
ከ 6 ሰአት በፊት
ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያንን ከሰው በታች ያወረደውን ዘረኛውን የአፓርታይድ ሥርዓት በመገርሰስ በኩል ትግል ያደረገው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) አገሪቷን ከሦስት አስርት ዓመታት በበላይነት ሲመራ ቆይቷል።
የበርካቶች ሕይወት ተገብሮ በአውሮፓውያኑ 1994 ደቡብ አፍሪካ ነጻነቷን ስትጎናጸፍ የፓርቲው መሪ ኔልሰን ማንዴላ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆኑ።
አስካሁን ለሰላሳ ዓመታት ያህል ፓርቲው አገሪቷን ቢመራም የሰሞኑ ምርጫ ያንን የፖለቲካ የበላይነቱ መቋጨቱን አሳይቷል።
ምርጫው ለፓርቲው የጥምር መንግሥትን አማራጭ እንዲያይ፣ እንዲሁም በፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ መጪ ሁኔታ ላይ ጥያቄዎችን ያስነሳ ሆኗል።
ደቡብ አፍሪካ እንዴት እዚህ ደረሰች? መጻኢው ጊዜስ ምን ይሆናል?https://flo.uri.sh/visualisation/18172379/embed?auto=1
ከኤኤንሲ ውድቀት ጀርባ
የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ለዘመናት በደቡብ አፍሪካውያን ዘንድ የነጻነት ተምሳሌት ነበር።
ደቡብ አፍሪካውያን በግፍ የተነጠቁትን የሰውነት ክብር ያስመለሰ በመሆኑም ንቅናቄው በብዙዎች ልብ ውስጥ ከፍ ያለ ስፍራ ነበረው።
ነገር ግን ከሦስት አስርት ዓመታት የሥልጣን ቆይታ በኋላ ይሄ ሁሉ ተቀይሯል።
ፓርቲው በአገሪቱ ውስጥ የተንሰራፋው ሙስና እና የመጥፎ አስተዳደር ተምሳሌት ሆኗል።
በዚህም የተነሳ ግንቦት 21/ 2016 ዓ.ም. በነበረው ምርጫ ወጣቶች በምርጫ ካርዳቸው ፓርቲውን ቀጥተውታል።
ወጣቶቹ ከዚህ በፊት ከነበሩ ምርጫዎች በተለየ መልኩ በከፍተኛ ቁጥር ወጥተው ነው ድምጽ የሰጡት።
“ሙስና ሰልችቷቸዋል፣ በሥራ አጥነት ክፉኛ ተጎድተዋል። ስለዚህ የኤኤንሲ ተጻራሪ ሆኑ” ሲሉ ዲሞክራሲ ወርክስ ፋውንዴሽን የተሰኘ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ሊቀ መንበር ዊልያም ጉመዴ ያስረዳሉ።
በርካታ ወጣቶች ኤኤንሲን ተቃውመው መነሳታቸው የትውልድ መከፋፈልንም ያሳየ ነው።
ትግሉን የሚያውቁት የወጣቶቹ ወላጆች ከአፓርታይድ ሰንሰለት ነጻ ያወጣቸው የነጻነት ንቅናቄ በመሆኑ አሁንም ለኤኤንሲ ታማኝ ናቸው። ሆኖም የኤኤንሲ ድጋፍ በዕድሜ በገፉ መራጮችም ሆነ በገጠሩ አካባቢ ጭምር ቀንሷል።
“ኤኤንሲ በትልልቅ ከተሞች ድጋፉን ያጣው ከረጅም ጊዜ በፊት ነው። አሁን ደግሞ በገጠሮችም ቢሆን ድጋፉን እያጣ ነው” ሲሉ ፕሮፌሰር ጉመዴ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ኤኤንሲ በአውሮፓውያኑ 2004 በተደረገው ምርጫ 70 በመቶ የመራጮችን ድምጽ በማግኘት ከፍተኛ ድል ያስመዝግቧል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ባሉ ምርጫዎች የ3 በመቶ ወይም 4 በመቶ ድጋፍ እያጣ መጥቷል።
በዚህ ምርጫ ደግሞ ፓርቲው በአስርት ዓመታት አይቶት የማያውቀው ውድቀት አጋጥሞታል።
