Addis Admas 

Saturday, 01 June 2024 20:44

Written by  Administrator

የደቡብ ጎንደር ዞን፣ ታች ጋይንት ወረዳ፣ የእናት ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ዲበኩሉ፣ በጸጥታ ሃይሎች መታሰራቸውን ፓርቲው አስታውቋል።  ”የአባላቱ እስራት የፖለቲካ ስብራታችን አንድ ማሳያ ነው” ብሏል፤ እናት።
ፓርቲው ሰሞኑን በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ባሰራጨው መረጃ፤ አቶ ሰለሞን ዲበኩሉ በጸጥታ ሃይሎች ተይዘው የታሰሩት ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ነበር። በአሁኑ ወቅት ሰብሳቢው በላይ ጋይንት ወረዳ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ እንደሚገኙ ነው ፓርቲው የጠቆመው።
አቶ ሰለሞን የታሰሩበትን ምክንያት የጸጥታ ሃይሎቹ እንዳልነገሯቸው እናት ፓርቲ በመግለጫው አትቷል። እስካሁን  የተመሰረተባቸው ክስ እንደሌለም ተጠቁሟል፡፡
 የአባላቱን እስራት “የፖለቲካችን ስብራት አንድ ማሳያ ነው” ያለው  ፓርቲው፤ “ትግላችን ሰላማዊ በመሆኑ መንግስት አባላቶቻችንን እያሳደደ ማሰሩን ያቁም” ሲል አሳስቧል።
የፓርቲው ሕግና ሥነ ስርዓት ክፍል ሃላፊ አቶ ዋለልኝ አስፋው ባለፈው ሰኞ  ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ሃይሌ ጋርመንት አካባቢ በሚገኘው፣ ግራር ሰፈር ፖሊስ ጣቢያ ለአንድ ቀን ታስረው፣ በነጋታው ከእስር መፈታታቸው ከእናት ፓርቲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በጉዳዩ ዙሪያ አዲስ አድማስ የእናት ፓርቲ አመራሮችን በስልክ ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል። ከሳምንታት በፊት እናት ፓርቲ ከመኢአድ ጋር ባወጣው መግለጫ፤ በስድስተኛው ዙር ቀሪና ድጋሚ ምርጫ እንደማይሳተፍ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ፓርቲው ለዚህ ውሳኔው ያቀረበው ምክንያትም፤ “ምርጫውን ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታ የለም” የሚል ነው።