
ከ 6 ሰአት በፊት
ሁለት ቀኝ ዘመም የእስራኤል ሚኒስትሮች አገራቸው የተኩስ አቁም ለማድረግ ከተስማማች ጥምር መንግሥቱን አፍርሰን ስልጣን እንለቃለን ሲሉ ዛቱ።
ሁለቱ ሚኒስትሮች ይህን ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጋዛ ያለውን ጦርነት ለማስቆም አማራጭ ያሉትን መፍትሄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው።
የፋይናንስ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች እና የብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትር አታማር ቤን-ጋቪር ሐማስ ሙሉ በሙሉ ሳይወገድ እስራኤል ወታደራዊ እርምጃዋን የሚያስቆም የተኩስ አቁም ስምምነት መድረስ የለባትም ብለዋል።
ሁለቱ ሚኒስትሮች ይህን ይበሉ እንጂ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ያኢር ላፒድ የኔታኒያሁ መንግሥት የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ቢወስን ለመንግሥት ድጋፍ እሰጣለሁ ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን ባቀረቡት አማራጭ መሠረት የተኩስ አቁም ስምምነቱ በሦስት ደረጃዎች ተፈጻሚ ይሆናል። በእቅዱ መሠረት በስድስት ሳምንታት ውስጥ የእስራኤል ጦር በርካታ ፍልስጤማውያን ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች ይወጣል።
ስምምነቱ በሐማስ እገታ ስር ያሉ ሰዎችን ነጻ እንደሚያወጣ እና በጋዛ ቋሚ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ አድርጎ ጋዛን ወደ መልሶ ገንባታ የሚያስገባ ነው።
ይህ እቅድ ይፋ መሆኑን ተከትሎ ሐማስ በባይደን የቀረበውን አማራጭ በበጎ እንደሚመለከተው ገልጿል። አንድ ከፍተኛ የሐማስ መሪ ለቢቢሲ ሲናገሩ እስራኤል ስምምነቱ ተፈጻሚ የምታደርግ ከሆነ ሐማስም እቅዱን ተግባራዊ ያደርጋል ብለዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ግን የሐማስ ወታደራዊ እና አስተዳደራዊ አቋም ሙሉ በሙሉ ሳይወገድ እና በእገታ ስር ያሉ ሰዎች በሙሉ ነጻ ሳይወጡ የተኩስ አቁም ለማድረግ አልስማማም ብለዋል።
- በአሜሪካ በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ለፕሬዝዳንትነት የተወዳደረ አለ? የትራምፕ ዕጣ ፈንታስ ምን ይሆናል?ከ 6 ሰአት በፊት
- የጋዛው ጦርነት እንዲቆም እስራኤል ያቀረበችውን ሐሳብ ባይደን ይፋ አደረጉ1 ሰኔ 2024
- በታሪካዊው የደቡብ አፍሪካ ምርጫ ኤኤንሲ አብላጫ ድምጽ ለምን አጣ? የትኞቹስ ፓርቲዎች ከፍ አሉ?ከ 6 ሰአት በፊት
የፋይናንስ ሚኒስትሩ ስሞትሪች አሜሪካ ያቀረበችውን አማራጭ ተፈጻሚ የሚያደርግ መንግሥት አካል ሆነው መቀጠል እንደማይችሉ ለጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ አሳውቄያለሁ ብለዋል።
የፋይናንስ ሚኒስትሩን ሐሳብ የተጋሩት የብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትሩ ቤን-ጋቪር “ስምምነቱ . . . ሐማስን የማጥፋት ዓላማው ተትቶ ጦርነት የሚያስቆም ነው። ይህ ለሽብርተኝነት ድል የሚሰጥ እና የእስራኤልን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ቸልተኛ አማራጭ ነው” ብለዋል።
የደኅንነት ሚኒስትሩ ስምምነቱ ተግባራዊ ከሆነ የእስራኤልን ጥምር መንግሥትን ለማፍረስ የተቻለኝ አድርጋለሁ ሲሉ ዝተዋል።
በአሁኑ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ቀኝ ዘመም ጥምር ፓርቲ በፓርላማ ውስጥ በአስተኛ ቁጥር ነው አብላጫውን ወንበር ይዞ የሚገኘው።
ጥምር መንግሥቱ በፓርላማ አብላጫ ወንበር የያዘው ከቤን-ጋቪር ፓርቲ ስድስት ወንበር እንዲሁም ከስሞትሪች የጺዮናዊ ፓርቲ 7 ወንበር በመደመር ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከግብጽ፣ ኳታር እና አሜሪካ የተወጣጡ አደራዳሪዎች እስራኤል እና ሐማስ ባይደን ያቀረቡትን አማራጭ ተፈጻሚ ለማድረግ ወደ ተግባር እንዲገቡ ጠይቀዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክም እንዲሁ ለእቅዱ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።