- ከሠራተኞች ኅብረት መሪነት ወደ የናጠጠ ሃብታምነት የተሸጋገረው የፕሬዝዳንት ራማፎሳ ጉዞ28 ግንቦት 2024
- በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚገኙባት የደቡብ አፍሪካ ምርጫ ስምንት ቁልፍ ጉዳዮች23 ግንቦት 2024
- ከ30 ዓመታት ነጻነት በኋላም የቀጠለው የደቡብ አፍሪካ የኢኮኖሚ አፓርታይድ29 ግንቦት 2024

የዙማ መመለስ
የ82 ዓመቱ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ወደ ምርጫው ተመልሰዋል።
ሲመለሱ ደግሞ ዝም ብለው ለመሳተፍ አይደለም የተመለሱት – በቀል ቋጥረው ነው።
ኤኤንሲ በአውሮፓውያኑ 2018 በሙስና ቅሌት ክስ ከሥልጣን ባረጨው ነበር። እሳቸው ግን ይህንን አስተባብለዋል።
ከመሪነት ስፍራቸውም ተነስተው በሲሪል ራማፎሳ ተተኩ።
ከሥልጣን ከተነሱ ከሦስት ዓመት ገደማ በኋላም በዘጠኝ ዓመታት የፕሬዚዳንት ዘመናቸው የተፈጸሙ የሙስና ወንጀሎችን የሚመለከት አጣሪ ፊት እንዲቀርቡ ፍርድ ቤት አዘዘ።
ፕሬዚዳንቱ ይህንን ትዕዛዝ በመጣሳቸው የ15 ወራት እስር ተፈረደባቸው። ሆኖም ዙማ ለሦስት ወራት በእስር ከቆዩ በኋላ፤ እርሳቸውንም ሆነ የተቆጡ ደጋፊዎቻቸውን የበለጠ ላለማስቆጣት ፕሬዚዳንት ራማፎሳ እንዲለቀቁ ወሰኑ።
ነገር ግን አሁን የራማፎሳን ውሳኔ የሚያጸጽት ነገር ሳይከሰት አልቀረም።
ዙማ ምኾንቶ ዊስዝዌ (ኤምኬ) በሚል ፓርቲ ወደ ፖለቲካው ግንባር ተመልሰዋል።
እስካሁን የወጡ የምርጫ ውጤቶች እንደሚያመለክቱ ኤኤንሲ ዋነኛው የድጋፍ መሠረቱ ነው በሚባልለት የኩዋዙሉ ናታል ግዛት በዙማ ፓርቲ ድምጽ ተነጥቋል።
በደቡብ አፍሪካ ትልቁ ሁለተኛው ትልቁ ክዋዙሉ ናታል ግዛት የዙማ ኤምኬ ፓርቲ 45 በመቶ ሲያሸንፍ፣ በመቀጠል ኢንካታ ፍሪደም ፓርቲ 18 በመቶ እንዲሁም ኤኤንሲ 17 በመቶ ድምጽ በማግኘት ሦስተኛ ሆኗል።
ይህም ዙማ የግዛቲቱ አድራጊ ፈጣሪ ያደርጋቸዋል የተባለ ሲሆን፣ በዚህም ዋነኛ ዓላማቸው የሆነውን የራማፎሳን ውድቀት የሚያሴሩበትን መሠረት እንደሚፈጥርላቸው እየተነገረ ነው።
ምንም እንኳን በፍርድ ቤት ጥፋተኛ በመባላቸው በአገሪቱ ምክር ቤት መግባት ባይችሉም፤ ሆኖም ከመጋረጃው በስተጀርባ ፖለቲካውን ሊያሽከረክሩት ይችላሉ ተብሏል።
የዙማ ፓርቲ ኤምኬ በዚህ መንገድ ድጋፍ ማግኘቱ ያልተለመደ ነው። ፓርቲው የተመዘገበው ከወራት በፊት መስከረም ላይ ሲሆን፣ ዙማ በራማፎሳ ለሚመራው ኤኤንሲ ድምጽ እንደማይሰጡ በመግለጽ ፓርቲውንም በታኅሣሥ ወር ነበር የተቀላቀሉት።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአፓርታይድ ሥርዓት ካከተመ በኋላ አዲስ ፓርቲ አድርጎት በማያውቀው መንገድ የደቡብ አፍሪካን ፖለቲካ አናግቷል።
የደቡብ አፍሪካው ሜይል እና ጋርዲያን ጋዜጣ የክዋዙሉ ናታል ዘጋቢ ፓዲ ሃርፐር እንደሚለው ኤምኬ የኤኤንሲን ድጋፍ ብቻ ሳይሆን፣ የአገሪቱ ሦስተኛ ትልቅ ፓርቲ የሆነውን ለስር ነቀል ለውጥ የሚታገለውን የጁሊየስ ማሌምን ኢኤኤፍ ፓርቲ ድጋፍን መሸርሸሩ ነው።
እስካሁን በተገኘው የምርጫ ውጤት ኤምኬ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተምጧል።

የጥምር ፓርቲዎች ፖለቲካ ሊወለድ ይሆን?
