ዜና ከሥራ የተሰናበቱ ዳኞችን ለሁለት ዓመታት ጥብቅና እንዳይቆሙ የከለከለ የአዋጅ ድንጋጌ እንዲሻር ጥያቄ…

ታምሩ ጽጌ

ቀን: June 2, 2024

ከሥራው የተሰናተ ዳኛ ሥራውን ካቆመበት የመጨረሻ ቀን ጀምሮ ለሁለት ዓመታት ይሠራበት በነበረው የፌዴራል ፍርድ ቤት ደረጃ በማናቸውም ችሎት በጥብቅና እንዳይቆም የሚከለክለው የፌዴራል ዳኝነት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1233/2013 አንቀጽ 32(1) ድንጋጌ፣ ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን በመሆኑ እንዲሰረዝ ወይም የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት ጥያቄ ቀረበ፡፡

ቀደም ብሎ በዳኝነት ያገለግሉ የነበሩ በርካታ ዳኞችና ከዳኝነት ሥራቸው ለቀው በጥብቅና ሙያ ላይ የተሰማሩ የሕግ ባለሙያዎች የአዋጁ ድንጋጌ ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን መሆኑን በዝርዝር በመጥቀስ፣ ትርጉም እንዲሰጥበትና እንዲሻር ወይም እንዲስተካከል ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳብ እንዲያስተላልፍላቸው ማመልከቻውን ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አቅርበዋል፡፡

አዋጁ ከዳኝነት ሥራ ተሰናብተው በጥብቅና ሙያ የሚሰማሩ የሕግ ባለሙያዎችን ለሁለት ዓመታት የከለከለው የሕገ መንግሥቱን አቀጽ 25 ማለትም ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል መሆኑንና ልዩነት ሳይደረግ ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብትን፣ አንቀጽ 40(1 እና 2) ድንጋጌ ማለትም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በጉልበቱ፣ በዕውቀቱና በካፒታሉ ንብረት የማፍራት ሰብዓዊ መብት እንዳለውና መተዳደሪያውን፣ ሥራውንና ሙያውን በመምረጥ በአገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ በነፃነት የመሥራት መብት እንዳለው ተደንግጎ የሚገኘውን፣ በአንቀጽ 41(1 እና 2) ድንጋጌ ደግሞ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሥራውንና ሙያውን ያለምንም ገደብ መርጦ የመሥራት መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት እንዳለው የሚደነግገውን ድንጋጌ የሚቃረን መሆኑን በማመልከቻቸው ገልጸዋል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን እንዳለው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62(1)፣ 83 እና በአዋጅ ቁጥር 1261/13 አንቀጽ 5(1 እና 2) ድንጋጌዎች መገለጹን ያብራሩት አመልካቾቹ አጣሪ ጉባዔውም ያቀረቡትን አቤቱታ መርምሮና አጣርቶ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 84(2) እና በተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 798/2005 አንቀጽ 5(3) ድንጋጌ መሠረት ማቅረብ እንደሚችልም አክለዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ሙያን መርጦ ለመተዳደሪያነት በመሥራት መብት ላይ ምንም ዓይነት የጊዜም ሆነ የቦታ ገደብ እንዳላስቀመጠ ጠቅሰው፣ የሰብዓዊ መብቶች ገደብ የሚጣልባቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ጊዜ ብቻ መሆኑን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 ሥር መደንገጉንም አስታውቀዋል፡፡

