። አንደኛው ክስ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማን በመድፈር የከሰሰች ሴትን በተመለከተ የሰጠውን አስተያየት ይመለከታል።
እስራኤል በጋዛ የምታካሂደውን ወረራ በመቃወም ሰልፍ ሲወጡ “ኢኤፍኤፍ ሥልጣን ሲይዝ ሐማስን አስታጥቆ ለሕዝቡ እንዲታገል ይረዳል” ማለቱ ውዝግብ አስነስቷል።
ሐማስን ምዕራባውያን አገራት እንደ አሸባሪ ቡድን ፈርጀውታል።
የመሬት ክፍፍልን በተመለከተ በ2016 ባደረገው ንግግር “አስፈላጊው ሁሉ ተደርጎ መሬቱ ይወሰዳል” ማለቱ ሌላ ውዝግብ ያስነሳ ጉዳይ ነው።
“ነጮች ይገደሉ እያልን አይደለም። ቢያንስ አሁን ላይ እሱን አላልንም። መሬት በሰላማዊ መንገድ እንወስዳለን። ለዚህ ደግሞ ይቅርታ አንጠይቅም” ብሏል።
ለድሃ ጥቁሮች ያለው ተቆርቋሪነት ደጋፊዎቹን ያስደስታል።
በተለይ በወጣቶች ዘንድ ዝነኛ ነው። ወደ ጋና፣ ላይቤሪያ እና ኬንያ ሲሄዱም አወዛጋቢነቱ ተከትሎት ይጓዛል።

ማሌማን በዚህ ዓመት ወደ ኬንያ የጋበዘው የፓን አፍሪካን ኢንስቲትዩት ኃላፊ ፕሮፌሰር ሉሙምባ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ “ማሌማ የሚወክለው ስለ ፓን አፍሪካ ጉዳዮች ማውራት የጀመሩትን ወጣት አፍሪካውያንን ነው” ብለዋል።
የፖለቲካ ተንታኙ ሪቻርድ ካላንድ እንደሚሉት፣ ማሌማ በምርጫ ድምጽ የሚያገኘው “ከጥቂት ታማኝ ደጋፊዎቹ” ብቻ ነው።
“ሥርዓትን የሚጻረር፣ ወታደራዊ፣ ሁከት የሚፈጥር በሚል ነው ማሌማ የሚታወቀው። ይሄ ለአብዛኛው ሕዝብ ተቀባይነት ያለው ነው ብዬ አላስብም” ይላሉ ተንታኙ።
ጁልየስ ማሌማ የተወለደው እአአ በ1981 ነው።
እናቱ ፍሎራ የቤት ሠራተኛ ነበሩ። በሊምፖፖ ግዛት ውስጥ ሼሼጎ በተባለ አካባቢ ነው ያደገው።
የሁለተኛ ደረጃ ውጤቱ እምብዛም አመርቂ የሚባል ባይሆንም፣ ፓርቲውን እየመራ ሁለት ዲግሪ አግኝቷል።
ማሌማ የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለ ነበር ወታደራዊውን የኤኤንሲ ክንፍ የተቀላቀለው። በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥም የአካባቢያው ወጣቶች ክንፍ መሪ ሆነ።
በ2008 (እአአ) የወጣቶች ሊግ መሪ ከሆነ በኋላ ነው ስሙ በደቡብ አፍሪካ የፖለቲካ መድረክ ላይ መነሳት የመጀመረው።
ጃኮብ ዙማ እንዲመረጡ ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርጓል።
በ2009 ዙማ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ ግን ግንኙነታቸው ሻከረ። ዙማ ድምጽ የሰጣቸውን ድሃ ማኅበረሰብ ረስተዋል ሲል ማሌማ ተቃወመ።
