
Saturday, 01 June 2024 20:47
Written by Administrator
ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ፣ በርበራ ወደብ በኩል ነዳጅ ለማስገባት መስማማቷን የበርበራ ከተማ ከንቲባ አብዲሽኩር መሃሙድ ሃሰን ተናግረዋል። ከንቲባው ይህንን የተናገሩት የሶማሌላንድ የነጻነት በዓል በአዲስ አበባ የሶማሌላንድ ኤምባሲ በተከበረበት ወቅት ነው።
አብዲሽኩር፤ ኢትዮጵያ የነዳጅ ምርት የምታስመጣበትን ወደብ ወደ በርበራ እንደምትቀይር ያብራሩ ሲሆን፣ የገቢ ምርቶቿንም ለማስገባት ወደቡ ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከንቲባ አብዲሽኩር መሃሙድ ንግግር ያደረጉት 33ኛው ዓመት የሶማሊላንድ የነጻነት በዓል ባለፈው ማክሰኞ ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የሶማሌላንድ ኤምባሲ በተከበረበት ወቅት ነው። እንደ ”በርበራ ታይምስ” ዘገባ፤ በዚህ ክብረ በዓል ላይ የኤምባሲው ባለስልጣናት፣ የሶማሌላንድ ከተሞች ከንቲባዎች፣ ፖለቲከኞችና የፓርላማ አባላት ታድመዋል፡፡
ከንቲባው “ተደርጓል” ያሉት ስምምነት መቼ በትክክል ወደ ስራ እንደሚገባ የገለጹት ነገር የለም። እስካሁን ከኢትዮጵያም ሆነ ከሶማሌላንድ መንግስታት በጉዳዩ ላይ ይፋዊ መግለጫ አልተሰጠም፡፡
ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረሙ በርካታ ወራት ተቆጥረዋል።
በስምምነቱ መሰረት፣ ሶማሌላንድ ለኢትዮጵያ ወደብ ስትሰጥ፤ ኢትዮጵያ በምላሹ ለሶማሌላንድ የአገርነት ዕውቅና ትሰጣለች።
ይሁንና ሶማሊያ ስምምነቱን “ሉዓላዊነቴን የሚጻረር ነው” ስትል ክፉኛ መኮነንዋ አይዘነጋም፡፡ ሶማሌላንድ ከሶማሊያ ራሷን ገንጥላ ነጻነቷን ያወጀችው ግንቦት 12 ቀን 1983 ዓ.ም. ላይ ነበር።