ተሰሚነት ያለው የደቡብ አፍሪካ የሳይንስ እና የኢንዱስትሪ ምርምር ምክር ቤት (ሲኤስአይአር) እና የኒውስ 24 ድረ ገጽ ኤንኤንሲ በዚህ ምርጫ ሊያገኘው የሚችለው ድምጽ 42 በመቶ አካባቢ ሊሆን እንደሚችል ተንብየው ነበር።
ሆኖም 99 በመቶ የድምጽ ቆጠራ በተጠናቀቀበት በአሁኑ ወቅት ኤኤንሲ ያገኘው ድምጽ 40 በመቶ ብቻ ነው።
ይህንንም ተከትሎ ውጤቱ ለኤኤንሲም ሆነ ለፕሬዚዳንት ራማፎሳ አስከፊ እንደሆነ እየተነገረ ነው። ራማፎሳን ፓርቲያቸው ሥልጣን እንዲለቁ ግፊት ሊያደርግባቸው ይችላል።
ምክትላቸው ፖል ማሻቲል ተተኪ ሊሆኑ እንደሚችሉም እየተነገረ ነው። ራማፎሳ ለፓርቲው ያደረጉት የምርጫ ቅስቀሳ ደካማ ከመሆኑ የተነሳ ፓርቲው ተስፋ ቆርጦ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪን እንዲሁም ሌሎች ጡረታ የወጡ የፓርቲውን አመራሮች ከዚህ እንዲያገግም በማለት ዘመቻውን እንዲቀላቀሉ አድርጓል።
በአብዛኛው የፓርቲው ደጋፊዎች ዘንድ ፕሬዚዳንቱ ደካማ እና ውሳኔ መስጠት የማይችሉ ሰው ተደርገው ነው የሚታዩት። እሳቸውም ትኩረታቸውን በአገሪቱ መግባባት እንዲፈጠር እየሠራሁ ነበር ሲሉ ራሳቸውን ይከላከላሉ።
በምርጫ ዘመቻቸውም ላይ “አምባገነን የሆነ፣ ጀብደኛ፣ ግዴለሽ ፕሬዚዳንት ለሚፈልጉ ሁሉ እኔ ይህንን አይደለሁም” ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ራማፎሳ በሥልጣን የመቆየት ዕድላቸው ከፍተኛ ይሆን የነበረው ኤኤንሲ ከ45 እስከ 50 በመቶ የሚሆነውን ድምጽ ማግኘት ቢችል ነበር።
በርካታ የኤኤንሲ አባላት በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ራሳቸውን ያገለሉ ሲሆን፣ ፓርቲው በክዋዙሉ ናታል ከፍተኛ ድጋፍ ካለው ኢንካታ ፍሪደም ፓርቲ እና በሙስሊሞች ዘንድ ድጋፍ ያለው አል ጃማህ አህ ካሉ ትናንሽ ፓርቲዎች ጋር ጥምረት ቢፈጥር በሥልጣን መቆየቱን እንደሚያስቀጥል ተናግረዋል።
ነገር ግን ኤኤንሲ ከ45 በመቶ በታች ድምጽ ካገኘ ጥምረቱን ከትልቅ ፓርቲ ጋር ለመመሥረት ሊገደድ ይችላል።
ይህም ማለት የዙማ ኤምኬ፣ የጁሊየስ ማሌማ ኢኤፍኤፍ ወይም ዋናው ተቃዋሚ ዲሞክራቲክ አሊያንስ ሊሆኑ ይችላሉ።
የቀኝ ፖለቲካ የሚያራምደው ዲሞክራቲክ አሊያንስ በከፍተኛ ሁኔታ የሕዝብን የልማት ተቋማት ወደ ግል የማዛወር (ፕራይቬታይዜሽን) በመደገፍ እንዲሁም ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወገድም የሚጠቅሱ ፖሊሲዎች አሉት።
ሆኖም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚኖረው ጥምረት የሚወሰነው በተለያዩ ግዛቶች በተለይም ጆሃንስበርግ እና ፕሪቶሪያን የያዘው ሃውቴንግ እና ክዋዙሉ ናታል የሚገኘው ድምጽ ነው።