በአውሮፓውያኑ 2013 የኢኮኖሚ ነጻነት ተፋላሚዎች (ኢኤፍኤፍ) የተባለውን የራሱን ፓርቲ መሠረተ።

በ2024 የፓርቲ ማኒፌስቷቸው ላይ “ኤኤንሲ አፓርታይድ የፈጠረውን ኢ-ፍትሐዊነት አባብሷል” በማለት በገዢው ፓርቲ ላይ ዘመቻ ከፍቷል።
ሥራ አጥ ለሆኑ ሚሊዮኖች ሥራ ለመስጠት ቃል ገብቷል። ፓርቲው ካሸነፈ በአገሪቱ በተደጋጋሚ የሚያጋጥመውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እንደሚቀርፍም ተናግሯል።
የማዕድን እና የባንክ ዘርፎችን በመንግሥት ይዞታ ሥር እንደሚደረጉ ይፋ አድርጓል።
የሚያቀነቅነውን የግራ ዘመም ርዕዮተ ዓለም ከድቷል በሚል ከዚህ ቀደም ተተችቶ ያውቃል።
በ2013 የደቡብ አፍሪካ የአገር ውስጥ ገቢ እንዳለው፣ ፓርቲው አንድ ሚሊዮን ዶላር የግብር እዳ አለበት።
ይህን እዳ ለመክፈል በጆሀንስበርግ ያለ ተገንብቶ ያላለቀ ቅንጡ ቪላን ለመሸጥ ተገዷል።
ከአንድ መንግሥት ባለሥልጣን ጋር በተያያዘ የማጭበርበር እና ሙስና ክሶችም አሉበት። በ2015 ሂደቱ ተጓቷል በሚል ፍርድ ቤት ክሱን አንስቶታል።
ማሌማ ክሶቹ ፓለቲካዊ ናቸው በማለት ሲያስተባብል ቆይቷል።
በ2018 ቪቢኤስ ከተባለ ባንክ 108 ሚሊዮን ዶላር በመዝረፍ ከተከሰሱ ሰዎች መካከልም ማሌማ ይገኝበታል።
በዚህ ወንጀል ዙሪያ የተካሄደው የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ “በቂ ማስረጃ የለም” በሚል ያለ መደምደሚያ ተቋርጧል።
በደቡብ አፍሪካ የሜል ኤንድ ጋርዲያን ጋዜጠኛ ፓዲ ሀርፐር “ማሌማ ፓርቲውን በጥንካሬ እየመራ ምርጫውን ተቀላቅሏል። መሪነቱ ግን እንደቀደመው ጊዜ ጠንካራ አይደለም” ብሏል።
ከምክትላቸው ፍሎይድ ሻቪምፑ ጋር ያለው ግጭት እና በመራጮች ሊያገኙ የሚችሉትን አነስተኛ ድምጽ እንደ ምሳሌ ይጠቅሳል።
ኢኤፍኤፍ ፉክክር የሚጠብቀው ከኤምኬ ፓርቲ ነው። የፓርቲው መሪ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጄኮብ ዙማ ናቸው። በዋናነት በዙማ ትውልድ ከተማ የኢኤፍኤፍ ደጋፊዎችን እንደወሰዱ ተዘግቧል።
ሁሌም ላለመሸነፍ የሚታገሉት ማሌማ በምርጫው የሚኖራቸው ውጤት በቀጣይ የሚታይ ይሆናል።
ደቡብ አፍሪካን ከኤኤንሲ አገዛዝ ለማውጣት ባደረጉት ሥር ነቀል እንቅስቃሴ ማሌማ ይታወቃል።
ታማኝ ደጋፊዎችን ያገኘውም በዚህ አቋሙ ነው።
የፓርቲውን ማኒፌስቶ ከወራት በፊት ሲያስተዋውቅ በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቹ ተገኝተዋል።
“የአብዮታችንን ጠላቶች የምናሸንፍበት መሣሪያ ይህ ነው” ሲሉ ነበር ደጋፊዎቹ ማኒፌስቶውን የገለጹት።