
ከ 6 ሰአት በፊት
በአሜሪካ ታሪክ የቀድሞም ይሁን ሥልጣን ያለ የአአገሪቱ ፕሬዝዳንት በወንጀል ተከሶ ጥፋተኛ ሲባል ዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያው ናቸው።
በማንሀተን ፍርድ ቤት በ34 ክሶች ጥፋተኛ ቢባሉም ሊታሰሩ እንደማይችሉ እየተነገረ ነው።
ትራምፕ ውሳኔውን ይግባኝ ማለታቸው አይቀርም። ይግባኙ የሚታይበት ጊዜም ከመጪው ምርጫ በኋላም ሊሆን ይችላል።
ጥፋተኛ በመባላቸው ቅጣት፣ ዕግድ ወይም ክትትትል ሊጠብቃቸው ይችላል።
ትራምፕ ቢታሰሩ እንኳን የፕሬዝዳንት ዕጩ ሆነው ሊቀጥሉ ይችላሉ። ከእስር ቤት ሆነው አሜሪካን ሊመሩም ይችላሉ።
ጥፋተኛ የተባለ ሰው እንዴት በምርጫ ይወዳደራል?
ለፕሬዝዳንት ማን ዕጩ እንደሚሆን የሚወስነው የአሜሪካ ሕግ እአአ ከ1789 ወዲህ አልተለወጠም። ያኔ ጆርጅ ዋሽንግተን ነበሩ ሥልጣን የያዙት።
በዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ኦፍ ለንደን፣ የአሜሪካ ታሪክ ፕሮፌሰር ኢዋን ሞርጋን እንደሚሉት፣ ዕጩዎች በአሜሪካ ግዛት መወለድ እንዳለባቸው ሕጉ ይደነግጋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ላይ የትውልድ ቦታ ጥያቄ የተነሳውም ለዚህ ነበር።
ዕጩዎች ከ35 ዓመት በላይ እንዲሆኑም ሕጉ ያዛል።
- ጥፋተኛ የተባሉት ትራምፕ፤ ዘብጥያ ሊወርዱ ይችላሉ? በመጪው ምርጫስ መሳተፍ ይችላሉ?31 ግንቦት 2024
- ዶናልድ ትራምፕ በታሪካዊው የክስ ሂደት በቀረቡባቸው ክሶች በጠቅላላ ጥፋተኛ ተባሉ31 ግንቦት 2024
- ጆ ባይደን ከዶናልድ ትራምፕ፡ ለፕሬዝዳንትነት አሸናፊውን የሚለዩ አራት ወሳኝ ነጥቦች16 ሚያዚያ 2024
በሕጉ መሠረት ዕጩዎች አሜሪካ ውስጥ ለ14 ዓመታት መኖር አለባቸው።
ሕጉ የማይቀበለው “አሜሪካ ላይ አመጽ ያነሳሱ” ሰዎችን እንደሆነ ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ።
ሆኖም ግን ይህ አንቀጽ ትራምፕ ላይ እንዳይተገበር ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያስተላለፈው ውሳኔ እንደሚያግድ ያስረዳሉ።
በወንጀል ጥፋተኛ የተባሉ ሰዎች ለፕሬዝዳንትነት መወዳደር አይችሉም የሚል ሕግ የለም።
“አሜሪካ የተፈጠረችው በአብዮት ነው። የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነበረች። ሕጉ ዘውዳዊውን ሥርዓት በመቃወም እስር ቤት የገቡ ሰዎች ለፕሬዝዳንትነት መወዳደር እንዳይችሉ ያደርግ ነበር” ይላሉ የታሪክ ምሁሩ።
አሜሪካ ስትመሠረት የ1787 ሕገ መንግሥትን ያወጡት የአሜሪካ መሥራቾች በእንግሊዝ ሊታሰሩ ተቃርበው የነበረ ቢሆንም አንዳቸውም ለእስር አልተዳረጉም።
“አብዮቱ ባይሳካ ኖሮ ዘውዳዊውን ሥርዓት በመቃወም ጥፋተኛ ይባሉ ነበር። ወንጀለኛም ይሆኑ ነበር” ሲሉ ያስረዳሉ።
ይሄንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው ፕሬዝዳንት ለመሆን የሚወዳደሩ ሰዎች በወንጀል ጥፋተኛ መሆን የለባቸውም የሚል አንቀጽ ያልተካተተው።