አንደኛው አማራጭ በኤምኬ እና በኤኤንሲ መካከል በክዋዙሉ ናታል ግዛት እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ጥምረትን መመሥረት ነው። ነገር ግን በሁለቱ ወገኖች መካከል ካለው መቃቃር የተነሳ ይህ የማይመስል ሊሆን ይችላል።
ሌላኛው ደግሞ ኤኤንሲ ዲሞክራቲክ አሊያንስ እና ኢንካታ ፍሪደም ፓርቲ (አይኤፍፒ) የተካተቱበት ሦስት ፓርቲዎች በክዋዙሉ ናታል ግዛት እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያስተዳድሩበትን ስምምነት ሊያቀርብ ይችላል።
“ዲሞክራቲክ አሊያንስም ሆነ ኢንካታ ፍሪደም ፓርቲ ኢኤፍኤን ከሥልጣን ውጪ ለማድረግ ያንን አማራጭ ክፍት አድርገውታል” በማለት ፓዲ ሃርፐር ይናገራል።
የዲሞክራቲክ አሊያንስ ድጋፍ እያደገ መጥቷል።
ፓርቲው ባለፈው ምርጫ በከፍተኛ የነጮች ድጋፍ የተወሰነ ድምጽ ያገኘ ሲሆን፣ በዘንድሮው ምርጫ በአገሪቱ የመንግሥት ምሥረታ ዕድል ሊሰጠው ይገባል ከሚሉ ጥቁሮችም ድጋፍን አግኝቷል።
የኤኤንሲ ሌላኛው አማራጭ ከኢኤፍኤፍ ጋር በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲሁም አብላጫውን ድምጽ ያጣበታል በተባለው ሃውተንግ ግዛት ጥምረት መመሥረት ነው።
በሃውተንግ ግዛት ያሉት የኤኤንሲ መሪዎች ከኢኤፍኤፍ ጋር ጥምረትን ይመርጣሉ ተብሏል።
ሁለቱ ፓርቲዎች በአሁኑ ወቅት የጆሃንስበርግ ከተማ ምክር ቤትን በአንድነት እያስተዳደሩ ነው ያሉት።
የቀድሞ የኤኤንሲ የወጣቶች መሪ እና የኢኤፍኤፍ መሪው ጁሊየስ ማሌማ ለዚህ ጥምረት ሃሳብ ዝግጁ ነው። ማሌማ በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት እና በሚያዝያ ወር በነበረው የማዘጋጃ ቤት ስብሰባ ላይ የኢኤፍኤፍ ጥምረት አጋር ኤኤንሲ ነው የሚለውን አመለካከት አንጸባርቋል።
የኤኤንሲ የተወሰነው አካል ከኢኤፍኤፍ ጋር ጥምረትን ይደግፋል። በሌላ መልኩ ደግሞ በኤኤንሲ ውስጥ ያሉ የራማፎሳ ደጋፊዎች እንዲህ ዓይነቱ ጥምረት ለቀድሞው የነጻነት ንቅናቄ ባህል ቀውስ ይፈጥራል ብለው ያምናሉ” ስትል የደቡብ አፍሪካው ዴይሊ ማቭሪክ ጋዜጠኛ ፌሪያል ሃፋጄ በቅርቡ ጽፋ ነበር።
ደቡብ አፍሪካን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያስገባትን ይህንን ምርጫ ተከትሎ ኤኤንሲ ከባድ ውሳኔዎች ይጠብቁታል። ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚመሠረተውን መንግሥት የመወሰን ወይም የማፍረስ ሥልጣን አላቸው።