የጥብቅና ሥራ የሙያ ሥራ መሆኑንና ከፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1249/13፣ እንዲሁም ከአዲሱ የንግድ ሕግና ከጠበቆች የሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 57/92 አንፃር ሲታይም ሙያውን መርጦ ለመሥራት አንድ ጠበቃ አስቀድሞ በዳኝነት ያያቸውን ጉዳዮችና በሥራው ምክንያት ያወቀውን ሚስጥር የመጠበቅ ግዴታ ስላለበት በጠበቃነት ቆሞ መከራከር እንደማይቻልም ተደንግጎ ሳለ፣ ለሁለት ዓመታት ክልከላ መጣል ኢሕገ መንግሥታዊ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ክልከላ የጣለው አዋጅ ቁጥር 1233/13 አንቀጽ 32 (1) ድንጋጌ ዓላማው ወይም ምክንያቱ ግልጽ እንዳልሆነ የገለጹት አመልካቾቹ፣ ከላይ አንድ ጠበቃ በዳኝነት ያያቸውንና ያወቃቸው ጉዳዮች ላይ ጥብቅና እንዳይቆም በአዋጅና በደንብ ክልከላ ከማስቀመጡም በተጨማሪ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያወጣው የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመርያ አንድ ጠበቃ ዳኛ ሆኖ ያያቸው ወይም ያወቃቸው ጉዳዮች ከስድስት እስከ 12 ወራት ሊቆዩ እንደሚችሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በተጠቀሰው ጊዜ ብቻ ክልከላ መጣሉንም አብራርተዋል፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን ክልከላዎች ባላከበረ ጠበቃ ላይ የአስተዳደራዊ፣ የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ኃላፊነቶችን ስለሚጥል ባለሙያውም ያንን እያወቀ ድርጊቱን እንደማይፈጽምና ክልከላው ተገቢ እንዳልሆነ ማመልከቻ አቅራቢዎቹ አስታውቀዋል፡፡ ምናልባት ጠበቆች ዳኛ በነበሩበት ጊዜ የሚያውቁት ዳኛ ካለና ባላቸው ቅርበት ፍትሕ እንዳይሰጡ ያስቸግራል በሚል ከሆነ ክልከላው የተጣለው፣ በአዋጅ ቁጥር 1234/13 አንቀጽ 33 ድጋጌ መሠረት ዳኞቹ ከያዙት ጉዳይ ላይ መነሳት እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡ ጠበቆችም ድርጊቱን ከፈጸሙ በአዋጅ ቁጥር 1234/13 አንቀጽ 85(12) ድንጋጌ መሠረት የዲሲፕሊን ቅጣት እንደሚጣልባቸውም አክለዋል፡፡

በአጠቃላይ ጠበቃው ዳኛ ሆኖ በሠራበት የመጨረሻ ችሎት ወይም ምድብ ችሎት ላይ ብቻ እንዳይሠራ ማድረግ እየተቻለ፣ በአጠቃላይ በፍርድ ቤቱ ለሁለት ዓመታት እንዳይሠራ ማድረግ ኢሕገ መንግሥታዊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የአዋጁ ድንጋጌ ዓላማና የዳኞችን ከሥራ መልቀቅ ለመገደብ ወይም የሰው ኃይል ፍልሰትን ለመቀነስ ታስቦ ከሆነም በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን በነፃነት ሙያን መርጦ የመሥራት መብትን የሚጥስ መሆኑን፣ የሕገ መንግሥቱን አዋጅ ቁጥር 78 እና 79 ድንጋጌዎችን መጣስም መሆኑንም በመግለጽ አብራርተዋል፡፡

ዳኞች በፈለጉበት ጊዜ ሥራቸውን ለቀው በጥብቅና ሙያ ላይ እንዳይሰማሩና ያለ ፍላጎታቸው ሥራቸውን በችግር ውስጥ ሆነው እንዲሠሩ፣ በተፈለገው መጠን ውጤታማ ሥራ እንዳይሠሩ የሚያደርግና ወደ ዳኝነት ለመምጣት ፍላጎት ያላቸውንም ዜጎች የሚያሸሽ ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በመሆነም በገለጿቸው ዝርዝር የሕግ ድንጋጌዎች፣ ሐሳቦች፣ ምክንያቶችና ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ታይተው ያቀረቡትን ማመልከቻ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረኑ መሆኑን በመመርመርና በመግለጽ፣ አዋጁ እንዲሰረዝ ወይም ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም እንዲሰጥበት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲልክላቸው ጠይቀዋል፡፡