ከእስር ቤት ሆነው ፕሬዝዳንት ለመሆን ለሚሞክሩም የሚከለክል አንቀጽ የለም።
የዩጂን ዴብስ ጉዳይ
በእስር ላይ ሳለ ለመሪነት በመወዳደር የሚታወቀው ዩጂን ዴብስ ነው። ይህ የሆነው በ1920 ነበር።
ዩጂን መጀመሪያ የታሰረው በ1894 እንደነበር ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ።
የባቡር ድርጅት ላይ ክስ በማቅረብ ሲከራከር ነበር የታሰረው። ለስድስት ወራት ከታሰረ በኋላ ስለ ፖለቲካ ያለው አመለካከት ተለውጧል።
“በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ የአሜሪካ ሶሻሊስት ፓርቲ ዋና አባል ነበር። በ1904፣ 1908፣ 1912 እና 1920 ለፕሬዝዳንትነት ተወዳድሯል” ይላሉ።
በ1912 ዴሞክራቱ ዉድሮው ዊልሰን እና ሪፐብሊካኑ ዊልያም ሀዋርድ ታፍት እንዲሁም የቀድሞው ሪፐብሊካን ፕሬዝዳንት ቴዎዶር ሩዝቬልት ሲወዳደሩ ዩጂን ጥሩ ተቀባይነት አግኝቷል።
“ወደ ሚሊዮን የሚጠጋ ድምጽ አግኝቷል። ከአጠቃላይ ድምጽ 6 በመቶው ነበር። በአሜሪካ በሶሻሊስት ፓርቲ ታሪክ ከፍተኛው ድምጽ ነው” ሲሉም ፕሮፈሰር ኢዋን ያስረዳሉ።

በዚህም ዩጂን ዴብስ በ1912 ካገኘው ድምጽ የተሻለ አግኝቷል። በ1920 ያገኘው 914,191 ድምጽ ሲሆን፣ በ1912 ደግሞ 901,551 ድምጽ አግኝቷል። 3 በመቶ ተጨማሪ ድምጽ ያገኘው ሴቶች ድምጽ እንዲሰጡ የተፈቀደበት ጊዜ ስለነበረ ነው።
ከሦስት ዓመት እስራት በኋላ ነበር የተለቀቀው። የጤና ቀውስ ገጥሞት በ1926 ሞቷል።
ከሞቱ በኋላ ሶሻሊስት ፓርቲ በአሜሪካ የጎላ ሚና አልኖረውም።
የሊንደን ላሩሽ ጉዳይ
ከእስር ቤት ሆኖ ሌላው ለፕሬዝዳንትነት የተወዳደረው ሊንደን ላሩሽ ነው።
“እንደ ዴሞክራት፣ እንደ ሦስተኛ ወገን ፓርቲም ቅስቀሳ አድርጓል። ከ1976 እስከ 2008 ድረስ ተወዳድሯል” ሲሉ የታሪክ ምሁሩ ይገልጻሉ።
በ1940 በግራ ዘመም ፖለቲካ ነበር የሚታወቀው። በ1970ዎቹ ወደ አክራሪ ቀኝ ዘመም ፖለቲካ ገባ።
“በዴሞክራት እና በሪፐብሊካን ማንነቱ መካከል ያለው ልዩነት ለሴራ ትንታኔ አጋልጦታል። ንግሥት ኤልሳቤጥ ልትገድለው እንደምትፈልግ ያምን ነበር” ይላሉ።
ወጣ ያሉ አመለካከቶች ያሉት ሰው ሲሆን፣ ግብር እንዲቀነስ እና መንግሥት ዜጎቹን እንዳይሰልል የሚያደርጉ ሐሳቦችን ያቀርብም ነበር።

በኤልኖይ ግዛት በ1986 በእሱ ድጋፍ ያገኙ ዕጩዎች የምርጫ ውድድር አሸንፈዋል። አንደኛዋ ጃኒስ ኤ ሀርት ስትሆን፣ ታንክ አደባባይ ለማውጣት ንቅናቄ ታደርግ ነበር።
ወደ 200 ሚሊዮን ዶላር ለምርጫ ውድድር ማሰባሰብ እንደቻለ የታሪክ ምሁሩ ይጠቅሳሉ።
“እምብዛም ስኬታማ ባይሆኑም ለአካባቢ እና ለኮንግረስ ምርጫ ዕጩዎችን ይደግፍ ነበር” ይላሉ።
በ1989 በሰነድ ማጭበርበር ክስ የ15 ዓመት እስራት ተፈርዶበታል።
በ1992 ግን በምርጫ ለመወዳደር ወሰነ። 27,000 ድምጽ (0.1% በመቶ) አግኝቷል።
