
Saturday, 01 June 2024 20:44
Written by Administrator
ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ግጭት በማገርሸቱ ሳቢያ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የሕክምና አገልግሎት እያገኙ አለመሆኑን አስታውቋል። በኢትዮጵያ የኮሚቴው ቡድን መሪ ኒኮላስ ቮን አርክስ እንደተናገሩት፣ ኮሚቴው በግጭቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ ከሆኑ ሃይሎች ጋር በመገናኘት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕጎችን እንዲያከብሩ በተደጋጋሚ እየወተወተ ይገኛል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ የተቀሰቀሰው የአማራ ክልል ግጭት፣ የጤና ተቋማት አገልግሎት እንዳይሰጡ ያደናቀፈ ሲሆን፤ መድሃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶችን ማሰራጨት ፈታኝ ሆኗል፡፡ በተመሳሳይ፣ በኦሮሚያ ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ አለመረጋጋቱ፤ የትግራይ ክልል ደግሞ በጦርነቱ ምክንያት የደረሰው ተጽዕኖ ሕዝቡ የጤና አገልግሎት እንዳያገኝ ዕንቅፋት መፍጠራቸው ተጠቁሟል።
“ችግሩን ለመፍታት በተወሰኑ አካባቢዎች እየተንቀሳቀስኩ ነው” ያለው ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፤ ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ ከ100 በላይ የጤና ተቋማት ዕርዳታ ማሰራጨቱን ጠቁሟል፡፡
ከእነዚህም ውስጥ በአማራ ክልል ለ62 የጤና ተቋማት፣ በኦሮሚያ ክልል ለ17፣ በትግራይ ክልል ለ20 እና በሶማሌ ክልል ለ6 የጤና ተቋማት ድጋፍ ማድረጉን ኮሚቴው በድረ ገጹ ባሰራጨው መረጃ ጠቅሷል።
በኢትዮጵያ፣ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የጤና እንቅስቃሴዎች አስተባባሪ ሲላስ ሙካንጉ፤ “በተለያዩ አካባቢዎች በግጭትና ጥቃት የተጎዱ ዜጎች ያሉበት ችግር አሳሳቢ ነው።
የሪፈር ስርዓት በመቋረጡ፣ ተጨማሪ የሕክምና አገልግሎት የሚያሻቸው ዜጎች ተጨማሪ አገልግሎት ለማግኘት አልቻሉም።” ሲሉ ተናግረዋል።