በ1994 ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ በ1996፣ በ2000፣ በ2004 እና በ2008 ተወዳድሯል።
“ሆኖም ግን በታሪክ ትንሽ ቦታ ካለው ሰውነት አልዘለለም” ሲሉ ፕሮፌሰሩ ይገልጹታል።
በ2019 ሕይወቱ አልፏል።

የጆሴፍ ስሚዝ ጉዳይ
ጆሴፍ ስሚዝ በ1830 የ‘ሞርሞኒዝም’ እምነትን የፈጠረው ሰው ነው።
የእምነቱ መነሻ ክርስቶስ ቢሆንም ከካቶሊክ፣ ከፕሮቴስታን እና ከኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የተለየ ምልከታ ነበረው።
ስሚዝ ከአንድ በላይ ሚስት ማግባትን እንዳስተዋወቀ የሚገልጹት ፕሮፌሰር ኢዋን እንደሚያስረዱት፣ ሐሳቡ ለአሜሪካውያን በቀላሉ ለመቀበል የሚከብድ ነበር።
“አሜሪካዊ አመለካከቶችን የሚጻረር ተደርጎ ነው የተወሰደው። ከፍተኛ ወንጀል ተደርጎም ታይቷል። ጆሴፍ ወደ 20 ሚስቶች እንደነበሩት ይነገራል” ይላሉ።
የተወለደው ማሳቹሴትስ ቢሆንም በኤልኖይ ነበር እንቅስቃሴውን የሚያደርገው።
በ1840 ሞርመኖች የናውቮ የተባለ ራሳቸውን ከተማ ሠርተዋል። የአምልኮም ስፍራ ነበረው።
ጆሴፍ ስሚዝ ከንቲባ ሆኖ ከተመረጠ በኋላ የሞርመን ሚሊሻ አቋቁሟል።
“በሞርመኖች መካከል የሚከፋፍል አካሄድ ነበረው። የአንዳንድ ሞርመኖችን ሚስት መቀማቱ አንደኛው ጉዳይ ነው” ይላሉ የታሪክ ምሁሩ።
ከእሱ ተጻራሪ የሆኑ ጋዜጦችን እንዲያጠፉ የሞርመን ሚሊሻዎችን ይልክ ነበር። ክስ የተመሠረተበትም በዚህ ነው።
በ1844 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሲካሄድ የሪፎርም ፓርቲ ዕጩ ሆኖ ቀረበ።
የሞርመን ፓርቲው ድምጽ ለማግኘት ተስፋ አድርጎ ነበር። ሁሉም ሰው ፈጣሪ ነው የሚለው አስተሳሰብ ሰርጾ እንዲገባ ፍላጎት ነበራቸው።
ሆኖም ግን በባርነት ውስጥ ያሉ ሰዎችን በአጠቃላይ ነጻ ለማውጣት ማሰባቸው ተቀባይነት አላገኘም።
“ያኔ ባርነት መቃወም ቀላል አልነበረም። ባርነት እንዲቆም የሚሹ ሕይወታቸውን ያጡ ነበር” ይላሉ ፕሮፌሰር ኢዋን።
ጆሴፍ እስር ቤት ሳለ በተከፈተበት ተኩስ ነው የሞተው።
አስክሬኑ ላይ ተጨማሪ ጥይት እንዲተኮስ ታዞም ነበር።
ሪፎርም ፓርቲ በ1844 ምርጫ ሌላ ዕጩ አላቀረበም።
በአሜሪካ ታሪክ በወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ ለምርጫ የሚወዳደረው አራተኛ ሰው ጆሴፍ ማልዶናዶ-ፓሴጅ ነው።
‘ጆ ኤግዞቲክ’ በተባለው የኔትፍሊክስ ዘጋቢ ፊልም ይታወቃል። በቀጣዩ የአሜሪካ ምርጫ የዴሞክራት ዕጩ ሆኖ እንደሚወዳደር አስታውቋል።
እንስሳትን በማሰቃየት እና ተቀናቃኙ የሆነን መካነ እንስሳት ባለቤትን ለመግደል በማሴር የ20 ዓመት እስራት ተፈርዶበት ማረሚያ ቤት ይገኛል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በወንጀል ጥፋተኛ ተብለው ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩት ሌላኛው ሰው ይሆናሉ።
የተከፋፈለው የአሜሪካ ሕዝብ ምናልባትም በወንጀል ጥፋተኛ በሆነ ሰው በምርጫ ውድድር ይወከል ይሆናል።